የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ በ11 ጨዋታዎች ቀጥሎ ሲካሄድ 8 ጎሎች በመጨረሻ ደቂቃ ተቆጥረዋል።
በቶማስ ቦጋለ ፣ ጫላ አቤ እና ተመስገን ብዙዓለም
የጠዋት ጨዋታዎች
ባህርዳር ላይ በምድብ \’ሀ\’ የሳምንቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ጅማ አባ ቡናን ከወልዲያ አገናኝቷል። መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ይቸገሩ እንጂ ተደጋጋሚ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ ተስተውሏል። ወልዲያዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመድረስ የተሻሉ የነበሩ ሲሆን 19ኛው ደቂቃ ላይ መጣባቸው ሙሉ ተከላካዮችን ቀምቶ ወደ ሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት በመግባት ለበድሩ ኑርሁሴን ሲያቀብል በድሩ ኳሱን ሳያገኘው ቀርቶ ትልቅ የግብ ዕድል አባክነዋል። 31ኛው ደቂቃ ላይም ቢንያም ላንቃሞ ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ላይ ተከላካይ አታልሎ በማለፍ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው ሌሊሣ ታዬ መልሶበታል። በጥሩ የኳስ ቅብብል መኃል ሜዳው ላይ ብልጫውን እየወሰዱ የመጡት ጅማ አባ ቡናዎች ብዙዓየሁ እንዳሻው ከቅጣት ምት ካደረገው ፈታኝ ያልሆነ ሙከራ ውጪ በአጋማሹ የተሻለ የግብ ዕድል ለመፍጠር ተቸግረዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ጅማ አባ ቡናዎች ዳኝነት ላይ በሚያነሱት ጥያቄ በውጥረት ታጅቦ ሲቀጥል 50ኛው ደቂቃ ላይም ጅማዎች ሁለት የፍጹም ቅጣት ምት ተከልክለናል በሚል ክስ ለማስመዝገብ ጨዋታውን ከአምስት ላላነሱ ደቂቃዎች ያህል አቋርጠውታል። እንደ ምሳሌ ይህ ጨዋታ ተጠቀሰ እንጂ በተደጋጋሚ በብዙ ክለቦች የሚታየው ጨዋታ አቋርጦ ክስ ለማስመዝገብ የመፈለግ ሂደትም የሊጉን ደረጃ እጅግ የሚያወርድ እና ለተመልካችም እጅግ አሰልቺ የሆነ ጉዳይ ስለሆነ በጊዜ መታረም ያለበት ጉዳይ ሆኖ አግኝተነዋል።
75ኛው ደቂቃ ላይም የአባ ቡናው የመስመር ተከላካይ አካሉ አበራ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ በቁጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም ያልተበገሩት ጅማዎች 87ኛው ደቂቃ ላይ በአጋማሹ የተሻለውን የመጀመሪያ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ እስጢፋኖስ ተማም በግሩም ሁኔታ ገፍቶ በወሰደው ኳስ ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው ቴዎድሮስ ጌትነት በእግሩ መልሶበታል። ያንኑ ኳስ በመልሶ ማጥቃት ወልዲያዎች በቶሎ በረጅም ኳስ ባስጀመሩበት ሂደት ኳሱን ያገኘው ግብጠባቂው ሌሊሣ ታዬ ለማቀበል ሲሞክር በሠራው ስህተት ኳሱን አቋርጦ ያገኘው ኃይሌ ጌታሁን ሳይጠቀምበት ቀርቶ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። 90ኛው ደቂቃ ላይም የጅማው ዘላለም አበበ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ያገኘው ሮሆቦት ሰላሎ በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው ቴዎድሮስ ጌትነት እና የግቡ የቀኝ ቋሚ ግብ ከመሆን አግደውታል። ያንኑ ኳስ ወልዲያዎች በተመሳሳይ ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ሲወስዱት ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ የተገናኘው ኃይሌ ጌታሁን በድጋሚ ሳይጠቀምበት ቀርቶ ተጨማሪ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል።
