ከፍተኛ ሊግ | የ9ኛ ሳምንት የመጀመሪያ የጨዋታ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ 12 ጨዋታዎች ሲስተናገዱበት የምድብ ሀ እና የምድብ ለ መሪዎች ነጥብ ሲጥሉ የምድብ ሐ መሪ ወደ ድል ተመልሷል።

በቶማስ ቦጋለ እና ጫላ አቤ

የ03:00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ ጅማ አባ ቡና እና ሰንዳፋ በኬን ባገናኛው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር የታየበት ቢሆንም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ጅማ አባ ቡናዎች እጅግ የተሻሉ ነበሩ። 25ኛው ደቂቃ ላይ ጃፋር ከበደ በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት የገባው እና ወደግብ ሞክሮት የግቡ የግራ ቋሚ የመለሰበት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራ የነበር ሲሆን ብሩክ ዳንኤል እና ግሩም ኩሩጌታም ከረጅም ርቀት ግሩም ሙከራዎችን ማድረግ ችለው ነበር። ከራሳቸው የሜዳ ክልል ተደራጅተው ለመውጣት እጅግ የተቸገሩት ሰንዳፋዎች በአጋማሹ ይህ ነው የሚባል የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም ነበር።

\"\"

ከዕረፍት መልስም ጥሩ ሆነው የቀረቡት አባ ቡናዎች ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ አንድ ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ጃፋር ከበደ በግንባሩ ገጭቶ ያደረገውን ሙከራ የግቡ የላዩ አግዳሚ መልሶበታል። የተጋጣሚን የማጥቃት እንቅስቃሴ መመከት የከበዳቸው በኬዎች ይባስ ብሎም 52ኛው ደቂቃ ላይ ግብ አስተናግደዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም እስጢፋኖስ ተማም ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሯል። ከግቧ መቆጠር በኋላም የአቻነት ግብ ለማስቆጠር የተሻለ የተንቀሳቀሱት ሰንዳፋዎች ባልተረጋጋ የኳስ ቅብብል ታጅበው አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። ጅማ አባ ቡናዎችም ውጤቱን አስጠብቀው በመውጣት 1-0 ማሸነፍ ችለዋል።

ጅማ ላይ የምድብ ለ መሪው ሻሸመኔ ከተማ ነጥብ ጥሏል። ከአምቦ ከተማ ጋር የተገናኘው ቡድኑ በአዲስዓለም ደሰላኝ የ37ኛ ደቂቃ ጎል ሲመራ ቢቆይም በጭማሪ ደቂቃ አምቦዎች ደረጄ ነጋሽ ከመረብ ባገናኛት ጎል ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል።

ሆሳዕና ላይ ሶዶ ከተማ እና ዳሞት ከተማ የምድብ \’ሐ\’ የዕለቱ የመጀመሪያ ተጋጣሚ ነበሩ። የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ክለቦች ጥሩ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ የታየበት እና በሁለቱም በኩል ወደ ግብ የመድረስ አጋጣሚዎችን ያገኙበት አጋማሽ ቢሆንም የገኘውን እድል በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ መልኩ ሞቅ ብሎ እና በሁለቱም ክለቦች በኩል ግብ ለማስቆጠር ፍላጎት የነበራቸው ሲሆን በጨዋታው በ61ኛው ደቂቃ የዳሞት ከተማ ግብ ጠባቂ በሰራው ስህተት አላዛር ፋሲካ በማስቆጠር ሶዶ ከተማን መሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን ከግቧ መቆጠር በኋላ ሶዶ ከተማዎች ያገቡትን ግብ ለማስጠበቅ ተጠጋግተው በማፈግፈግ መጫወት ሲጀምሩ ዳሞት ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር የበለጠ ተጭነው ሲጫወቱ ተስተውሏል። ጨዋታው በዚሁ ሁኔታ ቀጥሎ የመደበኛ ደቂቃው ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ዳሞት ከተማዎች ያገኙትን የመጨረሻ የግብ እድል በደረጀ ነጋሽ አማካኝነት በማሽቆጠር ዳሞት ከተማን ከሽንፈት መታደግ ችሏል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ተጠናቆ ነጥብ መጋራት ችለዋል።

