ከፍተኛ ሊግ | የ10ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ በሦስቱ አስታናጋጅ ከተሞች 11 ጨዋታዎች ተደርገውበታል።

በቶማስ ቦጋለ ፣ ጫላ አቤ እና ተመስገን ብዙዓለም

የ03:00 ጨዋታዎች

በምድብ \’ሀ\’ ባህርዳር ላይ ቡታጅራ ከተማን ከባቱ ከተማ ሲያገናኝ መጠነኛ ፉክክር ባስተናገደው የመጀመሪያ አጋማሽ በጥሩ የጨዋታ ስሜት  ቢጀመርም ቀስ በቀስ ግን በሚከሰቱ አካላዊ ንክኪዎች አሰልቺ እየሆነ ሄዷል። የቡታጅራው ሄኖክ መርሹ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያደረገውና ግብጠባቂው በእግሩ ያስወጣበት ኳስ በአጋማሹ የተሻለው ሙከራ ነበር።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ በመጠኑ ተሻሽሎ ሲቀጥል 60ኛው ደቂቃ ላይ የቡታጅራው ተስፋዬ ባደርጋ ከሳጥኑ አጠገብ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው መልሶበታል። አልፎ አልፎ ከሚያደርጓቸው ፈታኝ ያልሆኑ ሙከራዎች ውጪ የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር የተቸገሩት ባቱዎች 61ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ምቹ አጋጣሚ አግኝተው የነበረ ሲሆን ሳጥን ውስጥ ኳስ ያገኘው ዮሐንስ ደረጄ ዒላማውን ባልጠበቀ ሙከራ የግብ ዕድሉን አባክኗል። ጨዋታው እጅግ እየተቀዛቀዘ ሄዶ የተሻለ የግብ ዕድል ሳይፈጠርበትም 0-0 ተጠናቋል።

ጅማ ላይ በምድብ \’ለ\’ አዲስ አበባ ከተማ ከ ቦዲቲ ከተማ ሲገናኙ በመጀመሪያው አጋማሽ አዲስ አበባዎች ጥሩ እንቅስቃሴ በማድረግ የተሻሉ ነበሩ። መኃል ሜዳ ላይ ብልጫን በመውሰድ በሙሉቀን ታሪኩ ፣  አዲሱ ሰይፉ እና አዲስ አለም ዘውዱ ሙከራዎች ቢያደርጉም  ጎል እና መረብ ማገናኘት አልቻሉም። 34ኛው ደቂቃ ላይ አዲስአበባዎች አምበላቸውን በሁለት ቢጫ ካርድ አጥተዋል። ቦዲቲዎች በበኩላቸው ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋት በሚያገኙት ኳስ በመልሶ ማጥቃት ሙከራዎችን ቢያደርጉም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ አጋማሹ ተጠናቋል።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ቦዲቲዎች ተሻሽለው ሲቀርቡ ባገኙት የተጫዋች ቁጥር ብልጫ በተቃራኒ ሜዳ ክልል ኳስን በመጫወት ሲንቀሳቀሱ 81ኛው ደቂቃ ላይም በ ከድር ገንሳ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። አዲስ አበባዎች በሁለተኛው አጋማሽ በቁጥር ማነሳቸውን ተከትሎ መከላከሉ ላይ በማመዘን የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ሲከተሉ 72ኛው ደቂቃ ላይ ወንድሜነህ  ዘሪሁን ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡ ቋሚ መልሶበታል። ጨዋታውም ያለግብ ተጠናቋል።

የ05:00 ጨዋታዎች

ባህርዳር ላይ አቃቂ ቃሊቲን ከጅማ አባ ቡና ባገናኘው ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢታይም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረሱ በኩል ግን አባ ቡናዎች የተሻሉ ነበሩ። የጨዋታውን የመጀመሪያ ፈታኝ ሙከራም 26ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ብዙዓየሁ እንደሻው ከሳጥን ውጪ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡን የላዩ አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል። በሴኮንዶች ልዩነትም በተመሳሳይ ሁኔታ ግሩም ሙከራ ማድረግ ችሏል። ከራሳቸው የሜዳ ክፍል ተረጋግተው ለመውጣት የተቸገሩት አቃቂዎች 42ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት የሚጀምሩበትን ዕድል አባክነዋል። በግራ መስመር የተሰጠውን የቅጣት ምት በኃይሉ ወገኔ ሲመታ ግብጠባቂው መልሶበታል። ያንኑ ኳስ ሳይረጋጋ ያገኘው ቢኒያም ሲራጅ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በብርቱ ፉክክር ታጅቦ ሲቀጥል አጋማሹ በተጀመረ በሴኮንዶች ውስጥ በኃይሉ ወገኔ ከተጋጣሚ የሳጥን አጠገብ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡ የግራ ቋሚ መልሶበታል። ከኳስ ውጪ እጅግ ፈታኝ የነበሩት እና በጥንቃቄ ሲጫወቱ የነበሩት ጅማ አባ ቡናዎች 57ኛው ደቂቃ ላይ በብዙዓየሁ እንደሻው ድንቅ የቅጣት ምት ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።  የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር መቸገራቸውን የቀጠሉት እና ይባስ ብሎም 69ኛው ደቂቃ ላይ ማዕሩፍ መሐመድን በቀይ ካርድ ያጡት አቃቂዎች 75ኛው ደቂቃ ላይ በከድር አድማሱ የፍጹም ቅጣት ምት ግብ አቻ መሆን ችለዋል። 80ኛው ደቂቃ ላይ ኑርላይን አብዱልሳመድ ብዙዎችን ያስደነገጠ ከፍተኛ ጉዳት እግሩ ላይ አስተናግዶ ወደ ሆስፒታል ሲያመራ ሌላኛው የቡድኑ አጋር ጃፋር ከበደ 90ኛው ደቂቃ ላይ ተገልብጦ ግሩም ግብ አስቆጥሯል። ጨዋታውም በጅማ አባቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

