አክሲዮን ማኅበሩ ያስጠናውን ጥናት እያቀረበ በሚገኝበት ሲምፖዚየም የሁለተኛ ቀን ቆይታ \”የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደርን\” በተመለከተ ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
በእግርኳሳችን ላይ ያሉ ችግሮችን የተመለከተው እና \”ዘርፈ ብዙ የግምገማ ጥናት እና የልማት ፍኖተ ካርታ\” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ጥናት በትናንትናው ዕለት በርካታ የእግርኳሱ ባለ-ድርሻ አካላት በተገኙበት በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል መቅረብ መጀመሩ ይታወቃል። በትናንት ውሎውም \”የክለብ ፈቃድ አሰጣጥ መመሪያ\” እና \”የክለቦች የባለቤትነት ይዞታ\” በሚሉ ሁለት አንኳር ርዕሶች ላይ የጥናቱ ግኝት እና ምክረ-ሀሳብ ቀርቦ ከተሳታፊያን የተለያዩ ሀሳቦች የተንሸራሸሩበት ሲሆን ዛሬ ደግሞ ትናንት በተነሳው ሁለተኛ ሀሳብ ላይ ያተኮረ ፈተና ለተሳታፊዎች ተሰጥቶ \”የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳድር\” ወደሚለው የዛሬ የጠዋት አጀንዳ ተገብቷል። እንደ ትናንቱ ተሳታፊዎች በየቡድኖቻቸው በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ውይይት ከማድረጋቸው በፊት ጥናቱን ያጠናውን ቡድን በበላይነት የመሩት ዶ/ር ጋሻው አብዛ መነሻ ገለፃዎችን አድርገዋል።
ዶ/ር ጋሻው በንግግራቸው መግቢያ ይህ የተጫዋቾች ክፍያ አስተዳደር በዋናው ጥናት ነጥረው ከወጡ ትኩረት የሚሹ አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል አንዱን እንደሆነ ገልፀው በጥናቱ የባለ-ድርሻ አካላት እይታ፣ የሀገራት ተሞክሮ እና ገዢ የህግ ማዕቀፍ ተቀናብረው በሰነዱ እንደተካተተ እንዲሁም \’ሀገር በቀል የተጫዋቾች ክፍያ የአሰራር ስርዓት\’ ዙሪያ አማራጭ መንገዶች እና ምክረ-ሀሳቦች ተሰናድተው ለውይይት እንደቀረበ አመላክተዋል።
በተሞክሮዎች ዳሰሳ ላይ የአውሮፓ እግርኳስ ማኅበራት ህብረት የገንዘብ አወጣጥ ጨዋነት መመሪያ (Financial fair play) የክለቦች የገንዘብ አወጣጥ መመዘኛ እና መቆጣጠሪያ መንገድ የሆነበት ሂደት ምልከታ እንደተደረገበት በዝርዝር አስረድተዋል። ከዚህ ተቋም ተሞክሮ በተጨማሪ የፈረንሳይ ሊግ 1፣ የስፔን ላሊጋ፣ የጣሊያን ሴሪ ኤ፣ የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ፣ የሰሜን አሜሪካ ፉትቦል ሊግ (NFL)፣ የሰሜን አሜሪካው ቤዝቦል ሊግ (MLB) እና የሰሜን አሜሪካው ቅርጫት ኳስ ሊግ (NBA) ላይ ያሉ ሌሎች ተሞክሮዎችን ተነስተው ለተሳታፊያኑ ተመላክተዋል። በዋናነት ደግሞ የሌሎችን ሀገራት ተሞክሮዎች ወደ ኢትዮጵያ ለማውረድ በመሞከር ሂደት ውስጥ ለሜዳ ላይ ውድድሮች ዘላቂ እና ቁልፍ የሆኑ መሰረታዊ እውነታዎችን መዘንጋት እንደማይገባ አስታውሰው የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታዎች ያገናዘበ ሀገር-በቀል የሆነ የተጫዋቾች ክፍያ አሰራር ስርዓት ለመዘርጋት እያንዳንዱን ልምድ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የሚጣጣሙ ተሞክሮዎችን መዞ በማውጣት፣ የባለ-ድርሻ አካላትን እይታ ተካተው እንዲሁም ከፊፋ፣ ካፍ እና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ መመሪያዎች እና ከሰራተኞች ህግ ጋር በማስታረቅ የቀረበውን ምክረ-ሀሳብ አጋርተዋል።
