\”እንደተወራው ፌዴሬሽኑ ያላዋቂዎች እና የሰነፎች ጥርቅም አይደለም\” ባህሩ ጥላሁን

ዋልያዎቹ በቻን ውድድር የማሊያ ችግር አጋጥሟቸዋል ተብሎ ስለተሰራጨው ወሬ የፌዴሬሽኑ የጽህፈት ቤት ሀላፊ ምላሽ ሰጥተዋል።

በ7ኛው የአፍሪካ ሀገራት ሻምፒዮንሺፕ ውድድር ላይ የተሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከምድቡ አንድ ነጥብ በመያዝ መሰናበቱ የሚታወስ ነው። የቡድኑ አባላት በሦስት ዙር ከቀናት በፊት ወደ ሀገር ቤት ከገቡ በኋላ ስለውድድሩ ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ እና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን መግለጫ እየሰጡ ይገኛሉ። ዋና ፀሀፊው አቶ ባህሩ ከውድድሩ ጋር በተገናኘ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ገለፃ አድርገዋል።

\"\"

በቅድሚያ ብሔራዊ ቡድኑ ወደ ሞሮኮ አምርቶ ተዘጋጅቶ ሁለት የልምምድ ጨዋታዎችን ያደረገው በአልጄሪያ ያለው ወቅታዊ የዐየር ሁኔታ ተጠንቶ እንደሆነ ጠቁመዋል። ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ከምድብ ይወድቃል በሚል ጨለምተኛ ምክንያት ወደ ሀገር ቤት መመለሻው ትኬት በጊዜ አለመቆረጡን ጠቅሰው ቡድኑ ከምድብ ከወደቀ በኋላ ግን ትኬት ለማግኘት እንዳልተቻለ ገልፀው ልዑካን ቡድኑን በአስገዳጅ ሁኔታ በሦስት ዙር እንዲመጣ እንደተደረገ አመላክተዋል።

አቶ ባህሩ አስከትለው ብሔራዊ ቡድኑ በውድድሩ ወቅት የመለያ እጥረት አጋጥሞት ነበር ስለመባሉ \”ብሔራዊ ቡድኑ ከሞሮኮ ተነስቶ ወደ አልጀርስ ሲሄድ የትራንዚት ቆይታ ስለነበረው ሻንጣዎች ካዛብላንካ ላይ ነው የተጫኑት ፤ ሻንጣዎቹ የሚጠበቁት ደግሞ አልጀርስ ነው። በዚህ ሂደት የአራት ተጫዋቾች ሻንጣ እና ቡድኑ ከያዘው ማቴሪያል መካከል አንድ ሻንጣ በትራንዚት ምክንያት አልመጣም። ይሄ ተለዋጭ ማሊያ ነው። እንደተወራው ፌዴሬሽኑ ያላዋቂዎች እና የሰነፎች ጥርቅም አይደለም። ቢያንስ ሎጂካል ሆነን ብንነጋገር ጥሩ ነበር። ይህ የተፈጠረው በትራንዚት ምክንያት ነው። ግን ቡድኑ ማሊያውን አርጎ ሲጫወት ነበር።\” ብለዋል።

\"\"

አቶ ባህሩ አያይዘው በተመዘገበው ውጤት እንደ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዳዘኑ አመላክተዋል።