\"\"

እንጅባራ ከተማ እና አምቦ ከተማ ባደረጉት ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ እንጅባራ ኳስ መስርተው በመጫወት በሁሉም የሜዳ ክፍሎች እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ገና በ 2ተኛው ደቂቃም የግብ ሙከራ አድርገዋል። 9ኛው ደቂቃ ላይ አበበ ታደሰ በፍጹም ቅጣት ምት እንጅባራን በጎል ቀዳሚ ሲያደርግ 31ኛው ደቂቃ ላይም ባሐሩ ፈጠነ ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል። በጨዋታው ብልጫ የተወሰደባቸው አምቦዎች በመልሶ ማጥቃት 27ኛው ደቂቃ ላይ በገላን በዳዳ አማካኝነት ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ ተብሎ ተሽሮባቸዋል።

ከዕረፍት መልስ አምቦዎች ተሻሽለው ሲቀርቡ እንጀባራዎች በአንጻሩ ተቀዛቅዘው ቀርበዋል። 46ኛው ደቂቃ ላይ ሀብታሙ ጥላሁን ለእንጅባራ ግብ አስቆጥሮ የክለቡን መሪነት ሲያጠናክር ከግቧ መቆጠር በኋላ አምቦዎች በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርሱ 74ኛው ደቂቃ ላይ ሳዲቅ አክመል ባስቆጠሯት ግብ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥረዋል። እንጅባራዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል በመጠጋትም በመልሶ ማጥቃት ያገኟቸውን ንጹህ የግብ ዕድሎች ሳይጠቀሙባቸው ቀርተዋል። ጨዋታውም በእንጅባራ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በምድብ ሐ ደረጃው ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ የሚገኙት ሮቤ እና ሶዶ ባደረጉት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በወንድማገኝ ታደሰ የሚመራው የሮቤ ከተማው የመሀል ክፍል ብልጫ የታየበትና ለፊት መስመሩ በተደጋጋሚ የግብ ዕድል የፈጠሩ ቢሆንም ወደ ግብ መቀየር ተስኗቸው ታይቷል። በአንፃሩ ሶዶ ከተማዎችም የሚያገኙትን ኳሶች በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ወደ ተቃራኒ የግብ ክልል ለመድረስ ቢሞክሩም በጠንካራ የሮቤ ከተማዎች የተከላካይ ክፍል ሲያቋርጧቸው የተመለከትን ሲሆን አጋማሹም ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል ማምራት ችለዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽም እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የመሀል ክፍሉ በሮቤ ከተማ የበላይነት የቀጠለ ሲሆን መጨዋታው ድንቅ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ወንድማገኝ ታደሰ ከመሀል ሜዳ በሚነሱ ድንቅ ድንቅ ኳሶች ወደ ፊት መስመር እና ወደ ክንፍ በማሻገር የግብ እድሎች እንዲፈጠሩ ሲጥር የነበረ ሲሆን ሶዶ ከተማም አልፎ አልፎ ሲያገኙ የነበሩትን የመልሶ ማጥቃት እድል ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። መደበኛው ሰዓት ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ሮቤ ከተማዎች ያገኙትን የግብ እድል ተመስገን ይልማ ወደ ግብ የመታውን ኳስ የግቡ ቋሚን ገጭቶ መውጣት በመቻሉ ጨዋታወም ያለ ምንም ግብ ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል።