ውጤቱንም ተከትሎ የደረጃ ግርጌ ላይ የሚገኙት  ሶዶ ከተማዎች በዘጠነኛ ሳምንትም ቢሆን የመጀመሪያ ድላቸውን ማሳካት ተስኗቸው መጀመሪያ ከነበራቸው ሁለት ነጥብ ላይ አንድ ነጥብ ጨምረው በሶስት ነጥብ አሁንም የደረጃው ግርጌ ላይ ተቀምጠዋል።

\"\"

የ05:00 ጨዋታዎች

ወሎ ኮምቦልቻ እና አዲስ ከተማ ክ/ከን ባገናኘው ጨዋታ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ወሎ ኮምቦልቻዎች 17ኛው ደቂቃ ላይ ባስቆጠሩት ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ሰለሞን ጌዲዮንን ኳስ ለማስጣል የወጣው እና ኳሱን ያገኘው የአዲስ ከተማው ግብጠባቂ ናትናኤል ተፈራ አታልሎ ለማለፍ ሲሞክር መቀማት የቻለው ሲሣይ አቡሌ ግቡ ላይ የግብጠባቂውን ቦታ ለመተካት ተጫዋቾች ቢቆሙም ከሳጥን ውጪ ከቀኝ መስመር በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።

ከወትሮው በተለየ ቀዝቀዝ ብለው ለጨዋታው የቀረቡት አዲስ ከተማዎች በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራ 28ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ከሳጥኑ የግራ ክፍል የነበረው ያሬድ ዓለማየሁ ያቀበለውን ኳስ አሸናፊ በቀለ በተረከዙ ለማስቆጠር ቢሞክርም የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ግብጠባቂው ይዞበታል።

\"\"

ከዕረፍት መልስም አዲስ ከተማዎች 59ኛው ደቂቃ ላይ አቻ የሚሆኑበት አጋጣሚ አግኝተው ነበር። ከጨዋታ ውጪ ነው በሚል የኮምቦልቻ ተከላካዮች ትኩረት ባጡበት ቅፅበት ከግብጠባቂ ጋር የተገናኘው ከተማ ገረመው ሳይጠቀምበት ቀርቶ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። ካለፉት ጨዋታዎች እጅግ ተሻሽለው ለጨዋታው የቀረቡት ወሎዎች 87ኛው ደቂቃ ላይ ናትናኤል ሌሊሣ ከግራ መስመር ከሳጥን ውጪ ባስቆጠረው ድንቅ ግብ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ የአዲስ ከተማው  አቤል ፀጋዬ በግራ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ቢሞክረውም የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል። ጨዋታውም በወሎ ኮምቦልቻ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ወሎ ኮምቦልቻ በውድድር ዓመቱ የመጀመሪያውን ሦስት ነጥብ አሳክቷል።

በምድብ ለ ንብ በኪም ላም ብቸኛ የ73ኛ ደቂቃ ጎል ጉለሌ ክፍለከተማን 1-0 መርታት ችሏል።

ሆሳዕና ላይ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ እንደተለመደው በሀምበሪቾ ዱራሜ ደጋፊዎች ደማቅ ድጋፍ የጀመረው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ የደሴ ከተማዎች ጥሩ እንቅስቃሴ የታየበትና በኳስ ቁጥጥርም ይበልጥ ተሽለው የታዩበት አጋማሽ ሲሆን በ24ተኛው ደቂቃ ላይ ደሴ ከተማዎች በማናዬ ፋንቱ አማካኝነት መሪ መሆን የቻሉ ሲሆን የመጀመሪያ አጋማሹም በደሴ ከተማዎች መሪነት ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ ሀምበሪቾ ከተማዎች የበለጠ ተሻሽለውና በሙሉ ፍላጎት ወደ ሜዳ የገቡ ሲሆን ጨዋታው በጀመረ በ50ኛው ደቂቃ የተገኘውን የመአዘን ምት የሀምበሪቾ ዱራሜው የኋላ ደጀን የሆነው እንዳለ ዮሐንስ በግንባር በማስቆጠር አቻ መሆን የቻሉ ሲሆን ከግቧ መቆጠር በኋላ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ተጭነው በመጫወት በ81ኛው ደቂቃ ልማደኛው ዳግም በቀለ የአሸናፊነቷን ግብ በማስቆጠር ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ጣፋጭ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

