ቻን | ከነገው ጨዋታ በፊት ከሞዛምቢካዊው ጋዜጠኛ ኤሊሲዮ ጆስ ቡዋንሀ ጋር የተደረገ ቆይታ…

👉 \”እጅግ ፈጣን እና ከርቀት አክርረው ኳሶችን ማስቆጠር የሚችሉት አስደናቂዎቹ የቡድኑ የመስመር ተጫዋቾች ልዩነት ፈጣሪዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል\”

👉 \”አሁን ላይ ብሔራዊ ቡድኑን እያለጠኑ የሚገኙት አሰልጣኝ ቼኪኒዮ ኮንዴ የገነቡት ቡድኑ ይበልጥ ተለዋዋጭ ባህሪን የተላበሰ ነው\”

👉 \”አሁን ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ካለፉት 5 እና 6 አመታት አንፃር በብዙ መልኩ ተሻሽሏል ፤ የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድንም ለኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን የሚሰጠው ግምት ከቀደመው ጊዜ አንፃር በጣም የተሻለ ነው\”


👉 \”እውነቱን ለመናገር የሞዛምቢክ ሊግ ያን ያህል ጠንካራ የሚባል አይደለም ፤ ሊጉ እምብዛም ፉክክሮች ያሉበት አይደለም። ደካማ ስለመሆኑ በርከት ያሉ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል\”

በኮቪድ-19 ምክንያት ከ2022 ወደ 2023 የተዘዋወረው 7ኛው የአፍሪካ ሀገራት ቻምፒየንሺፕ ውድድር ከሁለት ሰዓታት በኋላ (4 ሰዓት) አልጄሪያ እና ሊቢያ በሚያደርጉት ጨዋታ ጅማሮውን ያደርጋል። በዚሁ ምድብ አንድ የሚገኙት ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ ደግሞ ነገ 10 ሰዓት በኔልሰን ማንዴላ ሥም በተሰየመው ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ድረ-ገፃችን ሶከር ኢትዮጵያ ተጋጣሚዎቻችንን እንዲሁም አጠቃላይ ውድድሩን የተመለከቱ ተከታታይ መረጃዎችን እያቀረበች የምትገኝ ሲሆን አሁን ደግሞ የነገው ተጋጣሚያችን የሞዛምቢክ ሀገር የስፖርት ጋዜጠኛ እና ዳታ ኢንኮደር የሆነውን ኤሊሲዮ ጆስ ቡዋንሀ አግኝታ አጠቃላይ ተጋጣሚያችንን የተመለከቱ ጥያቄዎች አቅርባ ተከታዩን ቆይታ ይዛ ቀርባለች።

\"\"

ስለሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን ቅድመ ዝግጅት…?

\”ለቻን የአፍሪካ ዋንጫ የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን አጠቃላይ የዝግጅት ሂደት ብዙ ክፍተቶች የነበሩበት ነበር። በተለይ አስቀድሞ አሰልጣኙ ለፌዴሬሽኑ ካቀረበው ጥያቄ አንፃር በታሰበው መልኩ የሄደ አልነበረም። አሰልጣኙ ለውድድሩ ዝግጅት ይረዳው ዘንድ ለሀገሪቱ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ቡድኑ ቀደም ብሎ ተሰባስቦ የሚቆይበትን ስፍራ ፣ የልምምድ ሜዳዎች እና ሌሎች ተያያዥ የስፖርት መሰረተ ልማት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያቀረባቸው ቅድመ ሁኔታዎች የነበሩ ቢሆንም በፌዴሬሽኑ በኩል የቀረቡትን ሁኔታዎችን መሟላት ሳይችላ ቀርቷል። ይህን ተከትሎ አሰልጣኙ በአስገዳጅ ሁኔታ እንደነገሩ ቡድኑን ለማዘጋጀት የተገደደበት ሁኔታ ተፈጥሯል። አሰልጣኙ በፈለጉት ቀን ባይሆንም ከታሰበው ቀን ትንሽ ዘግይቶ ወደ ውድድሩ ስፍራ አልጄሪያ መጥቶ ዝግጅቱን ከውኗል።\”

በስብስቡ መካተት እየተገባቸው ያልተመረጡ ተጫዋቾች ይኖሩ ይሆን?