የ08:00 ጨዋታዎች

በምድብ \’ሀ\’ ባህርዳር ላይ ዱራሜ ከተማ እና ወልዲያ ከተማ ሲገናኙ ብርቱ ፉክክር የታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ለተመልካች ሳቢ ነበር። ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ በማድረግ የጀመሩት ዱራሜዎች 15ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። አለኝታ ማርቆስ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ኪሩቤል ካሳ ከሳጥን አጠገብ በግሩም አጨራረስ ግብ ማስቆጠር ችሏል።

\"\"

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ይበልጥ ተጋግለው ጨዋታውን የቀጠሉት ወልዲያ ከተማዎች 22ኛው ደቂቃ ላይ በቢንያም ጥዑመልሳን የግንባር ኳስ አቻ መሆን ችለዋል። በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት የየጁ ፍሬዎች በቢንያም ጌታቸው ፣ ኃይሌ ጌታሁን እና ቢንያም ጥዑመልሳን ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑም ቢሆን ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ወልዲያዎች መጠነኛ ብልጫን ወስደዋል። 48ኛው ደቂቃ ላይ ቢንያም ጥዑመልሳን ወደ ግብ ሞክሮት ግብጠባቂው ማፑቱ ይስሃቅ በእግሩ ሲመልስበት 67ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋ ማቲዎስ ግሩም ሙከራ ቢያደርግም የግቡን የቀኝ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ጨዋታውን ከጀመሩበት ስሜት እጅግ እየተቀዛቀዙ የሄዱት ዱራሜዎች በአጋማሹ የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በሚያገኙት ኳስ ሁሉ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ወልዲያዎች 80ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው ኃይሌ ጌታሁን ባስቆጠራት ግብ 2-1 ማሸነፍ ችለዋል። ውጤቱን ተከትሎም ወልዲያ ከተማ ነጥቡን 21 በማድረስ ከመሪው ቤንች ማጂ ቡና ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ አንድ ዝቅ አድርጓል።

\"\"

ጅማ ላይ በምድብ \’ለ\’ ከንባታ ሺንሽቾ እና ይርጋጨፌ ቡና ሲገናኙ በኳስ ቁጥጥሩ ከንባታዎች በመጠኑ የተሻሉ የነበር ሲሆን የግብ ዕድል በመፍጠሩ በኩል ግን ሁለቱም ደካማ እንቅስቃሴ አሳይተዋል። ከንባታ ሺንሽቾዎች ወደ ቀኙ የሜዳ ክፍል አመዝነው ለማጥቃት ቢሞክሩም ፈታኝ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ከዕረፍት መልስም ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ይርጋ ጨፌዎች ቀስ በቀስ እየተሻሻሉ መጥተዋል። 56ኛው ደቂቃ ላይ የከንባታው ተካልኝ መስፍን ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው መልሶበታል።

\"\"

ይርጋ ጨፌዎች 73ኛው ደቂቃ ላይ በኤፍሬም ቶማስ ግብ ቢያስቆጥሩም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሮበታል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።

ሆሳዕና ላይ በምድብ ሐ ኦሜድላ እና ቡራዩ ከተማ ተገናኝተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አንስቶ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ያየንበት እና ኦሜድላዎች ተሽለው የታዩበት አጋማሽ ሲሆን በ28ኛው ደቂቃ ያገኙትን የቅጣት ምት ታምራት እያሱ የተሻገረውን ኳስ በግንባር በማስቆጠር ኦሜድላዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላም በሁለቱም በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ በአንፃሩ ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን በኦሜድላዎች በኩል በመጀመሪያ አጋማሽ ያስቆጠሩትን ግብ ለማስጠበቅ ተቀዛቅቀው የተጫወቱ ሲሆንም ቡራዩ ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር አልፎ አልፎ የሚፈጥሩትን የግብ እድል ሳይጠቀሙ ቀርተዋል። ጨዋታውም በኦሜድላ አሸናፊነት ተጠናቆ ጣፋጭ ሶስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

የ10:00 ጨዋታዎች

በበርካታ ደጋፊዎች ታጅቦ እና በብዙዎቹ በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው የቤንች ማጂ ቡና እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የምድብ ሀ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ ፉክክር ቢታይበትም የመረጡት ጥንቃቄ የተሞላ አጨዋወት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸውን ገድቦት ታይቷል። 6ኛው ደቂቃ ላይ የቤንች ማጂው ኤፍሬም ታምሩ ሳጥን ውስጥ ለማስቆጠር ምቹ የሆነ ኳስ አግኝቶ ቢሞክርም ግብጠባቂው አላዛር ማረኔ መልሶበታል። አቦሎቹ ፈታኝ ሙከራ ለማድረግ ይቸገሩ እንጂ አልፎ አልፎ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማድረግ መጣራቸውን ሲቀጥሉ ንግድ ባንኮች በበኩላቸው እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ለመድረስ ሲቸገሩ አብዱለጢፍ ሙራድ ከረጅም ርቀት ያደረገውና ዒላማውን ሳይጠብቅ የወጣው ኳስ በአጋማሹ ብቸኛ ሙከራቸው ነበር።

