የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ያዘጋጀው የውይይት መድረክ የቀትር በኋላ ውሎ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ያስጠናው ጥናት የሚያቀርብበት መርሐ-ግብር በከሰዓት ውሎው \”የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ\” እና \”የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ\” በሚሉ ርዕሶች ላይ ውይይት ተደርጎበታል።

አንድ ዓመት ተኩል በፈጀ ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ያስጠናውን ጥናት በዛሬው ዕለት ለበርካታ የስፖርቱ የባለ-ድርሻ አካላት መቅረብ መጀመሩን ከረፋድ ጀምሮ ተከታታይ ዘገባዎችን ስንሰራ ነበር። ከቀትር በፊት የነበረውን ዝርዝር ጉዳይ አስነብበን የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ከሰዓት በኋላ የነበሩ የውይይት ሀሳቦችን እናቀርባለን። በዋናነትም \”ከክለብ ፍቃድ አሰጣጥ መመሪያ\” እና \”የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ\” ጋር ተያይዞ በተነሱት ሁለት አጀንዳዎች ላይ ከመድረኩ መነሻ ሀሳብ ተንፀባርቆ በመቀጠል ተሳታፊዎች በቡድን ተከፋፍለው ውይይት እንዲከውኑ ተደርጓል።

በቅድሚያ ዶ/ር ጋሻው አብዛ በጥናታቸው ላይ በትኩረት ያጠነጠኑበት ጉዳይ የክለብ ፍቃድ አሰጣጥ መመሪያን በተመለከተ እንደሆነ ገልፀዋል። በዚህም በዋናነት ፊፋ የክለብ ፍቃድ አሰጣጥ ላይ ያስቀመጣቸውን አላማዎች፣ መስፈርቱን በማያሟሉ ክለቦች ላይ የሚጣለውን ቅጣት ወይም ገደብ እንዲሁም ደረጃዎችን በማንሳት ማብራሪያቸውን ጀምረዋል። በቅድሚያ ደግሞ በክለብ ፍቃድ አሰጣጣት መመሪያ መስፈርቶች ላይ ያሉትን አምስት አንኳር ሀሳቦች አብራርተዋል። በዚህም የስፖርት ልማት መስፈርቶች፣ የመሰረተ ልማት መስፈርቶች፣ የሰው ኃይል እና አስተዳደራዊ መመዘኛዎች፣ ህጋዊ መስፈርቶች እንዲሁም ፋይናንስን በተመለከተ ዝርዝር ነጥቦች አውስተዋል።

\"\"

ዶ/ር ጋሻው አስከትለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ክለባት ፍቃድ የህግ ማዕቀፍ ላይ 2005 ላይ ከፊፋ በፊት የኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ማኅበራት ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ የደነገገውን ዝርዝር አንስተው በሀገራችን የሚገኙ ክለቦች የፊፋ እና ካፍ የክለብ ፍቃድ አሰጣጥ መመሪያን ብቻ ሳይሆን 2005 ላይ የፀደቀው የስፖርት ማኅበራት እንዲያሟሉ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እና የሊጉ አክሲዮን ማኅበር አስገድደው ክለቦች እንዲያሟሉት ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል። በመጨረሻም ተሳታፊዎች በየቡድኖቻቸው የሚያደርጉትን ውይይት ከመጀመራቸው በፊት ከክለብ ፍቃድ አሰጣጥ መመሪያ ጋር በተያያዘ የባለ ድርሻ አካላት እይታን አጋርተዋል። በዋናነትም የግንዛቤ እጥረት እና የቁርጠኝነት እጦት በእይታው እንደተካተተ ገልፀው የፍቃድ አሰጣጥ መመሪያው አቀራረፁ፣ አቀራረቡ እና አተገባበሩን በተመለከተ ምክረ-ሀሳብ አቅርበው ውይይቱ ተጀምሯል።