\”በእኔ እምነት የብሔራዊ ቡድን ጥሪ እየተገባው ያልተመረጠ ተጫዋቾች አለ ብዬ አላምንም። አሰልጣኙ ወቅታዊ ብቃት እና ሊከተል የሚፈልገውን የጨዋታ መንገድ ታሳቢ በማድረግ ለተጫዋቾች ጥሪ አቅርቧል። በእኔ እምነት ጥሪ ያልተደረገላቸው ተጫዋቾች ስብስቡ ውስጥ ለመካተት የሚያበቃ በቂ እንቅስቃሴ በተለይም በሊጉ የመጨረሻ ሳምንታት ስላላሳዩ ነው ብዬ ነው የምወስደው።\”

የብሔራዊ ብድኑ ጠንካራ እና ደካማ ጎን ምንድን ነው?

\”ምናልባት እንደ ድክመት ማንሳት ከቻልን የመከላከል መስመሩ ላይ ያሉ ተጫዋቾች በተለይ ከኳስ ጋር ያላቸው አፈፃፀም ደካማ መሆኑ ትልቁ የቡድኑ ድክመት ይመስለኛል። በተቃራኒው እጅግ ፈጣን እና ከርቀት አክርረው ኳሶችን ማስቆጠር የሚችሉት አስደናቂዎቹ የቡድኑ የመስመር ተጫዋቾች ልዩነት ፈጣሪዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል። በተለይም በማጥቂያው ሲሶ ላይ ክፍተቶችን የሚያገኙ ከሆነ ብዙ ጉዳት ማድረስ ይችላሉ ብዬ አምናለሁ። በግለሰብ ደረጃ መመልከት ካስፈለገ ፊት መስመር ላይ የሚጫወተው ላው ኪንግ ብሔራዊ ቡድን ወደ ቻን አፍሪካ ዋንጫ እንዲያልፍ ትልቅ ሚናን ተወጥቷል። በማጣሪያው እጅግ ወሳኝ በሆኑ ጨዋታዎች በተለይም ዛምቢያን ጥለው ሲያልፉ እጅግ ወሳኝ የነበረችውን ግብ በስሙ ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን ብሔራዊ ቡድኑ ዝቅተኛ ግምት አግኝቶ በጀመረበት የዛምቢያው ጨዋታ ዛምቢያን የሚያክል ቡድን በሜዳው መርታት መቻላቸው በራሱ የቡድኑን የራስ መተማመን ወደ ከፍተኛ ምዕራፍ በማሸጋገር ረገድ ትልቅ ሚናን ተወጥቷል። በአፍሪካ ዋንጫው ላይም ለሞዛምቢክ የተለየ ነገር ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።\”

የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን በውድድሩ ምን ያህል ርቀት የመጓዝ አቅም አለው ብለህ ታስባለህ…?

\”እንደሚታወቀው ወደዚህ ውድድር የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን ሲመጣ ዝቅተኛ ግምትን አግኝቶ ነው። ቡድኑ ሩቅ እንዲጓዝ በብዙሃኑ ዘንድ ፍላጎቶች ቢኖሩም መሬት ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ከምድብ ማለፍ በራሱ ለሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን እንደ ትልቅ ስኬት ነው የሚቆጠረው።\”

ስለሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ መንገድ…?

