ጎፈሬ ከወላይታ ድቻ ጋር የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ፈፀመ

👉 \”ጎፈሬ በሀገራችን ትጥቆችን ማምረት ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ የእኛን ብቻ ሳይሆን የብዙ የሀገራችን ክለቦችን የማሊያ ችግር ቀርፏል\” አሰፋ ሆሲሶ

👉 \”ደጋፊዎች የሚያነሱትን የማሊያ ጥያቄ በተገቢው ሁኔታ ለመመለስ እንሰራለን\” አቤል ወንድወሰን

ሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ ብራንድ ጎፈሬ በሁለቱም ፆታዎች ከሚገኙ በርካታ የሀገራችን ክለቦች ጋር በትጥቅ አቅርቦት ጉዳዮች ሥራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ ይታወቃል። በዛሬው ዕለት ደግሞ በዋናው የወንዶች የሊግ ውድድር ተሳታፊ ከሆነው ወላይታ ድቻ ጋር የትጥቅ አቅርቦት እና የስፖንሰር ሺፕ ስምምነት በክለቡ መቀመጫ ከተማ ሶዶ ተፈራርሟል። በስነ-ስርዓቱም የወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ ኢሲሶ እንዲሁም የጎፈሬ ትጥቅ አምራች ተቋም ምክትል ስራ አስኪያጅ እና የሴልስ ማናጀር አቶ አቤል ወንድወሰን ተገኝተው ውሉን ፈርመዋል።

\"\"

በውል ስምምነቱ በሀገራችን ክለቦች ብዙም ያልተለመዱትን የብራንድ ትጥቆች አጠቃቀም፣ የብራንድ ምርቶች መብቶች አጠባበቀ እንዲሁም ሌሎች በርካታ የገቢ አሰባሰብ ስልጠና እና የስፖንሰርሺፕ ጉዳዮችን የተካተቱበት እንደሆነ ተገልጿል። ከፊርማው በኋላም ሁለቱ አካላት ስለስምምነቱ ተከታዩን መጠነኛ ገለፃ አድርገዋል።

በቅድሚያም አቶ አሰፋ \”ስፖርት ክለባችን በስሩ በርካታ ቡድኖች አሉት። ከዋናዎቹ የእግርኳስ እና የእጅ ኳስ ቡድኖች በተጨማሪ ከ20፣17 እና 15 ዓመት በታች ቡድኖች አሉት። ከዚህ በፊት ለእነዚህ ቡድኖቻችን የመጫወቻ እና የመለማመጃ ትጥቆችን ለማግኘት እንቸገር ነበር። መለያውን በክለቡ ቀለም የሚሰራ የሀገር ውስጥ ተቋም ባለመኖሩ ምክንያት እስከ ውጪ ድረስ እየተጓዝን እንኳን እንቸገር ነበር። አሁን ግን ጎፈሬ በሀገራችን ትጥቆችን ማምረት ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ የእኛን ብቻ ሳይሆን የብዙ የሀገራችን ክለቦችን የማሊያ ችግር ቀርፏል። በዚሁ መሰረት እኛም ከጎፈሬ ምርቶችን እየወሰድን ስንጠቀም ቆይተናል። ነገርግን አሁን ውል ገብተን ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ከጎፈሬ ጋር በህጋዊነት ለመስራት ፊርማችንን አኑረናል።\” ብለዋል።

ሥራ አስኪያጁ ጨምረው በስምምነቱ ክለቡ በጎፈሬ አማካኝነት ስፖንሰሮችን የሚያገኝበት እንዲሁም ከውጪ ሀገር ክለቦች ጋር የወዳጅነት ጨዋታዎችን የሚያደርግበት እና ገቢ የሚያሰባስብበት አማራጮች እንደተካተቱ ጠቁመዋል። በንግግራቸው ማገባደጃም ውሉ የሁለቱንም አካላት ጥቅም የሚየቀስጠብቅ እንደሆነ ገልፀው ከዚህ በኋላ የክለቡ ደጋፊዎች የማሊያ እጥረት እንደማያጋጥማቸው አመላክተዋል።

\"\"

አቶ አቤል በበኩላቸው ይህ ስምምነት በመፈፀሙ እንደ ድርጅት የተሰማቸውን ደስታ ገልፀው የስምምነቱን ፋይዳ አስረድተዋል። \”ወላይታ ድቻን የሚያክል ብዙ የደጋፊ መሰረት ካለው ክለብ ጋር እንደዚህ አይነት ስምምነት በመፈፀማችን ትልቅ ደስታ ይሰማናል። እርግጥ ጎፈሬ ከሌሎች ክለቦች ጋርም ስምምነቶችን ይፈፅማል ፤ ይሄ ግን ክለቡ ካለው የደጋፊ ብዛት መነሻነት ይህ ስምምነት ለየት ያለ ነው። ይህ ለእኛ የሚሰጠው ፋይዳ ትልቅ ነው። በክለቡ በኩልም ባለፉት ጊዜያት ሲነሱ የነበሩ የትጥቅ ችግሮችን በመቅረፉ ረገድ ያለው ፋይዳ ብዙ ነው። ከዚህም አልፎ ዛሬ የተደረገውን የወዳጅነት ጨዋታ የሚያካትት ስምምነት ስለሆነ ጥቅሙ የጎላ ነው።\” ብለዋል።

በመጨረሻም \”በሦስት ዓመቱ ውል ሰፋፊ ስራዎች እንሰራለን። በዋናነት ደጋፊዎች የሚያነሱትን የማሊያ ጥያቄ በተገቢው ሁኔታ ለመመለስ እንሰራለን። ዛሬ የተደረገው አይነት ኢንተርናሽናል የወዳጅነት ጨዋታዎችንም በማምጣት ክለቡን፣ ደጋፊውን እና ከተማውን የማነቃቃት ስራም እንሰራለን።\” በማለት ሀሳባቸውን አጋርተዋል።

የውል ስምምነቱን ማብሰሪያ ተደርጎ በሶዶ ስታዲየም የተዘጋጀው የወላይታ ድቻ እና የዩጋንዳው ክለብ ብላክ ስታርስ የወዳጅነት ጨዋታ በተጋባዡ ቡድን 3ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል።