ቻን | የነገውን የዋልያዎቹ ጨዋታ በምን ማየት ይቻላል?

ነገ 10 ሰዓት ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ የሚያደርጉትን የቻን ጨዋታ በሀገራችን የቀጥታ ስርጭት የሚሰጠው ተቋም ማነው?

ጥሩ ዝግጅት የተደረገበት 7ኛው የቻን ውድድር ዛሬ ምሽት አልጄሪያ እና ሊቢያ በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ጅምሩን ያደርጋል። ጨዋታው 4 ሰዓት ከመጀመሩ በፊትም ከ3 ሰዓት ጀምሮ የመክፈቻ መርሐ-ግብር እንደ አዲስ እድሳት በተደረገለት ውቡ ኔልሰን ማንዴላ ስታዲየም ይከወናል። የውድድሩ የበላይ አካል ካፍ እና አዘጋጅ ኮሚቴው ዛሬ የሚጀመረው ፍልሚያ በጥሩ ሁኔታ እንዲከወን ስራዎችን ሲሰሩ የነበረ ሲሆን አልጄሪያ ለማይገኙ የስፖርት ቤተሰቦችም ውድድሩን በቴሌቪዥን በተሻለ ጥራት ለማድረስ ሲደክሙ ሰንብተዋል። በዚህም ካፍ በተሻለ ፕሮዳክሽን ውድድሩ በቀጥታ እንዲተላለፍ ዝግጅቱን የጨረሰ ሲሆን የካፍ ቲቪ ከአልጄሪያው ኢፒ ቲቪ ጋር በጣምራ የቀረፃ እና የስርጭቱን ስራ እንደሚሰሩ ተመላክቷል።

\"\"

ከዚህ ቀደም ውድድሩ ከ10-14 ባሉ ካሜራዎች ሲቀረፅ የነበረ ቢሆንም አሁን ካፍ ውድድሩ በ24 ካሜራዎች እንደሚቀረፅ እና የዛሬው የመክፈቻ ጨዋታም ቢያንስ 66 ሀገሮች ጋር ተደራሽ እንደሚሆን ጠቁሟል። በአፍሪካ እግርኳስ ልምድ ያላቸው ተንታኞችም በቀጥታ ስርጭት ኮመንተሪው እና የትንተና ወቅት እንደሚሳተፉ ተገልጿል።

በርካታ የሀገራችን የስፖርት ቤተሰቦች ውድድሩ በቀጥታ የሚተላለፍበትን አማራጭ ሲጠይቁ የነበረ ሲሆን በኢትዮጵያ ፍቃድ ያለው አስተላላፊ ተቋም የሆነው ሱፐር ስፖርት ጨዋታዎችን እንደሚያስተላልፍ አውቀናል። በዚህም የዋልያዎቹን ፍልሚያዎች በልዩ ቻነል (240) እንዲሁም ሌሎች የውድድሩን ሁሉንም ጨዋታዎች በፉትቦል ኤች ዲ ቻነል (222) የሀገራችን የስፖርት ቤተሰቦች እንዲከታተሉ ተገልጿል። ከሱፐር ስፖርት በተጨማሪ ይህንን ጥንክር እያዘጋጀንበት ባለበት ጊዜ ማረጋገጫ ባናገኝም ኢትዮጵያ ቴሌቪዥንም ጨዋታዎችን እንደሚያስተላልፍ እንደሚጠበቅ ሰምተናል።

\"\"