ምድብ \’ለ\’ ጅማ ላይ አምቦ እና ይርጋ ጨፌ ቡናን በማገናኘት ተጀምሯል። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱ ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ሲያደረጉ ቀስ በቀስ ግን አምቦዎች የተሻለ ለማድረግ ሲጥሩ ታይቷል። በዚህም በብሩክ ቸርነት፣ሀይሌ ክፍሌ እና ሳዲቂ አክመ አማካኝነት የግብ ሙከራዎች ሲያደርጉ ይርጋ ጨፌዎች ደግሞ በመልሶ ማጥቃት በተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውሏል። ይህ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቶም በ23ኛው ደቂቃ አቤነዘር ከፍያለው ጎል አስቆጥሮ መሪ መሆን ቢችሉም አምቦዎች በአጋማሹ ጭማሪ ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት አማካኝነት ብሩክ ቸርነት ግብ አስቆጥረው የመጀመሪያ አጋማሽ በአንድ አቻ ተጠናቋል።
በሁለተኛ አጋማሽ ጨዋታው በእንቅስቃሴ ረገድ ብዙ ለውጥ ያልታየበት ቢሆንም ገና በጅምሩ በ53ኛው ደቂቃ ይርጋ ጨፌዎች በስዩም ደስታ አማካኝነት መሪ ሆነዋል። በአንፃሩ አምቦዎች ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ የተሻሉ በመሆን በተደጋጋሚ የጎል ሙከራ ለማድረግ ቢጥሩም ጎል ማስቆጠር አልቻሉም። ይርጋ ጨፌዎች በ90ኛው ደቂቃ ላይ ስዩም ደስታ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሶስተኛ ጎል በፍፁም ቅጣት ምት አማካኝነት በማስቆጠር የተደላደለ ውጤት ይዘዋል። አምቦዎች በተጨማሪው ደቂቃ ላይ ያገኙትን ቅጣት ምት በነብዩ ንጉሴ ድንቅ ምት ሁለተኛውን ጎል ማስቆጠር ቢችሉም ከጨዋታው ነጥብ ማግኘት አልቻሉም።
ሆሳዕና ላይ በተደረገው የመጀመርያ ጨዋታ ሶዶ ከተማ እና ቡራዩ ከተማ ሲገናኙ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ሙሉ የውድድሩ አባል አካላት በጋራ በመሆን ውድድር የሚካሄድበትን የመጫወቻ ሜዳ የማፅዳት ዘመቻ በማከናወን ዕለቱን ጀምረዋል።
በጨዋተው የመጀመሪያ አጋማሽ ጥሩ እንቅስቃሴ ተስተውሏል። እንደተጀመረ በ3ኛ ደቂቃ ሶዶ ከተማዎች ያገኙትን ግልፅ የግብ ዕድል በመዘናጋት ሳይጠቀሙት ቀርተዋል። ሆኖም በ16ኛው ደቂቃ በተመሳሳይ የግብ ዕድል አላዛር ፋሲካ ግብ በማስቆጠር ሶዶ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሶዶ ከተማ የግብ ክልል ውስጥ የቡራዩ ከተማ ተጫዋች ላይ ጥፋት በመሰራቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ሲሳይ ዋጆ በማስቆጠር ቡራዩ ከተማን አቻ ማድረግ ችሏል።
ሁለተኛው አጋማሽ የሶዶ ከተማ መጠነኛ የበላይነት የታየበት አጋማሽ ሲሆን በ65ኛው ደቂቃ የሶዶ ከተማ የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች የሆነው ታምራት ታደሰ ከርቀት አክርሮ የመታትን ኳስ ወደ ግብ በመቀየር ሶዶ ከተማን ድጋሚ መሪ አድርጓል። ጨዋታው በዚህ ሁኔታ የሄደ ሲሆን መደበኛው የጨዋታ ሰዓት ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩ ቡራዩ ከተማዎች በድጋሚ ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ሲሳይ ዋጆ በማስቆጠር ቡድኑን ከሽንፈት መታደግ ችሏል። ጨዋታውም በአቻ ውጤት ተጠናቋል።
የ05፡00 ጨዋታዎች
