የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | ተጠባቂው የንግድ ባንክ እና መቻል ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ12ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሁለተኛ ቀኑ ዛሬም ቀጥሎ የተጠበቀው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻል ጨዋታ ያለ ጎል ሲጠናቀቅ አዲስ አበባ ከተማ ከ ይርጋጨፌ ቡና ፍልሚያ ደግሞ 1ለ1 በሆነ ውጤት ፍፃሜውን አግኝቷል።

ሀዋሳ ከተማ ላይ እየተደረገ የሚገኘው የ2015 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የሁለተኛው ዙር የ12ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ዛሬም በሁለት መርሀግብር ቀጥሎ ተደርጎ መሸናነፍን ሳያስመለክተን ተጠናቀዋል። ቀደም ብሎ አራት ሰዓት ላይ አዲስ አበባ ከተማን ከይርጋጨፌ ቡና ያገናኘው ጨዋታ ሁለት የተለያዩ መልኮችን የተላበሱ አጋማሾችን አስመልክቶን ፍፃሜውን ያገኘ ነበር። በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ብልጫን ወስደው መጫወት የቻሉት አዲስ አበባ ከተማዎች የይርጋጨፌን ደካማ የመከላከል አደረጃጀት በረጃጅም እና ተሻጋሪ ኳሶች በመጫወት ለማስከፈት ተደጋጋሚ ጥረትን አድርገው 19ኛው ደቂቃ ላይ በተጋጣሚያቸው መረብ ላይ ግብ አስቆጥረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃ ላይ ቤቴልሄም መንተሎ በረጅሙ ወደ ይርጋጨፌ የግብ ክልል ያሳለፈችላትን ድንቅ ኳስ አስራት ዓለሙ ፍጥነቷን ተጠቅማ ወደ ሳጥን እየገፋች በመግባት ቡድኑን መሪ አድርጋለች።

ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ሲመለስ በቀዳሚው አርባ አምስት በተጋጣሚያቸው ተበልጠው የቆዩት ይርጋጨፌ ቡናዎች በዚህኛው አጋማሽ የተጫዋች ለውጥን አድርገው ወደ ሜዳ ከገቡ በኋላ በአንድ ሁለት ማራኪ የቅብብል መንገድ ተደጋጋሚ ያለቀላቸውን የግብ ዕድል ሲፈጥሩ ያስተዋልን ሲሆን ከመጀመሪያው አጋማሽ እንቅስቃሴያቸው መጠነኛ መቀዛቀዝ የታየባቸው አዲስ አበባ ከተማዎች በበኩላቸው በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት ሲጥሩ ቢታይም ውጤታማ ግን መሆን አልቻሉም። በአንፃሩ በእንቅስቃሴም ሆነ በግብ ሙከራዎች አመዛኙን ብልጫ ወደ ራሳቸው የወሰዱት ይርጋጨፌ ቡናዎች በዳግማዊት ሰለሞን ከሳጥን ውጪ በተቆጠረ ጎል አቻ ሆነዋል። ከጎሉም በኋላ ተጨማሪ ግብን ለማከል ይርጋጨፌዎች ጥረት ቢታይባቸውም ጨዋታው በሁለቱ አጋማሾች በተቆጠሩ ሁለት ግቦችን 1ለ1 ተደምድሟል።

\"\"

ፀሀያማ ከነበረው የሀዋሳ ዐየር በመጠኑም ቢሆንም ቀዝቀዝ ባለ ድባብ ውስጥ ሆኖ በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ የሳምንቱ ተጠባቂ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና መቻል ጨዋታ 10 ሰዓት ሲል ጅምሩን አድርጓል። ተመጣጣኝ የነበረን ሁለት አጋማሾችን ጨዋታው ቢያስመለክተንም በአመዛኙ ከወትሮ ደካማ አጨዋወታቸው በተለየ በጥንቃቄ የአጨዋወት ይዘት የቀረቡት መቻሎች ከሚፈጥሯቸው ዕድሎች አንፃር በብዙ ነገሮች ተሽለው መታየት ችለዋል።

ጨዋታው ምንም እንኳን አስቀድሞ አጓጊ የሆነ መልክ ይኖረዋል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም የጠሩ አጋጣሚዎችን በጉልህ ሳያሳየን በመጨረሻም ያለ ጎል ተጠናቋል። ሊጉን በመሪነት ላይ ተቀምጦ ማድረግ የቻለው ንግድ ባንክ ነጥቡን ሀያ ስድስት በማድረስ አሁንም ደረጃውን አስጠብቆ በመሪነቱ ሲቀጥል የአሰልጣኝ ስለሺ ገመቹው መቻል በበኩሉ እየተንሸራተተ ስድስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።

ነገ ዓርብ

ንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ 4፡00
ልደታ ክፍለ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ 10፡00

\"\"