\”አሁን ላይ ብሔራዊ ቡድኑን እያለጠኑ የሚገኙት አሰልጣኝ ቼኪኒዮ ኮንዴ የገነቡት ቡድኑ ይበልጥ ተለዋዋጭ ባህሪን የተላበሰ ነው። ቡድኑ በጨዋታዎች እምብዛም ኳስን የመቆጣጠር ፍላጎት የሌለው ሲሆን በመሰረታዊነት ለተጋጣሚ ኳሱን በመፍቀድ በመልሶ ማጥቃት መጫወትን ምርጫው ያደረገ ቡድን ነው። ሌላው ቡድኑ በጨዋታዎች ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር የሚቸገር መሆኑን ተከትሎ የሚገኙትን ውስን ዕድሎች ወደ ግብ መቀየር ላይ ሰፊ ትኩረት ያደርጋሉ። በአሁኑ ስብስብ ውስጥ ከመስመር እየተነሱ አደጋ መፍጠር የሚችሉት ፈጣን የመስመር ተጫዋቾች የቡድኑ ቁልፍ ናቸው።\”

የሀገራችሁን ሊግ በጥቂቱ አስተዋውቀን እስቲ…?

\”እውነቱን ለመናገር የሞዛምቢክ ሊግ ያን ያህል ጠንካራ የሚባል አይደለም ፤ ሊጉ እምብዛም ፉክክሮች ያሉበት አይደለም። ደካማ ስለመሆኑ በርከት ያሉ ምክንያቶችን ማቅረብ ይቻላል። በዋነኝነት ግን የኮቪድ ወረርሽኝ በሀገሪቱ እግር ኳስ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ቀዳሚ ምክንያት ነው። ለምሳሌ ድህረ ኮቪድ በሀገሪቱ እግር ኳስ ውስጥ በተከሰተው ከፍተኛ የፋይናንስ ቀውስ መነሻነት በሊጉ የሚካፈሉ ቡድኖች ቁጥር ከ14 ወደ 12 እንዲቀንስ ተደርጓል። በአጠቃላይ ኮቪድ በሞዛምቢክ ሊግ ሆነ በሀገሪቱ እግር ኳስ መዋቅር ላይ እያሳደረ ያለው ተፅዕኖ እጅግ ከባድ ነው።\”

\"\"

በጋናው የአቋም መፈተሻ ጨዋታ የተፈጠረው ነገር ምንድን ነው…?

\”በመጨረሻው የጋና የወዳጅነት ጨዋታ ላይ ስለተፈጠረው ጉዳይ ጥርት ያለ መረጃ የለኝም። እንደሰማሁት ከሆነ ግን በጨዋታው በነበረው ዳኝነት እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ ላይ የተሰጠባቸው የፍፁም ቅጣት ምት ተገቢ አይደለም በሚል የሞዛምቢክ ተጫዋቾች ሜዳው ላይ የተፈጠረው ሁኔታ ምቹ አይደለም በሚል ሜዳውን ለቀው ወጥተዋል።\”

ሰለ ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ቡድን የሞዛምቢክ ሚዲያ ያለው ምስል ምን ይመስላል?

\”አሁን ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ካለፉት አምስት ስድስት አመታት አንፃር በብዙ መልኩ ተሻሽሏል ፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ በአውንታዊ ለውጥ ውስጥ ይገኛል። የሞዛምቢክ ብሔራዊ ቡድንም አሁን ላይ ለኢትዮጵያን ብሔራዊ ቡድን የሚሰጠው ግምት ከቀደመው ጊዜ አንፃር በጣም የተሻለ ነው ፤ እንደ ብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ ክብር ይሰጣሉ። አሰልጣኙም ከጨዋታው አስቀድመው ለሀገራችን ሚዲያዎች እንደተናገሩት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጠንካራ ፈተና እንደሚገጥማቸው ይጠብቃሉ።\”

ሞዛምቢካዊያን ከነገው ጨዋታ ምን ይጠብቃሉ?

\”ክብር ከመስጠቱ ባለፈ ግን በሞዛምቢካውያን ዘንድ ቡድናቸው ይህን ጨዋታ ማሸነፍ እንደሚችል ከፍተኛ እምነት አለ ፤ ምክንያቱም በተጫዋቾች የጥራት ደረጃ ረገድ በሁለቱ ቡድኖች በኩል ይህ ነው የሚባል ልዮነት የለም። በዚህም መነሻነት ሞዛምቢክ ኢትዮጵያን በመጀመሪያው ጨዋታ በማሸነፍ በተሻለ ተነሳሽነት ወደ ቀጣይ ጨዋታዎች ታመራለች የሚል እምነት አለ።\”