👉 \”እንደ አሠልጣኝ ሥራዬ ከተከላካይ እስከ አጥቂ ድረስ ቡድን መገንባት ነው። የግብ ዕድሎችን እየፈጠርን ባይሆን ችግር አለ ማለት ነው ፤ ግን…\” አሠልጣኝ ውበቱ
👉 \”ምንም እንኳን ሊቢያ ጠንካራ እንደሆነች ብናውቅም ጨዋታውን ለማሸነፍ እና ወደቀጣዩ ዙር ለማለፍ እንጥራለን\” ጋቶች
👉 \”ለወደፊቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ግንባታ እየፈፀምን ነው\” አሠልጣኝ ውበቱ
በቻን ውድድር ላይ እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት በአናባ ከተማ በሚገኘው ሜ 19 ስታዲየም ከሊቢያ አቻው ጋር ወሳኝ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል። ወደ ቀጣይ ዙር ለማለፍ ይህንን ጨዋታ ማሸነፍ እና የሞዛምቢክን መሸነፍ የሚጠብቀው ቡድኑ ከጨዋታው በፊት በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና አማካዩ ጋቶች ፓኖም አማካኝነት የቅድመ-ጨዋታ አስተያየት አልጄሪያ ለሚገኙ የብዙሃን መገናኛ አባላት ሰጥቷል። በቅድሚያም አሠልጣኙ ተከታዩን በማለት ንግግራቸው ጀምረዋል።
\”የዛሬው ጨዋታ ለእኛ በጣም ወሳኝ ነው። የሊቢያ ብሔራዊ ቡድን እንደአጋጣሚ ሁለቱን የምድብ ጨዋታዎች ቢሸነፍም ጥሩ ቡድን ነው። አሁን ላይ አንድ ነጥብ ነው ያለን ፤ ግን በእኛ የሚወሰን ባይሆንም የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፍን ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ የተሻለ ዕድል ይኖረናል። ለዚህም ደግሞ ያለንን ሁሉ እንሰጣለን።\” ብለዋል።
አሠልጣኝ ውበቱ ቀጥለው የሊቢያ ብሔራዊ ቡድን ከውድድሩ ውጪ መሆኑ ቢታወቅም የ2014 ሻምፒዮን መሆኑን አንስተው የኮረንቲን ማርቲንስ ቡድን ሜዳ ላይ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል። \”ሊቢያዎች ከእኛ የተሻለ በምቾት ሊጫወቱ ይችላሉ ፤ ምክንያቱም ከእኛ ያነሰ ጫና ስላለባቸው። ለክብር ብለውም ስለሚጫወቱ ጨዋታው ከበድ ሊል ይችላል።\”
ከአጨራረስ ጋር በተያያዘ እየተቸገረ ያለው ዋልያው እስካሁን አንድም ጎል አለማስቆጠሩን ተከትሎ \”ስላለፈው ነገር ማሰብ አልፈልግም። ብዙ ዕድሎችን አባክነናል። በአንዳንድ አጋጣሚዎ ጥሩ ብንጫወትም ግብ ካላስቆጠርን አናሸንፍም። ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ግቦችን ማስቆጠር አለብን። በጨዋታው ተስፋ እንደቆረጠ ቡድን አንጫወትም ፤ ጨዋታውን ለመቆጣጠር እንሞክራለን።
\”እንደ አሠልጣኝ ሥራዬ ከተከላካይ እስከ አጥቂ ድረስ ቡድን መገንባት ነው። የግብ ዕድሎችን እየፈጠርን ባይሆን ችግር አለ ማለት ነው ፤ ግን የግብ ዕድሎችን እየፈጠርን ነው። ስለዚህ ጎል እናገባለን። በሊቢያውም ጨዋታ እንደምናገባ አስባለው።\” በማለት ሀሳባቸውን ለግሰዋል።
መድረኩን አማካዩ ጋቶች ፓኖም ከመረከቡ በፊት አሠልጣኙ በካሜሩኑ የአፍሪካ ዋንጫ እና ባሁኑ የቻን ውድድር ተጫዋቾቻቸው እያሳዩ ባለው ብቃት ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረው \”ለወደፊቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ግንባታ እየፈፀምን ነው።\” በማለት ሀሳባቸውን አገባደዋል።
በመጀመሪያው የሞዛምቢክ ጨዋታ ኮከብ ተብሎ የተመረጠው ጋቶች ፓኖም በበኩሉ የቻን ውድድር ከባድ መሆኑን የጠቆመበትን ንግግር አሰምቷል። \”የቻን ውድድር ከባድ ነው። በበርካታ ጨዋታዎች የአቻ ውጤቶች ይመዘገባሉ። ሁሉም ቡድኖች ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ይፈልጋሉ። በእኔ እይታ ይህ ውድድር ጥሩ ፉክክር የሚደረግበት ነው።\” ካለ በኋላ ስለዛሬው ጨዋታ ተከታዩን ብሏል።
\”እንደ ተጫዋች የዛሬው ጨዋታ ከባድ እንደሚሆን አስባለው ፤ ግን ደግሞ ወደቀጣዩ ዙር እንድናልፍ ዕድል የሚሰጠን ጨዋታ ነው። ምንም እንኳን ሊቢያ ጠንካራ እንደሆነች ብናውቅም ጨዋታውን ለማሸነፍ እና ወደቀጣዩ ዙር ለማለፍ እንጥራለን።\” በማለት ሀሳቡን ቋጭቷል።