ሶከር ሜዲካል | የአበረታች መድኃኒቶች ቁጥጥር በምን ሁኔታ ላይ ይገኛል ?

በሀገራችን እግርኳስ ስላለው የአበረታች መድኃኒቶች ቁጥጥር ተከታዩን ፅሁፍ አዘጋጅተናል።

በእግርኳስ ውስጥ ጨዋታን ፍትሃዊ ማድረግ ከዋና የውድድሩ መርሆች መካከል ዋናው ነው፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ ከሚወሰዱ እርምጃዎች መካከል አበረታች መድኃኒቶች ላይ የሚደረግ ቁጥጥር አንዱ ነው፡፡ የእግርኳስ የበላይ አካል የሆነው FIFA ከዓለም አቀፍ የፀረ-አበረታች መድኃኒት ባለስልጣን (WADA) ጋር አንድ ላይ በመሆን ሰፊ ሥራዎችን እየሰራ ይገኛል፡፡ ለዚህም ማሳያ የሚሆነው በቅርቡ በካታር በተካሄደው አለም ዋንጫ ወቅት በአጠቃላይ 2846 ምርመራዎች መደረጋቸው ነው፡፡ በሀገራችን ያለውን ሁኔታ ስንመለከት ምንም እንኳን በተለያዩ ወቅቶች ለተጫዋቾች ፣ ለአሰልጣኞች እና ለክለብ አመራሮች አበረታች መድኃኒቶችን በተመለከተ የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች ቢዘጋጁም ተጫዋቾች ላይ እየተደረገ ያለው ምርመራ ግን የሚፈለገው ደረጃ ላይ አይደለም፡፡

\"\"

ለፕሪሚየር ሊጉ ተጫዋቾች የሚደረገው ምርመራ ዱባይ እና ካታር የሚሰራ ሲሆን ዋጋውም እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ ናሙና የማጓጓዣ ወጪን ሳይጨምር አንድ የሽንት ምርመራ ለማሰራት እስከ 160 ዶላር እንደሚፈጅ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ በዚህም ምክንያት የሚመረመረው የተጫዋች ቁጥር አነስተኛ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች መድኃኒት ባለስልጣን በጀት የሚፈቅደውን ያህል ከ30 እስከ 40 የሚሆኑ ምርመራዎች በዓመት ውስጥ ይደረጋሉ፡፡ ይህ ደግሞ የምርመራው መጠን በበቂ ሁኔታ እየተደረገ ስላለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡

ጠንከር ያለ የምርመራ አተገባበር ቢኖር ምን ያህል ተጫዋች ያልፋሉ የሚለው ጉዳይ አሳሳቢ ነው፡፡ በሀገራችን አዲስ በወጣው የታገዱ መድኃኒቶች ዝርዝር ውስጥ ያሉትን ስኒፕ እና ትራማዶል መጠቀም የተለመደ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ እንደ ካፍ መስፈርት መሰረት በየጊዜው ከሚካሄዱ ውድድሮች በፊት ምርመራ ይደረጋል፡፡ እስካሁንም ምርመራውን የወደቀ ተጫዋች የለም፡፡ በክለብ በኩል ግን ከጥቂት ወራት በፊት የመከላከያው አሌክስ ተሰማ ካቲኖን የተሰኘ አነቃቂ ንጥረ ነገርን ተጠቅሞ በመገኘቱ የአንድ ዓመት እገዳ እንደተጣለበት ይታወሳል፡፡ በፕሪሚየር ሊግ አክስዮን ማህበር በኩል ተጫዋቾች አንድን መድኃኒት ከመውሰዳቸው በፊት ፎርም መሙላት እና ለሚመለከተው ኮሚቴ ማስተላለፍ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ የክለብ የጤና ባለሙያዎች እንዴት መቆጣጠር እና ፎርሙን መሙላት እንዳለባቸው ገለፃ መደረጉን የሊግ ካምፓኒው ዋና ሜዲካል ኦፊሰር ዶ/ር ፍሬው አስራት አስረድተዋል፡፡

\"\"

በቀጣይ ወር ሊግ ካምፓኒው ከብሔራዊ ፀረ-አበረታች መድሃኒት ጋር አንድ ላይ በመሆን ሰፋ ያለ ሥልጠናን ለመስጠት እየተዘጋጀ መሆኑን ዶ/ር ፍሬው አክለው ገልጸዋል፡፡ ሥልጠናው በቅርቡ ተሻሽሎ የቀረበው የተከለከሉ መድሃኒቶች ዝርዝር ላይ ትኩረቱን ያደርጋል፡፡ ይህንን በተመለከተ ዋናው የሊግ ካምፓኒ ግብም ግንዛቤን መፍጠር እና ክለቦች ለቅጣት እንዳይጋለጡ መከላከል ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ ከአትሌቲክስ ብቻ ጋር ተያይዞ የነበረውን የፀረ-አበረታች መድኃኒት ቁጥጥር ወደ እግር ኳሱም ማምጣት ነው፡፡ እንደዚሁም በደጋፊዎች በኩል ያለው እውቀት እንዲጨምር በሥራ ላይ ነው፡፡