ቻን | የዋልያዎቹ የቻን የመጀመሪያ ጨዋታ በእንስት ዳኞች ይመራል

ቅዳሜ 10 ሰዓት የሚደረገውን የኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ ጨዋታ ሦስት እንስት ዋና እና ረዳት ዳኞች እንደሚመሩት ታውቋል።

7ኛው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒየንሺፕ ውድድር በነገው ዕለት አስተናጋጇ አልጄሪያ ከሊቢያ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ጅማሮውን ያደርጋል። በዚሁ ምድብ የምትገኘው ሀገራችን ኢትዮጵያ በበኩሏ የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋን ከሞዛምቢክ ጋር ቅዳሜ 10 ሰዓት ላይ የምታደርግ ይሆናል። ይህንን ጨዋታ ደግሞ በመሐል ዳኝነት የሚመሩት ቶጓዊው እንስት አልቢትር ቪንሴንቲያ እንዮናም አሜዶሜ እንደሆኑ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል።

\"\"

በዚህ ውድድር በመሐል ዳኝነት እንዲያገለግሉ ከተመረጡ ሦስት እንስት ዳኞች መካከል አንዷ የሆነችው ቪንሴንቲያ አሜዶሜ ከዚህ ቀደም የወንድ እና የሴት አህጉራዊ የሀገራት እንዲሁም የክለብ ውድድሮችን መርታ የምታውቅ ሲሆን ከሰባት ወራት በኋላ በኒውዝላንድ እና አውስትራሊያ በሚደረገው የሴቶች የዓለም ዋንጫ ላይ ግልጋሎት እንዲሰጡ ከተመረጡ የአፍሪካ አልቢትሮች መካከልም አንዷ ነች።

ከቪንሴንቲያ አሜዶሜ ጋር በመሆን የቅዳሜውን የኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ ጨዋታ ካሜሩናዊቷ ካሪን አተዛምቦንግ ፎሞ እና ዛምቢያዊቷ ዲያና ቺኮቴሻ በረዳትነት እንዲሁም ከቱኒዚያ የተመረጡት ሜህሬዝ ሜልኪ አራተኛ ዳኛ ሆነው ይመሩታል። ሞሪታኒያዊው ማሳ ዲያራ በበኩላቸው የጨዋታው ኮሚሽነር ሲሆኑ ከቱኒዚያ እና ሞሮኮ የመጡ ሌሎች አልቢትሮች ደግሞ የቪ ኤ አር ዳኝነቱ ላይ እንደተሰየሙ ታውቋል።

\"\"