የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚጀመርበት ቀን ታውቋል

በዋልያዎቹ የቻን ተሳትፎ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው ቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚጀመርበትን ቀን የውድድሩ የበላይ አካል ለክለቦች አሳውቋል።

\"\"

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የበላይነት የሚደረገው የሀገሪቱ ከፍተኛው የሊግ እርከን ውድድር ታኅሣሥ 16 ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቻን ዝግጅት እና ውድድር መቋረጡ ይታወሳል። ብሔራዊ ቡድናችንም በውድድሩ ሁለት የምድብ ጨዋታዎችን አድርጎ በአንድ ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን የፊታችን ቅዳሜ የመጨረሻ የምድብ ፍልሚያውን አከናውኖ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ እና አለማለፉን ይለያል። ይህ በእንዲህ እንዳለ የሊጉ የበላይ አካል በዛሬው ዕለት ሊጉ የ14ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን ማከናወን የሚጀምርበትን ቀን ለክለቦች በላከው ደብዳቤ አሳውቋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቻን ተሳትፎውን ካገባደደ ከአምስት ቀናት በኋላ ሊጉ ጨዋታዎችን ማከናወን እንደሚጀምር ተጠቁሟል። ከ14ኛ ሳምንት ጀምሮ የሚደረጉት ጨዋታዎች ደግሞ በአዳማ ሳይንስ እና ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እንደሚከናወኑ ተገልጿል።

\"\"

የቀጣይ ሳምንታት መርሐ-ግብሮች ይፋ ባይሆኑም በአዳማ የሚደረጉት ጨዋታዎች በቀን ሁለት ጊዜ ዘጠኝ እና አስራ ሁለት ሰዓት ሊከወኑ እንደታሰበ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።