በምድብ \’ሀ\’ ባህርዳር ላይ ባቱ ከተማን ከ ቤንች ማጂ ቡና ሲያገናኝ ብርቱ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም በኩል ማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲታይበት የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ቤንች ማጂዎች የተሻሉ ነበሩ። 5ኛው ደቂቃ ላይ ዘላለም በየነ ከሳጥን አጠገብ በሞከረውና በግቡ የግራ ቋሚ ለጥቂት በወጣበት ኳስ የመጀመሪያውን የተሻለ ሙከራ ያደረጉት አቦሎቹ 15ኛው ደቂቃ ላይም ኤፍሬም ታምሩ በድንቅ ሩጫ ወደ ሳጥን ይዞት በገባውና በተከላካዮች ተጨርፎ በወጣበት ኳስም ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለዋል።
በጥሩ የኳስ ቅብብል ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት የሚሞክሩት ባቱዎች 29ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። ሰይድ ሰጠኝ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ዘላለም በየነ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው በረከት በሽር በግሩም ፍጥነት አግዶበታል። ያንኑ ኳስ ብሩክ ወልዱ በግራ መስመር ከማዕዘን ሲያሻማ ያገኘው ኤፍሬም ታምሩ በግንባሩ በመግጨት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው በረከት በድጋሚ መልሶበታል። እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር ፈታኝ ሙከራ ለማድረግ የተቸገሩት አሳዎቹ የተሻለውን ሙከራ 33ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። ኢዩኤል ሳሙኤል ገፍቶ በወሰደው ኳስ ግሩም ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው መስፍን ሙዜ እና የግቡ የቀኝ ቋሚ ግብ ከመሆን አግደውታል።
ከዕረፍት መልስ ባቱዎች እጅግ ተሻሽለው ሲቀርቡ 69ኛው ደቂቃ ላይም በተመስገን ቃበቶ ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን በመውሰድ ጨዋታውን የተቆጣጠሩ ይመስሉ የነበሩት አሳዎቹ በጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይ ግን ትኩረታቸውን እያጡ በመምጣት ያልታሰበ የጨዋታ ሂደት አጋጥሟቸዋል።
ቤንች ማጂዎችም 91ኛው እና 93ኛው ደቂቃ ላይ በእንዳለማው ድክሬ እና ሀሰን ሁሴን ግቦች ከነበራቸው እንቅስቃሴ አንጻር ያልተጠበቀ እጅግ ጣፋጭ ድል ሲያስመዘግቡ ተቀይረው ወደ ሜዳ የገቡት ረጀብ ሚፍታሕ እና ጅብሪል ናስርም ግብ ለሆኑ ኳሶች ቁልፍ መነሻ በመሆን ለድሉ መገኘት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል። ጨዋታውም በቤንች ማጂ ቡና 2-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም አቦሎቹ ነጥባቸውን 27 በማድረስ ነገ ከሚጫወተው የምድቡ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር በእኩል ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በምድብ \’ለ\’ ሁለተኛ ጨዋታ ቦዲቲ እና ደብረ ብርሃን ተጫውተዋል። ጨዋታው በተጀመረ 3ኛ ደቂቃ ደብረ ብርሃን በሀብታሙ ረጋሳ ጎል መሪ መሆን ችሏል። ጎል ከተቆጠረ በኋላ ቡድኖቹ ቀዝቀዝ ያለ ጨዋታ ያሳዩን ሲሆን በአንፃራዊነት ቦዲቲዎች የኳስ ቁጥጥር ላይ ብልጫ በመውሰድ የጎል ሙከራዎች ማድረግ ቢችሉም ጎል ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል የመጀመሪያ አጋማሽ በደብረ ብርሃን መሪነት ተጠናቋል።
