ዛሬ ምሽት ከዋልያዎቹ ጋር የሚፋለሙት የአልጄሪያዎች ወሳኝ ተጫዋች የቅድመ-ጨዋታ አስተያየቱን ሰጥቷል።
በደማቅ ሁኔታ በኤልጄሪያ አራት ከተሞች እየተከናወነ የሚገኘው የቻን ውድድር ከተጀመረ ዛሬ አምስተኛ ቀኑን ይዟል። በአምስተኛ ቀን ውሎም የምድብ ሁለተኛ ጨዋታዎች የሚደረጉ ሲሆን በምድብ አንድ የምትገኘው ኢትዮጵያም ምሽት 4 ሰዓት ከአስተናጋጇ አልጄሪያ ጋር ተጠባቂውን ፍልሚያ ትከውናለች። በአልጄሪያ በኩል የቡድኑ ዋና አሠልጣኝ መጂድ ቡጌራ የሰጡትን የቅድመ-ጨዋታ አስተያየት ትናንት ያስነበብን ሲሆን አሁን ደግሞ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ዛካሪያ ድራዊ ከጨዋታው ጋር ተያይዞ ለብዙሃን መገናኛ አባላት የተናገረውን አጠር ያለ ሀሳብ ይዘን ቀርበናል።
\”ውድድራችንን ሊቢያን አንድ ለምንም በማሸነፍ በጥሩ ሁኔታ ጀምረናል። የራስ መተማመናችንን እንድናገኝ የሚያደርግ ውድ ድል ነው ያገኘነው። አሁን ደግሞ ከኢትዮጵያ ጋር ላለብን ወሳኝ ጨዋታ እየተዘጋጀን ነው። ጨዋታውን አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ስራውን መስራት የእኛ ኃላፊነት ነው።\”በማለት የቤሉይዝዳድ ተጫዋች የሆነው ዛካሪያ ተናግሯል።
የተከላካይ አማካዩ ጨምሮ \”በአልጄሪያ የውስጥ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች ምን ያልህ ብቃት እንዳላቸው ለማሳየት እንሞክራለን ፤ በዚህም ጨዋታዎችን እያሸነፍን በተቻለን አቅም በውድድሩ ሩቅ ለመጓዝ እንጥራለን።\” ካለ በኋላ ከዛሬው የኢትዮጵያ ጨዋታ በፊት ሁሉም ተጫዋቾች በተነቃቃ ስሜት ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁሟል።
\”ሁሉም ተጫዋቾች በጨዋታው ያላቸውን ለማድረግ በጥሩ ተነሳሽነት ላይ ይገኛሉ። ሁላችንም እዚህ የተገኘነው ለደጋፊዎቻችን ደስታን ለመስጠት ነው።\” በማለት ሀሳቡን አገባዷል።