በምክረ-ሀሳቡ ላይ ደግሞ መነሻ እውነታዎች ሲቀርቡ ጥናቱ ሲጠና የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ክለቦች አሁን ባለው አሰራር እያንዳንዱ ክለብ በአማካይ 70% (ወደ 40 ሚሊዮን ብር) ወጪው ለደሞዝ ክፍያ የሚውል መሆኑ (በአማካይ ለአንድ ተጫዋች በዓመት 1.6 ሚሊዮን ብር) እና በአንድ ዶላር የምንዛሬ ተመን በወር አንድ ተጫዋች 2667 ዶላር እንደሚያገኝ በጥናቱ ተጠቁሞ በአፍሪካ ሀገራት ያለው የደሞዝ አሀዝ እንደ ማነፃፀሪያ ተነስቷል። ይህንን ተንተርሶ የቀጣይ የውድድር ዓመት ከመጀመሩ ቢያንስ ከ6 ወራት በፊት የመጪውን ዓመት ገቢና ወጪ በዝርዝር እና በግልፅ የሚያሳይ በጀት ለሊጉ ጽ/ቤት ለግምገማ እንዲቀርብ ማድረግ፣ ሊጉ \”ልማትን ያማከለ የደሞዝ ክፍያ\” እንዲከተል ማድረግ፣ ከመንግስት የሚገኘው ገቢ ለደሞዝ ከሚውለው መጠን 50%ቱ ለልማታዊ ተግባራት (የቢሪ፣ አደረጃጀት፣ የልምምድ ሜዳ ግንባታ እና የስታዲየም ግንባታ እና ማሻሻያ)እንዲውል ማድረግ እና ክለቦች የሚያገኙትን ኦርጋኒክ ገቢ (የቲቪ መብት ድርሻ እና የስፖንሰርሺፕ ገቢዎች) ሙሉ ለሙሉ ለተጫዋቾች ደሞዝ እንዲውል የሚጠቁም ምክረ-ሀሳቦች ቀርቧል።
በአጠቃላይ የተጠቀሰውን \”ልማትን ያማከለ የደሞዝ ክፍያ\” ስርዓት ለማስፈን እና ከሀገራችን እውነታ ጋር የታረቀ የደሞዝ ክፍያ ለማስፈን የአጭር ጊዜ እቅድ በሚል ለውድድር ዘመን ዋስትና ከበጀት ጋር ማቅረብ፣ የመካከለኛ ጊዜ እቅድ በሚል ገቢ ማስፋት እንዲሁም የረጅም ጊዜ እቅድ በሚል ህዝባዊ ማድረግ የሚሉ ሦስት ማዕቀፎችን አብራርተው ከተሳታፊዎች ግብዐት መሰብሰቢያ የቡድን ውይይት መደረግ ጀምሯል።
በውይይቱ አብዛኞቹ ቡድኖች ይህ ጉዳይ አንገብጋቢ እንደሆነ ሲገልፁ የተሰማ ሲሆን ከደሞዙ በላይ ክለቦች ያላቸው ቁመና እና የረጅም ጊዜ እቅድ ልክ አለመሆን፣ ይህንን ችግር ስለተፈጠረበት ምክንያት፣ የተጫዋቾች ዝውውር ላይ ስላሉ እንከኖች እና ግልፅነት፣ በታዳጊ ተጫዋቾች ላይ ስላሉ የተዳከሙ ስራዎች እና የመንግስት እንዲሁም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ቁርጠኝነት ላይ ያሉ ውስንነቶች ተነስተዋል።
ከዚህ ከተጫዋቾች ዝውውር ጋር ተያይዞ ስለሚነሱ ችግሮች የአክሲዮን ማኅበሩ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ሊጉ ከመንግስት ጋር ተነጋግሮ በተጫዋቾች የዝውውር ሂደት አላስፈላጊ አካላት የሚያደርጉትን ጣልቃ እና የገንዘብ ሽሚያ ሊያስቆም የሚችል ደንብ እንዲወጣ ስራዎች እንደሚሰሩ አመላክተው ይህንን ሲያደርር የተገኘ ሰው በወንጀል እንዲጠየቅ እንደሚደረግ አመላክተዋል። የመዝጊያ ንግግር እያደረጉ የሚገኙት ሰብሳቢው ዛሬ የተሰበሰበው ግብዐት በጥናቱ ተካቶ በመፅሐፍ መልክ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ እንደሚገባ አመላክተው ውይይቱ ተጠናቋል።
በመጨረሻም በሲምፖዚየሙ ላይ በተሰጡት ሁለት ፈተናዎች ከፍተኛ ውጤት ያመጡ ስድስት ግለሰቦች የሽልማት አሰጣጥ መርሐ-ግብር ተደርጓላቸዋል። በዚህም አቶ ይግዛው ብዙአየሁ፣ አቶ ንዋይ በየነ እና አቶ በረከት ከ19 ነጥብ 19 ነጥብ በማግኘት በቅደም ተከተላቸው የዲ ኤስ ቲቪ ዲኮደር እና የ6፣4 እና 2 ወር ነፃ ፓኬጅ ሽልማት ሲበረከትላቸው ከ19 18 ያመጡት አቶ አማኑኤል አስራት፣ አቶ ይስማሸዋ ሰይፈ እና አቶ ሸዋንግዛው ተባበል የዲኮደር እና የአንድ ወር ነፃ ፓኬጅ ሽልማት ተሰጥቷቸዋል።
የሁለተኛ ቀን ውሎውም ረፋድ 3 ሰዓት ጀምሮ 8 ሰዓት ሲል ተጠናቋል።