የወልዲያ ስታዲየም ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ይገኛል ?

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው ግጭት ውድመት ያጋጠመው የወልዲያ ስታዲየም ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል ስንል ቀጣዩን ጽሁፍ አሰናድተናል።

\"\"

ለግንባታ 1 ቢሊዮን ብር የፈሰሰበት እና የወልዲያ ከተማ ተወላጅ በሆኑት ሼህ መሐመድ ሁሴን ዓሊ አላሙዲን የተገነባው የወልዲያ ስታዲየም ቀሪዎቹ የሆቴል ፣ ውሃ ዋና ፣ ሁለገብ ሥፍራው ( መረብ ኳስ ፣ እጅ ኳስን እና ቅርጫት ኳስ ሜዳዎች) እና የግቢው ድንጋይ ንጣፍ በሕዝብ ርብርብ እና በክልሉ መንግሥት የ50 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መጠናቀቁ ይታወቃል። ሆኖም 2013 ላይ በካፍ የቴክኒክ ቡድን አባላት ተገምግሞ ዓለም አቀፋዊ ውድድሮችን ለማስናገድ ፍቃድ በሚጠብቅበት ሰዓት በተጀመረው የሰላም ማስከበር ሂደት ወልዲያ ከተማ ላይ የተዘጋጀ የሠራዊት ካምፕ ባለመኖሩ ሠራዊቱ ወልዲያ ስታዲየም ላይ እንዲሰፍር ተደርጓል።

በኢንተርፕራይዙ ሥር 71 ሠራተኞችን የያዘው እና 32 የመኝታ ክፍሎች ያሉት ስታዲየሙ የ2013 የከፍተኛ ሊግ ውድድርን ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ እንደነበር እና ቦታው የጦርነት ቀጠና ነው በሚል ውድድሩ ወደ ዝዋይ መወሰዱም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ይሁን እና በሰሜኑ ክፍል የተከሰተው የሀገራችን ቀውስ በትር ያረፈበት ስታዲየሙ 177 ሚሊዮን ብር የሚገመት ንብረት ወድሞበታል።

ስታዲየሙ የተዘጋውን ሆቴል ጨምሮ ለመከላከያ ሠራዊት በነፃ ያቀረበው አገልግሎት በገንዘብ ቢተመን 145 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሲሆን እስካሁን መልሶ ለማቋቋም ምንም ዓይነት ፍላጎት ያሳየ ተቋም አለመኖሩን ፣ የክልሉ መንግሥት ለሠራተኞቹ ደመወዝ ብቻ መክፈሉ ፣ ለፅዳት እና ለቢሮ ቁሳቁስ የገንዘብ ድጋፍ ተጠይቆ ሌሎች የመንግሥት ተቋማት ሲደጋገፉ ለወልዲያ ስታዲየም ምንም ዓይነት የቁሳቁስ እና የገንዘብ ድጋፍ አልተደረገለትም።  የክልሉ ስፖርት እና ወጣቶች ቢሮም ሀሣቡ እንዳለ ሆኖ እንደ  ባህርዳር ስታዲየም ትኩረት መስጠቱ ላይ ክፍተት ይታይበታል ሲሉ የስታዲየሙ ሥራ አስኪያጅ አቶ ይመር አበባው ገልፀዋል።

ሜዳው ውስጥ ጉዳት ከደረሰባቸው ክፍሎች አንዱ የሆነው የመጫወቻ ሣሩ ጥልቅ የውሃ ጉድጓዱ በመዘረፉ ምክንያት ሙሉ በሙሉ ሲደርቅ ከከተማ አስተዳደሩ ውሃ ለማምጣት ቢሞከርም በስታዲሙ ዙሪያ ያሉ 10 ባለ 10ሺህ ሊትር የውሃ ማጠራቀሚያዎች ሲስተም የሚያንቀሳቅሰው ንብረትም ውድመት ደርሶበታል። በዚህ ሰዓት ግን መከላከያ ሠራዊቱ ስታዲየሙን እንዲለቅ በመጠየቁ ከ አንድ መቶ የማይበልጡ የመከላከያ ሠራዊት እና ሎጅስቲኮች ብቻ የቀሩ ሲሆን \”ስታዲየሙ  ይህ ሁሉ ወድመት ቢደርስበትም  ከፍተኛ ሊጉን ማስተናገድ የሚያስችል አቅም አለው\” ሲሉ አቶ ይመር አበባው ይናገራሉ።

\"\"

ሥራ አስኪያጁ ስታዲየሙን ወደ ነበረበት ለመመለስ እጅግ ከባድ ቢሆንም የፅዳት ሥራዎችን በቶሎ አጠናቅቆ የሀገር ውስጥ ውድድሮችን ለማዘጋጀት ብቁ ከመሆኑ በተጨማሪ በጦርነት ሥነልቦና ጉዳት የደረሰበትን እግርኳስ ወዳዱ ማኅበረሰብ ለማነቃቃትም ሁነኛ መሳሪያ እንደሆነ ጠቁመዋል።

አቶ ይመር አበባው አክለውም በዚህ ሳምንት በስታዲየሙ አስተዳደር ሥር ያሉ የፅዳት እና የጉልበት ሠራተኞችን በመያዝ ስታዲየሙ የያዛቸውን 280 ሽንት ቤቶችን በማፅዳት ሥራ ለመጀመር መታሰቡን እና ስታዲየሙ ለሀገር ውስጥ ውድድሮች ብቁ መሆኑን ለክልሉ ወጣት እና ስፖርት ቢሮ እና ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ማሳወቃቸውንም አስረድተዋል።