ውጤቱን ተከትሎ መሪዎቹ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች ነጥባቸውን ወደ 22 በማሳደግ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። በዛሬው ጨዋታ ግብ ያስቆጠሩት እንዳለ ዮሐንስ እና ዳግም በቀለ ከመጀመሪያ ጨዋታ አንስቶ ለቡድናቸው ወሳኝ መሆናቸውን እያሳዩ ይገኛሉ።

የ08:00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ በብርቱ ፉክክር በታጀበው እና ለተመልካች ማራኪ በነበረው የዱራሜ ከተማ የምድቡ መሪ ቤንች ማጂ ቡና ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ዱራሜ ከተማዎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን 13ኛው ደቂቃ ላይም አለኝታ ማርቆስ በቀኝ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ሲያሻማ ያገኘው ወንዱ ፍሬው በግንባሩ በመግጨት ባስቆጠረው ግብ መሪ መሆን ችለዋል። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው መመለስ የቻሉት ቤንች ማጂዎች 29ኛው ደቂቃ ላይ አቻ መሆን ችለዋል። ረጅብ ሚፍታ በግሩም ዕይታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ሰይድ ሰጠኝ በድንቅ የጊዜ አጠባበቅ እና አጨራረስ ግብ አስቆጥሯል። አቻ ከሆኑ በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት አቦሎቹ 40ኛው ደቂቃ ላይ መሪ ሊሆኑ የሚችሉበትን ትልቅ አጋጣሚ አባክነዋል። ዘላለም በየነ ሳጥን ውስጥ በ ተስፋሁን ተሾመ በተሠራበት ጥፋት የተገኘውን የፍጹም ቅጣት ምት ራሱ ዘላለም በየነ ሲመታ ግብጠባቂው ማፑቱ ይስሃቅ መልሶበታል። ኳሱን በድጋሚ አግኝቶት በግንባሩ ገጭቶ ቢሞክርም የግቡ የላዩ አግዳሚ መልሶበታል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ቀዝቅዞ ሲቀጥል 50ኛው ደቂቃ ላይ ጄይላን ከማል በግራ መስመር የተሰጠውን የቅጣት ምት ሲመታ ግብጠባቂው ማፑቱ ይስሃቅ በእግሩ ቢመልስበትም ኳሱ ሲመለስ ያገኘው ኤፍሬም ታምሩ በቀላሉ በማስቆጠር አቦሎቹን መሪ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውን ሲጀምር ከነበራቸው ግለት እየቀዘቀዙ የመጡት ዱራሜዎች በተደጋጋሚ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ቢያደርጉም ፈታኝ የግብ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረዋል። በቀሪ ደቂቃዎችም የተሻለ የግብ ዕድል ሳይፈጠር ጨዋታውን በተሻለ የራስ መተማመን መቆጣጠር የቻሉት ቤንች ማጂ ቡናዎች ጨዋታውን እንደጨረሱት በማሰብ በተዘናጉበት ቅጽበት 9ዐ+1 ላይ አለኝታ ማርቆስ በቀኝ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት ሲያሻማ ያገኘው ወንዱ ፍሬው በግንባሩ በመግጨት ለራሱ እና ለክለቡ ሁለተኛውን ግብ ማስቆጠር ችሏል። ጨዋታውም 2 – 2 ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ቤንችማጂዎች በ 21 ነጥቦች በደረጃ መሪነታቸው ቢቀጥሉም የነጥብ ልዩነቱን ሊያሰፉ የሚችሉበትን ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

\"\"

ጅማ ላይ በምድብ \’ለ\’ በተደረገው ጨዋታ ደብረ ብርሃን ከተማ ኃይሌ እሸቱ በጭማሪ ደቂቃ ባስቆጠራት ብቸኛ ግብ ከምባታ ሺንሺቾን 1-0 ረቷል።

