ቻን | ስለዋልያዎቹ ተጋጣሚ ሞዛምቢክ…

ነገ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የሚገጥመው የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድንን የተመለከ ጥንቅር እንደሚከተለው አሰናድተናል።

የኮሳፋ ተወካይ የሆነችው ሞዛምቢክ 2014 ላይ በደቡብ አፍሪካ አዘጋጅነት በተከናወነው ሦስተኛው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒየንሺፕ (ቻን) ውድድር ላይ ተሳትፋ ከምድብ የተሰናበተች ሲሆን ዛሬ በሚጀምረው 7ኛው ውድድር ላይ ሦስት የመድረኩ ፍልሚያዎች ካለፉዋት በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ለመካፈል የማጣሪያ ፍልሚያዎቿን በበላይነት ፈፅማ የአልጄሪያ ትኬቷን ቆርጣለች። በማጣሪያው ሞዛምቢክ ጉዞዋን የጀመረችው ከዛምቢያ ጋር በመጫወት ነበር። በመጀመሪያ ጨዋታዋ ማፑቶ ላይ ያለ ግብ አቻ ከተለያየች በኋላ ከሜዳዋ ውጪ ሉሳካ ላይ ላው ኪንግ ባስቆጠረው ብቸኛ ጎል አሸንፋ ወደ ሁለተኛው ማጣሪያ አልፋለች። በሁለተኛው እና በመጨረሻው የማጣሪያ ጨዋታ ከማላዊ ጋር የተደለደለችው ሞዛምቢክ ሁለቱንም ጨዋታዎች አላሸነፈችም አልተሸነፈችም ፤ ነገርግን ሊሎንጊዌ ላይ ኔልሰን ዲቭራሶን ባስቆጠረው ጎል አንድ አቻ ተለያይታ ወደ ሜዳዋ ከተመለሰች በኋላ በርካታ ደጋፊዎች በታደሙበት በዚምፔቶ ስታዲየም ጨዋታ ያለ ግብ ተለያይታ ከሜዳ ውጪ ባስቆጠረ በሚለው ህግ በአልጄሪያው ውድድር ተሳታፊ መሆኗን አረጋግጣለች።

ከዚህ ቀደም በተሳተፈችበት በደቡብ አፍሪካው ውድድር ከናይጄሪያ፣ ማሊ እና አዘጋጇ ደቡብ አፍሪካ ጋር ተደልድላ የነበረችው ሞዛምቢክ በሦስቱም የምድብ ጨዋታዎች ቀድማ ግብ ብታስቆጥርም (በሁለተኛው የናይጄሪያ ጨዋታ አምበሉ ዳሪዮ ካሀን ያስቆጠረው የቅጣት ምት ጎል የውድድሩ ድንቅ ጎል ከተባሉት ውስጥ ይገኝ ነበር) የኋላ ኋላ ግን ግብ ተቆጥሮባት እጅ ሰጥታለች።

\"\"

በዘንድሮው ውድድር ከሁሉም ተሳታፊ ብሔራዊ ቡድኖች ቀድማ አልጄሪያ የደረሰችው ሞዛምቢክ በ57 ዓመቱ አሠልጣኝ ቼኪኒዮ ኮንዴ የምትመራ ይሆናል። የቀድሞ የተጨበጨበላቸው አጥቂ የነበሩት ኮንዴ በተጫዋችነት ዘመናቸው ሀገራቸውን ሦስት ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ መድረክ (1986 – ግብፅ፣ 1996 – ደቡብ አፍሪካ እና 1998 – ቡርኪና ፋሶ) ወክለው ተጫውተዋል። እግርኳስን መጫወት ካቆሙ በኋላ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የአሠልጣኝነት ህይወታቸውን የጀመሩት 2005 ላይ ወደ ፖርቹጋል ከማምራታቸው በፊት በሞዛምቢክ ተጫውተውበት በነበረው ማክስኩዊን ክለብ ነው። በዚህ የአሠልጣኝነት ህይወታቸው ሞካምቦላ ተብሎ የሚጠራውን የሞዛምቢክ ናሽናል ሊግ ሁለት ጊዜ ማሸነፍ ችለዋል። 2021 ጥቅምት ወር ላይ ደግሞ ፖርቱጋላዊውን አሠልጣኝ ሆራሲዮ ጎንካልቬስን በመተካት በተጫዋችነት ያገለገሉትን ብሔራዊ ቡድን በአሠልጣኝ ለማገልገል ሹመት ተቀብለዋል።

