የሴቶች ፕሪምየር ሊግ | መሪው ንግድ ባንክ እና ተከታዮቹ የመጀመሪያውን ዙር በድል ቋጭተዋል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 13ኛ ሳምንት ጨዋታቸው ዛሬ በተደረጉ ሦስት መርሀግብሮች ሲጀመር የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንዲሁም ተከታዮቹ ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና አርባምንጭ ከተማ አሸንፈዋል።

የአንደኛው ዙር የመጨረሻ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ መደረግ ሲጀምሩ ረፋድ ላይ የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ይርጋጨፌ ቡና ተጫወተዋል። በመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ተቀራራቢ የጨዋታ መንገድን በሁለቱም ቡድኖች በኩል መመልከት ብንችልም ወደ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ተጠግቶ ልዩነት ከመፍጠሩ አንፃር ግን ንግድ ባንኮች በተሻለ ቆይታ ነበራቸው። በተለይ ቡድኑ ወደ ግራ መስመር ያደላ እንቅስቃሴን በድግግሞሽ መጠቀሙ ጎል እንዲያገኝ አስችሎታል። 22ኛው ደቂቃ ላይ መነሻውን ከመዲና ዐወል ያደረገን ኳስ ያገኘችው አረጋሽ ካልሳ በጥሩ አጨራረስ ከመረብ አዋህዳ ቡድኗን መሪ አድርጋለች። ይርጋጨፌዎች ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ በሚሻገሩ ኳሶች ወደ ቀኝ መስመር አጋድለው ለመንቀሳቀስ ጥረት ቢያደርጉም የንግድ ባንክን ጠጣር የተከላካይ ክፍል ለማለፍ አልታደሉም።

ጨዋታው በሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ንግድ ባንክ ለሀያ አምስት ያህል ደቂቃዎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ መዲና እና አሪያትን የትኩረት አድርገው ልዩነቱን በይበልጥ ለማስፋት ጥረዋል። በተቃራኒው በአሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ የሚመሩት ይርጋጨፌ ቡናዎች በተለይ በቀኝ መስመር በኩል በተሰለፈችው መስታወት አመሎ አማካኝነት ዕድሎችን ለማግኘት ቶሎ ቶሎ ኳስን ማግኘት ቢችሉም የሚያገኟቸውን ኳሶች ወደ ጎልነት በመቀየሩ ረገድ ፍፁም ደካሞች ነበሩ።

\"\"

ይሁን እንጂ 52ኛው ደቂቃ ላይ አሪያት ኦዶንግ ከሳጥን ውጪ ግሩም ጎል ስታስቆጥር 66ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በአሪያት ኦዶንግ ላይ የይርጋጨፌ ቡና ተከላካዮች የሰሩትን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት አረጋሽ ካልሳ የዓመቱ 13ኛ ጎሏን ለቡድኗ ሦስተኛ ጎል ከመረብ አዋህዳለች። የመጨረሻዎቹን አስር ደቂቃዎች ተጭነው በመጫወት ወደ ጨዋታ ለመመለስ የጣሩት ይርጋጨፌ ቡናዎች በየሺ አስመቼ አማካኝነት ከባዶ መውጣት ያስቻለችን ግብ አስቆጥረው ጨዋታ 3-1 ተጠናቋል።

ከመሪው ንግድ ባንክ እግር በእግር እየተከተለ የሚገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከደሞወዝ ጉዳዮች ጋር ስሙ ተያይዞ የሚብጠለጠለውን አዳማ ከተማን ጋብዞ ግማሽ ደርዘን ጎልን ከጨዋታ ብልጫ ጋር በማሳረፍ ወሳኝ ሦስት ነጥብን አሳክቷል።

\"\"

ሁለቱንም የጨዋታ አጋማሾች ፍፁማዊ የጨዋታ ብልጫን ያሳዩት የአሰልጣኝ መሠረት ማኔ ተጫዋቾች ኳስን በራሳቸው እግር ስር በማድረግ በአንድ ሁለት ቅብብል ወደ መስመር አጋድሎ በመጫወት በደካማው አዳማ ላይ ጥቃትን በተደጋጋሚ ሰንዝረዋል። ጨዋታው 33ኛ ደቂቃ ላይ መዳረሻውን እንዳደረገ ከወትሮ እንቅስቃሴዋ ተሽላ የታየችው ዙለይካ ጁሀድ ለኤሌክትሪክ አስቆጥራ ቡድኑን መሪ አድርጋለች። ከሦስት ደቂቃዎች ቆይታ መልስ የትንቢት ሳሙኤል ጥሩ ዕይታ ታክሎበት ሰላማዊት ጎሳዬ በጥሩ አጨራረስ ሁለተኛ ግብ አድርጋለች። ፋታ የለሽ እንቅስቃሴያቸውን በተጋጣሚያቸው ማሳረፋቸውን የቀጠሉት ኤሌክትሪኮች 37ኛ ደቂቃ ላይ በትንቢት ሳሙኤል የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ በጭማሪው ደቂቃ ላይ የአዳማ ተከላካዮች ኳስ በሳጥን ውስጥ በእጅ በመንካታቸው የተሰጠውን የፍፁም ቅጣት ምት ህይወት ደንጌሶ አስቆጥራው ኤሌክትሪክን 4-0 በማድረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ጨዋታው በሁለተኛ የጨዋታ አርባ አምስት ሲመለስ አሁንም የተጫዋች ለውጥን ጭምር በማድረግ የበላይነትን የወሰዱት አሁንም ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ሆነዋል። ከጨዋታ ጨዋታ የወጥነት ችግር የሚታይባቸው አዳማዎች ወደ ጨዋታ ለመመለስ ደካማ ፍላጎትን ማሳየታቸው ተጨማሪ ጎሎችን ለማስተናገድ እንዲገደዱ አድርጓቸው ተስተውሏል። 75ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ሰብለወንጌል ወዳጆ ነፃ ቦታ ላይ ለተገኘችው ሰላማዊት ስትሰጣት አጥቂዋ በፍጥነት ወደ ሳጥን ስታሻግር ተቀይራ የገባችው ምንትዋብ ዮሐንስ አምስተኛ ግብን በጥሩ አጨራረስ ግብ አድርጋዋለች። 84ኛው ደቂቃ ምንትዋብ ዮሐንስ ለራሷ ሁለተኛ ለቡድኗ ስድስተኛ እና የማሳረጊያ ጎል አድርጋው ጨዋታው 6-0 በኢትዮ ኤሌክትሪክ አሸናፊነት ተቋጭቷል።

\"\"

10 ሰዓት ላይ በደረጃ ሰንጠረዡ ሦስተኛ ላይ የተቀመጠው አርባምንጭ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማ ላይ ሦስት ግቦች ከመረብ አሳርፎ አሁንም በድል ጉዞው ቀጥሏል። በእንቅስቃሴ ረገድ ምንም እንኳን በቦሌ የመበለጥ ዕድሉ ቢነፈገውም የሚያገኟቸውን ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀሙ የአሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልዱ እንስት አዞውቹ በብዙ ረገድ የተሻሉ ነበሩ። በሚሻገሩ ረጃጅም ኳስች ኳስን ይዞ ከሚጫወተው ቦሌ በተቃራኒው በመጫወት ጥቃት የመሰንዘሩን መንገድ ያስቀጠሉት አርባምንጭ ከተማዎች ገና በጨዋታው ጅማሮ 3ኛ ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ መሠረት ወርቅነህ ግሩም ግብን አስቆጥራለች።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ቦሌ ክፍለ ከተማ አሁንም የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሳቸው አድርገው መንቀሳቀስን ምርጫቸው አድርገው መቀጠል ቢችሉም ከጎል ጋር ሲገናኙ አይምሬ የነበሩት አርባምንጭ ከተማዎች በመሠረት ወርቅነህ እንዲሁም በቤተልሄም ታምሩ ተጨማሪ ጎሎች 3-0 አሸንፈው ጨዋታውን አጠናቀዋል።