ቻን | \”ኢትዮጵያን ለማሸነፍ ሁሉንም ነገር እንሰራለን\” ኮረንቲን ማርቲንስ

የዛሬ ምሽት የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ሊቢያ ዋና አሠልጣኝ ኮረንቲን ማርቲንስ ከጨዋታው በፊት መግለጫ ሰጥተዋል።

\"\"

የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒየንሺፕ ውድድር በአልጄሪያ እየተደረገ እንደሆነ ይታወቃል። የምድብ ሦስተኛ እና የመጨረሻ ጨዋታዎች በዛሬው ዕለት ሲጀምሩ ሀገራችን ኢትዮጵያም ከውድድሩ ገና በጊዜ መውደቋን ካረጋገጠችው ሊቢያ ጋር ወሳኝ ፍልሚያዋን ምሽት 4 ሰዓት ላይ ታከናውናለች። ከዚህ ጨዋታ በፊት አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና አማካዩ ጋቶች ፓኖም የሰጡትን ቅድመ-ጨዋታ አስተያየት ቀደም ብለን ያቀረብን ሲሆን አሁን ደግሞ የተጋጣሚያችን ሊቢያ ዋና አሠልጣኝ ኮረንቲን ማርቲንስ ስለጨዋታው የሰጡትን ሀሳብ ይዘን መጥተናል።

አሠልጣኝ ማርቲንስ \”በሁለት ምክንያቶች ውድድራችንን በጥሩ መልኩ መቋጨት እንሻለን። የመጀመሪያው ለሀገራችን እና ለባንዲራው ክብር ስንል ሲሆን ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ እግርኳሳዊ ነው። ምንም እንኳን ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፍ ባንችልም በዛሬው ጨዋታ ያለን ዕቅል ሙሉ አቅማችንን አውጥተን በመጫወት ጨዋታውን ማሸነፍ ነው። ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ሁሉም ነገር መጥፎ አልነበረም። የተወሰነ ነገር ነው ትክክል ያልሄደው።\” በማለት ከተናገረ በኋላ በዛሬው ጨዋታ ቡድኑ ድል ለማሳካት ስላለው ቁርጠኝነት ሀሳቡን አካፍለዋል።

\"\"

\”ምንም የምናጣው ነገር የለም። የሊቢያን ቁርጠኝነት ሜዳ ላይ ለማሳየት እንሞክራለን። ኢትዮጵያን ለማሸነፍ ሁሉንም ነገር እንሰራለን።\” ብሏል። አስከትሎም ብሔራዊ ቡድኑ ከውድድሩ ውጪ ስለሆነ የመጫወት ዕድል ያላገኙ ተጫዋቾችን በጨዋታው ሊጠቀሙ እንደሚችሉ የተጠየቁት ፈረንሳዊው አሠልጣኝ \”ጨዋታውን እንድናሸንፍ የሚያስችለንን ምርጡን ስብስብ በጨዋታው እጠቀማለው።\” የሚል አጠር ያለ ምላሽ ሰጥተዋል።