ቻን | ስለ ሊብያ ብሔራዊ ቡድን ጥቂት መረጃዎች

ዛሬ ምሽት 04፡00 የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን የሚገጥመው የሊቢያ ብሔራዊ ቡድንን የተመለከቱ መረጃዎች አዘጋጅተናል።

ሊቢያ በ2011 በተነሳው የአረብ አብዮት የቀድሞ አነጋጋሪው መሪዋ መዓሙር ጋዳፊን በህዝብ ዓመፅ ከጣለች በኋላ እንደ ኢኮኖሚዋ ሁሉ እግርኳሷም አሽቆልቁሏል።

ብሔራዊ ቡድኗ ከሰሜን አፍሪካ ሀገራት አንፃር ሲታይ ደካማ ብቃት በማሳየት ላይ ቢገኝም በውድድሩ ላይ ያላት የቀድመ ውጤት ግን መጥፎ የሚባል አይደለም። ሀገሪቱ በ2014 ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው የቻን ውድድር አሸናፊ ስትሆን በአጠቃላይ በውድድሩ አራት ጊዜ ተሳትፋለች ፤ የአሁኑ የአልጀርያ ውድድርም አምስተኛ ተሳትፎዋ ነው። ሊቢያ እንደ ኢትዮጵያ ብዙ በውጭ ሀገር ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች የላትም። ከዋናው ብሔራዊ ቡድኗም በጣት የሚቆጠሩ በውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾች ብቻ ነው የቀነሰችው።

\"\"

በመጀመርያው ጨዋታ በአዘጋጅዋ አልጀርያ አንድ ለባዶ ተሸንፋ ውድድሩን የጀመረችው ሊቢያ በሁለተኛው ጨዋታም በሞዛምቢክ ሦስት ለሁለት በሆነ ጠባብ ውጤት ስትሸነፍ ቡድኑ በጨዋታው መጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ግብ አስቆጥሮ መምራት ቢጀምርም በተከታታይ በተቆጠሩባቸው ግቦች ተሸንፎ ከውድድሩ ውጪ መሆኑን አረጋግጦ ወደ ዛሬው ጨዋታ ደርሷል።

የሊቢያ ብሔራዊ ቡድን በቀድሞው የኦግዜር ተጫዋች ኮረንቲን ማርቲንስ መሰልጠን ከጀመረ አስር ወራት ያስቆጠረ ሲሆን ከመጨረሻዎቹ አስራ ሦስት ጨዋታዎችም አራት (4) ድል ፣ ሰባት(7) ሽንፈት እና ሁለት (2) አቻ አስተናግዷል። ቡድኑ በተጠቀሱት አስራ ሦስት ጨዋታዎች አስራ ሰባት (17) ግቦች ያስተናገደ እና ከነዚህ ውስጥ በአስራ አንድ(11) ጨዋታዎች መረቡን ያስደፈረ ደካማ ተከላካይ ክፍል አለው። የማጥቃት ክፍሉ ግን ከተቆጠሩበት ጎሎች ባልተናነሰ ቁጥር ጥሩ የሚባል የግብ ማስቆጠር ንፃሬ አለው ፤ በዚህም በአስራ ሥስት (13) ጨዋታዎች ዘጠኝ (9) ግቦችን አስቆጥሯል።

በውድድሩ ያላት ታሪክ

በዚህ ውድድር ቤተኛ ከሆኑት ሀገራት ውስጥ የምትመደበው ሊቢያ አምስተኛ ተሳትፎ በማድረግ ላይ ትገኛለች። በ2009 በሱዳን በተካሄደው የመጀመርያው ውድድር መሳተፍ ጀምረው በ2011 ውድድር ላይ መሳተፍ ባይችሉም ዋንጫውን ባነሱበት የደቡብ አፍሪካው ውድድር ጋናን በመለያ ምት አሸንፋው ዋንጫውን አንስተዋል። ከዛ ቀጥለው በተካሄዱት የ2018 እና 2021 በውድድሮች ማጣርያውን አልፈው መታደም ችለዋል።

\"\"

የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች

በዘንድሮው የቻን አፍሪካ ዋንጫ ወቅታዊ ብቃት ሊብያ ይህ ነው የሚባል ለውጥ ፈጣሪ ወሳኝ ተጫዋች እንደሌላት ባለፉት ሁለት የምድብ ጨዋታዎች ታይቷል። ሆኖም በቡድኑ ውስጥ በ2018 የቻን ላይ ሦስት ግቦችን ያስቆጠረው የአል አህሊ ትሪፖሊው አጥቂ ሳልህ አል ታህር ተካቷል።
ከአጥቂው በተጨማሪም አማካዩ ዓሊ ረመዳን ዓሊ አል አማሚ ሌላው ተጠባቂ ተጫዋች ነው።

የሁለቱ ቡድኖች የውድድሩ የቀደመ ግንኙነት

ኢትዮጵያ እና ሊቢያ በ2014 ቻን የምድብ ጨዋታዎች ላይ አንድ ጊዜ ተገናኝተው ሊቢያ በኤልሙታሰም አቡሸናፍ እና አብዱሰላም ኦማር ግቦች ኢትዮጵያን ሁለት ለባዶ አሸንፋለች። በውድድሩ ፍፃሜ ጨዋታም ጋናን በመለያ ምት አሸንፋ ዋንጫውን ማንሳቷ ይታወሳል።