ከፍተኛ ሊግ | የ9ኛ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ ስምንት ጨዋታዎችን አስተናግዶ ዘጠነኛው ሳምንት ተጠናቋል።

በቶማስ ቦጋለ እና ጫላ አቤ

የ04፡00 ጨዋታዎች

በምድብ \’ሀ\’ ባህር ዳር ላይ ወልዲያን ከቡታጅራ ባገናኘው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢታይበትም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ግን ወልዲያዎች የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ጨዋታው በጀመረ በሴኮንዶች ውስጥም ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። በፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ወንድማገኝ ሌራ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ፀጋ ማቲዎስ በግንባሩ ሙሉ ለሙሉ ሳያገኘው ቀርቶ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ውስጥ በጥሩ ቅብብል ለመውጣት የሚሞክሩት ግን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ የተቸገሩት ቡታጅራዎች የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም። ይባስ ብሎም 31ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። አምበሉ ሙሉቀን ደሳለኝ ከረጅም ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ሲያሻማ ያገኘው ቢንያም ጥዑመልሳን በግራ እግሩ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡ የቀኝ ቋሚ መልሶበታል።

\"\"

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው በብርቱ ፉክክር ታጅቦ ሲቀጥል በመጀመሪያ ደቂቃዎች ቡታጅራዎች ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሲችሉ 49ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድ ሁሴን ከግራ መስመር ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ ያገኘው ርሂሙ ዑስማን በግንባሩ በመግጨት ቢሞክርም የግቡ የላዩ አግዳሚ መልሶበታል። ግብ ለማስቆጠር በመጓጓት ባልተረጋጋ ሁኔታ ወደፊት ሲሄዱ ኳሱ የሚቋረጥባቸው ወልዲያዎች 67ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። 59ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ቢንያም ላንቃሞ ወደ ቀኙ የሜደ ክፍል ካጋደለ ቦታ ላይ ከተጋጣሚ የሳጥን አጠገብ እጅግ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል።

የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ወደ ተሻለ የጨዋታ ስሜት የገቡት ቡታጅራዎች 79ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሄኖክ መርሹ ከግራ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው ዮናስ ወልዴ ኳሱ በአየር ላይ እንዳለ በግራ እግሩ መትቶት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡን የግራ ቋሚ ታክኮ ለጥቂት ወጥቶበታል። ጨዋታውም በወልዲያ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ወልዲያ ከተማ ነጥቡን 18 በማድረስ ከመሪው ቤንች ማጂ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሦስት ዝቅ አድርጓል።

\"\"

ጅማ ላይ በምድብ \’ለ\’ ቀዳሚ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ ወደ ሁለተኛ ደረጃ የመጣበትን ድል አስመዝግቧል። ተጋጣሚው ይርጋጨፌ ቡና በኤፍሬም ቶማስ ጎል ቀዳሚ ቢሆንም የመዲናዋ ክለብ ሙሉቀን ታሪኩ በጨዋታ ሮቤል ግርማ በፍፁም ቅጣት ምት ማስቆጠሯቸው ግቦች 2-1 ማሸነፍ ችሏል።

የ08፡00 ጨዋታዎች

ባቱ ከተማን ከ አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ያገናነኘው የምድብ \’ሀ\’ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በብርቱ ፉክክር እና በማራኪ የኳስ ቅብብሎች የታጀበ ቢሆንም ቀስ በቀስ ግን በተደጋጋሚ በሚከሰቱ አካላዊ ንክኪዎች እየደበዘዘ መጥቷል። በመጀመሪያው አጋማሽም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል አቃቂዎች የተሻሉ የነበር ሲሆን ባቱዎች በአሸብር ውሮ የቅጣት ምት አቃቂ ቃሊቲዎች ደግሞ በኪሩቤል ይጥና የግንባር ኳስ እና በሊዮናርዶ ሰለሞን ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።

ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ እጅግ ተሻሽለው የቀረቡት አቃቂዎች 58ኛው ደቂቃ ላይ ሊዮናርዶ ሰለሞን ባስቆጠራት ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። 64ኛው ደቂቃ ላይም ዳዊት ቹቹ በኃይሉ ወገኔ ላይ በሠራው ጥፋት የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት ኪሩቤል ይጥና ሲመታ ግብጠባቂው አብርሃም ከተማ መልሶበት ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። በተደጋጋሚ ረፍት የለሽ እንቅስቃሴ በማድረግ ጨዋታውን የተቆጣጠሩት አቃቂዎች 72ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። በኃይሉ ወገኔ ወደ ሳጥን ይዞት ገብቶ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው እሸቱ ጌታሁን ማስቆጠር ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ይበልጥ የተንቀሳቀሱት አሳዎቹ 87ኛው ደቂቃ ላይ ሳላዲን ሙሰማ ከማዕዘን ተሻምቶ ሲመለስ ባገኘው ኳስ ካደረገው ሙከራ ውጪ ፈታኝ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረው ጨዋታውም በአቃቂ ቃሊቲ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
\"\"

ጅማ ላይ በተደረገው የከሰዓት ጨዋታ
ቦዲቲ ከተማ እንጅባራ ከተማን 2-1 ረቷል። ናትናኤል ዳንኤል ሁለቱን የቦዲቲ ግቦችን ሲያስቆጥር የእንጅባራን ብቸኛ ግብ አበበ ታደሰ ከመረብ አገናኝቷል።

ሆሳዕና ላይ የዕለቱ የምድብ ሐ የመጀመሪያ የሆነው የጅማ አባ ጅፋር እና ሮቤ ከተማ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ እንቅሰቃሴ የታየበትና በአብዛኛው የሮቤ ከተማ የበላይነት የታየበት ነበር። በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በግብ ሙከራም የተሻሉት ሮቤ ከተማዎች የፈጠሩትን የግብ ዕድል ወደ ግብነት መቀየር የተሳናቸው ሲሆን በአንፃሩ ጅማ አባ ጅፋሮች በኳስ ቁጥጥርም ሆነ በግብ ሙከራም ደክመው የታዩበት ነበር። አባ ጅፋሮች አፈግፍገው በመጫወት ግብም ሳያስቆጥሩ እና ግብ ሳያስተናግዱ ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት ችለዋል።
\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማ አባ ጅፋሮች በመጀመሪያው አጋማሽ የነበረባቸውን ችግር በመቅረፍ እና የተጋጣሚያቸውን አጨዋወት በመረዳት ተሽለው የተገኙበት አጋማሽ ሲሆን ግብም ለማስቆጠር የበለጠ ተጭነው ሲጫወቱ ተመልክተናል። በ69ኛው ደቂቃ ጅማ አባ ጅፋሮች በጫና የፈጠሩትን የግብ ዕድል ሱራፌል ፍቃዱ በማስቆጠር ቡድኑን መሪ ማድረግ ችሏል። ጨዋታው በእንደዚህ ዓይነት አጨዋወት በመቀጠል ሮቤ ከተማዎችም የሚያገኙትን ኳስ በመልሶ ማጥቃት ሂደት ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል በመድረስ ሙከራዎችን ሲያደርጉ የነበረ ሲሆን የጨዋታው መደበኛ ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጠው ተጨማሪ ደቂቃ በያሬድ መኮንን አማካኝነት ሮቤ ከተማዎች ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።

\"\"