\"\"

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተቀዛቅዞ ሲቀጥል ሁለቱም ከወትሮው በተለየ ከሚታወቁበት የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ወርደው ታይተዋል። በመጠኑም ቢሆን ግን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ቤንች ማጂዎች የተሻሉ ነበሩ። 50ኛው ደቂቃ ላይም ብሩክ ወልዱ ከሳጥን አጠገብ ግሩም ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው አላዛር ማረኔ መልሶበታል። 80ኛው ደቂቃ ላይም ጴጥሮስ ገዛኸኝ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ተደርበውበት ኳሱ የግቡን የቀኝ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮችም በጨዋታው አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው ያለግብ ተጠናቋል።

ጅማ ላይ ደብረ ብርሃን እና ጅንካን ባገናኘው ጨዋታ ጅንካዎች በጥብቅ መከላከል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በመልሶ ማጥቃት በተደጋጋሚ ከቀኝ መስመር በመነሰት ማጥቃት ችለዋል። በ7ኛው ደቂቃ የደብረ በርሃኑ ተጫዋች የሆነው በኃይሉ በለጠ በራሱ ላይ ሲያስቆጥር ጅንካ መሪነቱን ይዟል። በተደጋጋሚ ከመስመር የሚሻገሩ ኳሶችን ኑር ሀሰን በግንባር ቢገጭም ጎል ሳያስቆጥር ቆይቷል። በ25 ደቂቃ ግን ኑር ሀሰን ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ቀይሮታል። ደብረ ብርሃኖች ኳስን ይዞ በመጫወት ከጅንካዎች ብልጫ ቢወስዱም በመከላከል ረገድ ጅንካዎች ሙከራዎች እያከሸፉባቸው ቆይተዋል። በ38ኛው ደቂቃ የተሻ ግዛው ለደብረ ብርሃን ጎል ሲያስቆጥር ከጎሏ በኋላ ከፍተኛ መነቃቃት በተደጋጋሚ ወደ ጎል በመድረስ በጭማሪ ደቂቃ የተሻ ግዛው እና ሙሉቀን ወንድሙ ሙከራ ቢያደርጉም ጎል ሳያስቀጥሩ ቀርተዋል።

\"\"

በሁለተኛ አጋማሽ በደብረ ብርሃን ቡድን በኩል ከፍተኛ የማሸነፍ ፍላጎት ሲታይ በጨዋታውም ብልጫ በመውሰድ የበላይ ሆነዋል። ኳስን ይዞ በመጫወት ወደ ጎል በተደጋጋሚ ሲሄዱ በ76ኛው ደቂቃ መስፍን ኪዳኔ ለደብረብርሃን የአቻነት ጎል ማስቆጠር ችሏል። ደብረብርሀኖች በተቀሩት ደቂቃዎች ለማሸነፊያ የምትሆን ጎል ለማግኘት ጥረት ቢያደርጉም በጅንካ ጥብቅ የመከላከል ታክቲክ ጎል ሳያስቆጥሩ ቀርተዋል። ጅንካዎች በሁለተኛ አጋማሽ አፈግፍገው ለመጫወት ሲሞክሩ የአቻነት ግብ ሲቆጥርባቸው ጎሉ ከተቆጠረባቸው ደቂቃ በኋላ እያንዳንዷን የደብረ ብርሃንን እንቅስቃሴ በመከላከል መግታት ችለዋል። ጨዋታውም 2-2 ተጠናቋል።

በምድብ ሐ ገላን ከተማ እና ስልጤ ወራቤ የዕለቱን የመጨረሻ ጨዋታ አድርገዋል። የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ክለቦች መካከል የአልሸነፍ ባይነት መንፈስ የታየበት እና ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ ያየንበት አጋማሽ ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩ የስልጤ ወራቤ መጠነኛ የበላይነት የታየበት እና ገላን ከተማዎች የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ታይቷል። በእንደዚ ዓይነት አጨዋወት የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ምንም ግብ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

\"\"

ሁለተኛው አጋማሽ እንደመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የሚባል እንቅስቃሴ የተመለከትን ሲሆን በተጨማሪም ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ የመድረስ እንቅስቃሴ የታየበት አጋማሽ ሲሆን በ64ኛ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን ምት የተሻገረውን ኳስ ተመስገን አዳሙ በግንባሩ በማስቆጠር ገላን ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ስልጤ ወራቤዎች ጫና በመፍጠር በርከት ያሉ የግብ ሙከራዎችን የፈጠሩ ቢሆንም ገላን ከተማዎች በመከላከሉ ረገድ ተሽለው በመገኘታቸው ግብ ሳያስተናግዱ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።