አርባምንጭ ከተማ የአጥቂውን ውል አራዝሟል

ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሶ የነበረው አህመድ ሁሴን በዛሬው ዕለት በአዞዎቹ ቤት ለተጨማሪ አንድ ዓመት ከስድስት ወራትን ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል።

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የአምናው ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁለተኛው ዙር የሊጉ ጨዋታዎች ላይ ተጠናክሮ ለመቅረብ ከቀናቶች በፊት አጥቂው አህመድ ሁሴንን በሁለት ዓመት ውል ለማስፈረም ከተጫዋቹ ጋር ድርድር በማድረግ ከስምምነት ደርሰው እንደነበር መሰማቱ ይታወሳል።

\"\"

ሆኖም የአርባምንጭ ከተማ የተጫዋቹ ውል የሚጠናቀቀው መጋቢት 6 2015 በመሆኑ ተጫዋቹ ክለቡን የመልቀቂያ ደብዳቤ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ክለቡ ውሉን ማክበር እንዳለበት ለተጫዋቹ ገልፆለት ሲደራደሩ ቆይተዋል። ከድርድራቸው በኋላም ለአንድ ዓመት ከስድሰት ወራት አብረው ለመቆየት መስማማታቸውን የክለቡ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምሩ ናሳ እና ተጫዋቹ አህመድ ለሶከር ኢትዮጵያ አሳውቀዋል።

በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ላይ ለአሰላ ከተማ በመጫወት እግር ኳስን የጀመረው አጥቂው በወልቂጤ ከተማ በከፍተኛ ሊጉ እና በፕሪምየር ሊጉ ከ2010 እስከ 2014 አጋማሽ ድረስ ቆይታ አድርጓል። በመቀጠል ባሳለፍነው ዓመት አጋማሽ ወደ አርባምንጭ አምርቶ ያለፉትን ጊዜያት የቆየ ሲሆን ውሉ መገባደዱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለመቀላቀል ከጫፍ ቢደርስም በመጨረሻም መክረሚያውን በአዞዎቹ ቤት አድርጓል።

\"\"