ኮንዴ መጀመሪያ ቡድኑን በአሠልጣኝነት እየመሩ በቀረቡበት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ በኮትዲቯር ሦስት ለምንም ተረተው ነበር። ከቀናት በኋላ ግን በቡድኑ አምበል ብቸኛ ጎል ማላዊን አንድ ለምንም አሸንፈው በአሠልጣኝነት የመጀመሪያ ድላቸውን አግኝተዋል። ሴኔጋል፣ ቤኒን እና ሩዋንዳ በተደለደሉበት የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያም አራት ነጥብ ይዘው በአሁኑ ሰዓት ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠው ብሔራዊ ቡድኑን ለ5ኛ ጊዜ በአፍሪካ ዋንጫ እንዲካፈል የሚያስችል የተሻለ ቦታን ይዘዋል።

አሠልጣኙ የሀገሪቱ ሊግ ታኅሣሥ 4 ካለቀ ከ12 ቀናት በኋላ ብሔራዊ ቡድኑ ተሰባስቦ ልምምድ እንዲጀመር እና የተጫዋቾቹን የአካል ብቃት ለመጠበቅ ስራዎች ቀድመው እንዲሰሩ ፍላጎት የነበራቸው ቢሆንም ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አዎንታዊ ምላች ስላልሰጣቸው እቅዳቸው ሊፈፀም አልቻለም። ወደ አልጄሪያ ከመጓዛቸው ከሦስት ቀናት በፊት ተሰባስበው ታኅሣሥ 27 ወደ ውድድሩ አዘጋጅ ሀገር በመሄድ ግን እሳቸው ካሰቡበት ቀን ረፈድ ብሎም ቢሆን ዝግጅታቸውን መከወን ይዘዋል። በዚህም በዝግጅት ወቅት የሀገሪቱ ብሔራዊ የእግርኳስ ፌዴሬሽን ትብብር ባለማድረጉ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቅሬታቸውን ሲገልፁ ተሰምቷል። የሆነው ሆኖ ግን አልጄሪያ ከገቡ በኋላ ከሁለት የሀገሪቱ ክለቦች ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርገው ሲሸነፉ ከጋና ጋር ያደረጉትን የመጨረሻ ጨዋታ ደግሞ አንድ ለምንም እየመሩ በ72ኛው ደቂቃ ከዳኛነት ጋር ተያይዞ ቅሬታ ገብቷቸው አቋርጠው ወጥተዋል።

\"\"

\”ማምባስ\” በሚል ቅፅል ስም የሚጠሩት ሞዛምቢኮች ለዚህ ውድድር 25 ተጫዋቾችን በመያዝ በሜርኩሪ ሆቴል ማረፊያቸውን አድርገዋል። በስብስቡ ውስጥ 3 የግብ ዘቦች፣ 8 ተከላካዮች፣ 7 አማካዮች እና 7 አጥቂዎች የሚገኙ ሲሆን በብዙ የሀገሪቱ የብዙሀን መገናኛዎች በውድድሩ ደምቆ ይወጣል ተብሎ የተገመተው ተጫዋች 10 ቁጥር መለያ የሚለብሰው አይዛክ ዲ ካርቫልሆ ነው። የ33 ዓመቱ ተጫዋች በ2014ቱ የብሔራዊ ቡድኑ የቻን ተሳትፎ ውስጥ ከነበሩት ሳዳም ጉዋምቤ እና ፍራንሲስኮ ሙቼንጋ ጋር በመሆን በአሁኑ ስብስብ የሚገኝ ነው። አጥቂው በተጠናቀቀው የሞዛምቢክ ሊግ በ10 ግቦች ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ የጨረሰ ሲሆን ባሳየው ምርጥ ብቃትም 2019 ላይ በአንበልነት የሊጉን ዋንጫ ወዳነሳበት የቀድሞ ክለቡ ኮስታ ዱ ሶል ተመልሷል።

ከአይዛክ በተጨማሪ ብሔራዊ ቡድኑ የቻን ትኬቷን እንድታገኝ ያስቻለች ጎል ማላዊ ላይ ያስቆጠረው 7 ቁጥር መለያ የሚለብሰው ኔልሰን ዲቭራሶን በውድድሩ ይጠበቃል። የቀኝ መስመር ተጫዋቹ ኔልሰን ክለቡ የሊጉን ዋንጫ እንዲያገኝም በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ድንቅ አበርክቶ ሲሰጥ ነበር።

ሞዛምቢክ ነገ ኢትዮጵያን 10 ሰዓት የምትገጥም ሲሆን ጥር 9 ሊቢያን ጥር 13 ደግሞ አልጄሪያን የምትገጥም ይሆናል።

ምሽት ላይ ደግሞ ከሞዛምቢካዊው የእግርኳስ ጋዜጠኛ እና ዳታ ኢንኮደር ኤሊሲዮ ጆስ ቡዋንሀ ጋር ስለብሔራዊ ቡድኑ እና ስለነገው ጨዋታ ያደረግነው ቆይታ የምናቀርብ ይሆናል።