ሆሳዕና ላይ የዕለቱ ሦስተኛ ጨዋታ የሆነው በኦሜድላ እና በስልጤ ወራቤ መካከል የነበረው በመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ በስልጤ ወራቤ የበላይነት የታየበት እና በስልት እና በታክቲክ ተሽለው የተገኙበት አጋማሽ ሲሆን ጨዋታው በተጀመረ በ10ኛው ደቂቃ በማቲያስ ኤሊያስ አማካኝነት ስልጢ ወራቤዎች መሪ ማድረግ የቻለ ሲሆን የመጀመሪያ አጋማሽም ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ የስልጤ ወራቤ የበላይነት የቀጠለበት እና ከእረፍት እንደገቡ በሁለተኛው ደቂቃ በ47ኛው ደቂቃ ሙሰፊን ያሲን ግብ በማስቆጠር ስልጢ ወራቤን በሁለት ግብ ልዩነት እንዲመራ አድርጓል። ከሁለተኛው ግብ መቆጠር በኋላም የስልጢ ወራቤዎች የጨዋታ ፍላጎት የበለጠ የጨመረ ሲሆን ሶስተኛ ግብም ለማስቆጠር በተደጋጋሚ ኦሜድላዎች ግብ ክልል በመድረስ ጫና ሲፈጥሩ ተመልክተናል። ጨዋታውም በዚህ እንቅስቃሴ ቀጥሎ በ88ተኛው ደቂቃ የስልጢን ሶስተኛ ግብ ዳንኤል ታደሰ በማስቆጠር ስልጢ ወራቤ ኦሜድላን 3:0 መርታት ችሏል። የጨዋታውን ውጤት ተከትሎ ስልጤ ወራቤዎች ከተከታታይ የነጥብ መጣል ወደ ድል ተመልሰዋል።

የ10:00 ጨዋታዎች

ሰበታ ከተማ እና ጋሞ ጨንቻን ባገናኘው የምድብ ሀ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። በተሻለ የቁጥር ብልጫ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መግባት የቻሉት ሰበታዎች 22ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራ አድርገዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም በቀኝ መስመር የተሻማውን እና የጨንቻ ተከላካዮች በሥርዓት ያላራቁትን ኳስ ያገኘው ዮናስ ሰለሞን ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው መልሶበታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ በሁለቱም ቡድኖች አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳይደረግ አጋማሹ ተጠናቋል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነቱን ለመውሰድ ጨዋታው በመጠኑም ቢሆን ተሻሽሎ ሲቀጥል 77ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው የጋሞው ፍስሐ ቶማስ ከቀኙ የሜዳ ክፍል ላይ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው መልሶበታል። በመጨረሻ ደቂቃዎች ብልጫ መውሰድ የቻሉት ጋሞዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊያስቆጥሩ የሚችሉበትን ትልቅ አጋጣሚ አባክነዋል። ኳሱን ከግብጠባቂ ጋር በመጋጨት የራሱ አድርጎ ከተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ብቻውን ኳስ ይዞ የገባው ምትኩ በንዳ እጅግ እጅግ በወረደ እና በማይታመን መልኩ ክፍት ጎል ስቷል። ጨዋታውም ያለግብ ተጠናቋል።

በምድብ ለ ጅማ ላይ በተከወነው የመጨረሻ ጨዋታ ቂርቆስ ክፍለከተማ ነቀምት ከተማን በሄኖክ አወቀ ብቸኛ ግብ 1-0 ማሸነፍ ችሏል።

በምድብ ሐ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የነበረው የኮልፌ እና የየካ ፍልሚያ ብዙም በክስተት ያልታጀበ ጨዋታ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ብዙም እንቅስቃሴ የታየበት ቢሆንም ግን ወደ ግብ የሚደረጉ ሙከራዎች ላይ በሁለቱም ክለቦች ደካማ ነበር። እና አልፎ አልፎ በሁለቱም ክለቦች በኩል ከሚደረግ የግብ ሙከራ በቀር ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ አጀማመሩ የተሻለ እንቅስቃሴ እና የማሸነፍ ፍላጎት በሁለቱም ክለቦች በኩል ያየን ቢሆንም በ51 ደቂቃ የኮልፌ ክ/ከተማ ተጫዋች የሆነው ስንታየሁ በቀይ ካርድ ከሜዳ መሰናበቱን ተከትሎ ኮልፌ ክ/ከተማዎች ሙሉ ትኩረታቸውን ወደ ኋላ በማፈግፈግ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ሙከራ ያደረጉ ሲሆን የካ ክ/ከተማዎች ያገኙትን የአንድ ተጫዋች ብልጫ ለመጠቀም እና ግብ ለማስቆጠር ወደ ፊት ተጭነው ለመጫወት የሞከሩ ቢሆንም ምንም ግብ ሳያስቆጥሩ ኮልፌ ክ/ከተማዎችም ግብ ሳያስተናግዱ ጨዋታው ያለ ምንም ግብ በአቻ ውጤት ነጥብ ተጋርተው ወተዋል።