በማስከተል በቡድን ከተቦደኑት የክለብ ሥራ-አስኪያጆች እና ፕሬዝዳንቶች፣ የአክሲዮን ማኅበሩ እንዲሁም የእግርኳስ ፌዴሬሽኑ አመራሮች፣ የክልሎች ወጣቶች እና ስፖርት ቢሮ ተወካዮች፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተወካዮች እና የአክሲዮን ማኅበሩ የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴ አባላት፣ የስፖርት ባለሙያዎች (ዳኞች እና ኮሚሽነሮች)፣አሠልጣኞች እንዲሁም የሙያ ማኅበራት የተወያዩበትን ሀሳብን እንዲያንፀባርቁ ተደርጓል። በዚህ የተሳታፊዎች መድረክ ላይ በአስገዳጅነት መመሪያ ተዘጋጅቶ እንዲተገበር ተደርጎ የማትጊያ አማራጮች እንዲቀርቡ፣ ደረጃ በደረጃ ክለቦች እንዲያሟሉት እንዲደረግ፣ ከዚህ በፊት የተስተዋሉ የአስፈፃሚ አካል አተገባበር ክፍተት እንዳይደገም መስራት፣ ያሉ የግንዛቤ ችግሮችን መቅረፍ፣ የአበረታች ንጥረ ነገሮች ጉዳይ እና አተገባበሩን የሚከታተሉ አካላት ሚና ከብዙ በጥቂቱ የተነሱ ሀሳቦች ሲሆኑ ለአጥኚው አካልም ግብዐት የሚሆኑት ተይዘው የዳበሩ ሀሳቦች በጥናቱ እንደሚካተቱ ተመላክቷል።

\"\"

የሻይ ዕረፍት ከተደረገ በኋላ ደግሞ የክለቦች የባለቤትነት ይዞታን በተመለከተ ሀሳቦች መንሸራሸር ይዘዋል። እንደ መጀመሪያው አጀንዳ ጥናቱን ያጠኑት ዶ/ር ጋሻው በጉዳዩ ዙሪያ መነሻ ገለፃ አድርገዋል። በዚህም በክለቦች የባለቤትነት ይዞታ ላይ የባለድርሻ አካላት እይታ፣ የሀገራት ተሞክሮ (የአውሮፓ እና የአፍሪካ የእግርኳስ ክለባት የባለቤትነት ይዞታ)፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ ክለባት ተሞክሮ፣ የኢትዮጵያ እግርኳስ እና የህግ ማዕቀፍ (የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የስፖርት ፖሊሲ እና የፌዴራል የስፖርት ኮሚሽን መመሪያ)እንዲሁም የኢትዮጵያ ክለባት በንግዱ ዓለም የመመዝገባቸው አውድ ላይ ያሉ ሀሳቦችን አንስተው ጥናቱ ያቀረበውን ምክረ-ሀሳብ በማስታወስ ዳግም የቡድን ውይይቱ ቀርቧል።

በዚህ ጉዳይ ላይም ቡድኖቹ በዋናነት የመንግስት የክለብ ባለቤትነት ይዞታ ላይ ተደጋጋሚ ሀሳቦች አንፀባርቀዋል። በአብላጫው መንግስት በአንዴ ሳይሆን ቀስ በቀስ ከባለቤትነት ይዞታ የሚወጣበት አካሄድ እንዲፈጠር እንዲደረግ ተገልጿል። ከመንግስት ጎን ለጎን ግን ባለ-ሀብቶች እና የተመዘገቡ ደጋፊዎችን ወደ ባለቤትነት ድርሻ እንዲመጡ ማድረግ እንደሚገባ ተመላክቷል።

የመጀመሪያው ቀን ውሎም ረፋድ ላይ ተጀምሮ ምሽት 12:40 ሲል ፍፃሜውን አድርጎ ለነገ 3 ሰዓት ቀጠሮ ይዞ ተጠናቋል።