ቻን | የዋልያዎቹ ተጋጣሚ አሠልጣኝ እና አምበል ከጨዋታው በፊት ምን አሉ?

👉 \”አሁን ላይ ያለን እቅድ የነገውን የኢትዮጵያ ጨዋታ ማሸነፍ ነው\” ቼኪኒዮ ኮንዴ

👉 \”በነገው ጨዋታ ጥሩ ተጫውተን ለሞዛምቢክ ህዝብ ደስታ እንሰጣለን\” ሳዳን ጉዋምቤ

ከ2022 ወደ 2023 የተዘዋወረው 7ኛው የቻን ውድድር በዛሬው ዕለት እንደሚጀመር ይታወቃል። ሀገራችን ኢትዮጵያም በነገው ዕለት ከሞዛምቢክ ጋር የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታዋን የምታደርግ ይሆናል። ከጨዋታው አንድ ቀን በፊት የቡድኖቹ አሠልጣኞች እና አምበሎች ቀትር ላይ አልጄሪያ ለሚገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት መግለጫ ሰጥተዋል። በኢትዮጵያ በኩል የተነሳውን የቅድመ ጨዋታ ሀሳብ ከደቂቃዎች በፊት ያቀረብን ሲሆን አሁን ደግሞ የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ቼኪኒዮ ኮንዴ እና አምበሉ ሳዳን ጉዋምቤ የሰጡትን ሀሳብ ይዘን ቀርበናል።

\"\"

በቅድሚያ ዋና አሠልጣኙ \”በመጀመሪያ አልጄሪያ በመገኘታችን ደስታ ተሰምቶናል ፤ ከ9 ዓመታት በኋላም ብሔራዊ ቡድኑ ወደዚህ መድረክ በመመለሱ ደስ ተሰኝተናል። ወደዝግጅታችን ስመጣ በደንብ ተዘጋጅተናል። የምድቡ የመጀመሪያ ጨዋታ ከየትኛውም ጨዋታ በላይ ወሳኝ ነው።\” በማለት ሀሳባቸውን በስፍራው ለተገኙ ጋዜጠኞች አጋርተዋል። የቡድኑ አምበል ሳዳን ጉዋምቤም እንደ ዋናው አሠልጣኝ እዚህ በመገኘቱ የተሰማውን ደስታ ጠቁሞ በነገው ጨዋታ ሁሉም ተጫዋቾች ያላቸውን ሁሉ ለመስጠት እንደተዘጋጁ ተናግሯል።

በውድድሩ ስላላቸው እቅድ የተጠየቁት አሠልጣኝ ቼኪኒዮ ኮንዴ አሁን ላይ ያላቸው እቅድ ነገ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያደርጉትን የመጀመሪያ ጨዋታ ማሸነፍ እንደሆነ ገልፀዋል። ከዝግጅት ጋር ተያይዞ ደግሞ የሀገራቸው ሊግ በማለቁ እንደ ቅድመ ዝግጅት አይነት ልምምድ አልጄሪያ ላይ እንዳደረጉ ጠቁመዋል። በምላሹ ላይ ተጨማሪ ሀሳብ የሰጠው አምበሉ ሳዳን ጉዋምቤ ደግሞ አልጄሪያ ላይ ጥሩ ዝግጅት እንዳደረጉ ገልፆ በልምምድ ላይ የሰሩትን ነገ ሜዳ ላይ እንደሚያሳዩ ተናግሯል። አክሎም \”በነገው ጨዋታ ጥሩ ተጫውተን ለሞዛምቢክ ህዝብ ደስታ እንሰጣለን\” ሲል ተደምጧል።

\"\"

በመጨረሻም ስለሚገኙበት ምድብ ሀሳብ የሰጡት የ57 ዓመቱ አሠልጣኝ ኮንዴ የውድድሩ አዘጋጅ ሀገር አልጄሪያ የተሻለ ግምት እንደሚሰጣት አምነው ሁሉንም ተጋጣሚዎቻቸውን እንደሚያከብሩ እና አሁን ዋናው ትኩረታቸው የነገው የኢትዮጵያ ጨዋታ እንደሆነ በአፅንኦት ተናግረዋል። ጨምረውም ቡድናቸው በምድቡ ግምት ባይሰጠውም ከአዘጋጇ ሀገር ቀጥለው ሁለተኛ ሆኖ ለማለፍ ያላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ አመላክተዋል።