የ10፡00 ጨዋታዎች

ባህር ዳር ላይ በበርካታ ተመልካቾች ታጅቦ ለጨዋታ ምቹ በሆነ የዓየር ሁኔታ በተደረገው የምድብ \’ሀ\’ የዘጠነኛ ሣምንት የመጨረሻ የንግድ ባንክ እና የሀላባ ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ብርቱ ፉክክር የታየበት ሲሆን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመድረሱ በኩል ሀላባዎች የተሻሉ ነበሩ። የመጀመሪያውን ፈታኝ ሙከራም 20ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ሙሉቀን ተሾመ ከቅጣት ምት ግሩም ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው አስወጥቶበታል። በጥሩ ቅብብሎች በታገዘ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የሚፈልጉት ግን ከተጋጣሚ የግብ ክልል ከደረሱ በኋላ በችኮላ ኳሶችን የሚያባክኑት ንግድ ባንኮች 42ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው በረከት ግዛቸው በግሩም ዕይታ አመቻችቶ ባቀበለው ኳስ የግብጠባቂውን መውጣት የተመለከተው አቤል ማሙሽ ከፍ አድርጎ በመምታት በጥሩ አጨራረስ በማስቆጠር ክለቡ መርቶ ወደ ዕረፍት እንዲያመራ ማድረግ ችሏል።
\"\"

ጨዋታው ከዕረፍት መልስ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል በሁለቱም በኩል በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነቱን ለመውሰድ ብርቱ ፉክክር ቢያስተናግድም የጠሩ የግብ ዕድሎች ግን ያልተፈጠሩበት ነበር። በበርበሬዎቹ በኩል 55ኛው ደቂቃ ላይ አቡሽ ደርቤ ከቅጣት ምት የሞከረውና የላዩን አግዳሚ ታክኮ የወጣው ኳስ በንግድ ባንኮች በኩል በመጨረሻ ደቂቃዎች ዳግማዊ ዓባይ ከረጅም ርቀት ያደረገው ሙከራ ብቻ ተጠቃሽ ናቸው። ጨዋታውም በንግድ ባንክ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥቡን 20 በማድረስ ከመሪው ቤንች ማጂ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ አድርጎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ጅማ ላይ በተደረገው የምድብ ለ የመጨረሻ ጨዋታ ከፍ ቡና በይበልጣል አደመ ብቸኛ ጎል ጅንካ ከተማን 1-0 መርታት ችሏል።

የምድብ ሐ የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በነገሌ አርሲ እና ገላን ከተማ መካከል ተደርጓል። የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ እልህ የበዛበት እና አልሸነፍ ባይነት የታየበት ነበር። በሁለቱም በድኖች ከፍተኛ የሆነ የማሸነፍ ስሜት የተመለከትንበት በተጨማሪም ውበት ያለው እግር ኳስ በሁለቱም በኩል የተመለከትንበት እና ቶሎ ቶሎ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ሲደርሱ የተመለከትንበት ሆኗል። በ24ኛው ደቂቃ ገላን ከተማዎች ያደረጉትን የግብ ሙከራ በያሬድ ወንድማገኝ አማካኝነት ግብ በማስቆጠር መሪ መሆን የቻሉ ሲሆን በ39ኛው ደቂቃ ሜዳ ውስጥ በተፈጠረ ግጭት ከነገሌ አርሲዎችም ከገላን ከተማዎችም አንድ አንድ ተጫዋቾች ከሜዳ በቀይ ካርድ መወገድ ችለዋል። ተጫዋቾቹም ምስጋና አንጋሳ እና ቱፋን ተሽቴ ሲሆኑ ሁለቱም ቡድኖች በጎዶሎ ተጫዋች እንዲቀጥሉ ተገደዋል። የመጀመሪያው አጋማሽም በገላን ከተማ መሪነት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
\"\"

ሁለተኛው አጋማሽም ሁለቱም ቡድኖች እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ውጥረት የሞላበት እና አልሸነፍ ባይነት የተመለከትንበት አጨዋወት ሲሆን ነገሌ አርሲዎች ግብ ለማስቆጠር ገላን ከተማዎች ደግሞ ግብ ላለማስተናገድ ያደረጉትን ጥረት ተመልክተናል። መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ተጠናቆ በተጨመረው ተጨመረው ደቂቃ ነገሌ አርሲዎች ያገኙትን የመጨረሻ የግብ ዕድል በአብዱላዚዝ አብደላ አማካኝነት በማስቆጠር ቡድኑን ከሽንፈት መታደግ ችሏል።