በሁለተኛ አጋማሽ ቡድኖቹ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ እንቅስቃሴያቸው ለሃያ አምስት ደቂቃዎች ለተመልካች ብዙ አዝናኝ አልነበረም። በተቀሩት ደቂቃዎች ቦዲቲዎች የአቻነቷን ጎል ለማስቆጠር በተሻለ የኳስ ቁጥጥር እንዲሁም የተሻሉ የጎል ሙከራዎች ሲያደርጉ ደብረ ብርሃኖች ግን የሚሰነዘሩ ሙከራዎችን ሲያመክኑ ነበር። በዚህም በመከላከል ውጤት አስጠብቀው በመውጣት ጨዋታውን ረተዋል።
በምድብ \’ሀ\’ ባህር ዳር ላይ ሰበታ ከተማ እና ዱራሜ ከተማ ሲገናኙ በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢታይበትም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቁጥር በዝቶ በመድረሱ እና የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ዱራሜዎች የተሻሉ ነበሩ። 21ኛው ደቂቃ ላይም ዳግም ደሳለኝ በግሩም ሁኔታ ተከላካይ አታልሎ በማለፍ ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው ሚሊዮን ሰለሞን ይዞበታል። በተረጋጋ የኳስ ቅብብል አልፎ አልፎ የግብ ዕድል ለመፍጠር የሚሞክሩት ሰበታዎችም በ ሰላሙ አለፈ ጥሩ ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር። በቁጥር በዝተው እንደሚያደርጉት የማጥቃት እንቅስቃሴ በርካታ የጠሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር የነበረባቸው ዱራሜዎች 35ኛው ደቂቃ ላይ በዳግም ደሳለኝ ጥሩ ሙከራ ሲያደርጉ የአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃ ላይም ኪሩቤል ካሳ ጥሩ ሙከራ አድርጎ የግቡን የቀኝ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል 61ኛው ደቂቃ ላይ የዱራሜው አለኝታ ማርቆስ ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው ሚሊዮን መልሶበታል። ቀስ በቀስ ጨዋታውን እየተቆጣጠሩ የመጡት ሰበታዎች 66ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ የነበረው ኪዳኔ አሰፋ ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው ማፑቱ ይስሃቅ ሲመልስበት ኳሱን ያገኘው ቦጃ ኢዴቻ አክርሮ በመምታት በጥሩ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። ዱራሜዎች ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች ባለመጠቀማቸው ቁጭት ውስጥ በመግባት ለመረጋጋት ሲቸገሩ 85ኛው ደቂቃ ላይም ወንዱ ፍሬው በግንባሩ በመግጨት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው ሲመልስበት የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ እጅግ ንጹህ የግብ ዕድል ፈጥረውም በግቡ ቋሚ እና በዕለቱ ኮከብ በነበረው የሰበታ ከተማ ግብጠባቂ ሚሊዮን ሰለሞን መክኖባቸዋል። ጨዋታውም በሰበታ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ነቀምት እና ከንባታ ሺንሽቾን ባገናኘው እና ብዙም ማራኪ ባልነበረው የምድብ \’ለ\’ ጨዋታ ግብ የተስተናገደው በ8ኛው ደቂቃ ነው። በተጠቀሰው ደቂቃም ነቀምት በዳንኤል ዳዊት አማካኝነት ግብ አስቆጥሯል። ከንባታ ሺንሽቾዎች አብዛኛውን ከኳስ ጋር ያላቸው ጊዜ በራሳቸው ሜዳ ሲያደርጉ ነቀምቶች ደግሞ በላይኛው ሜዳ የተጫዋች ቁጥር በማብዛት ተከላካዮች የሚሰሩትን ስህተት በመጠቀም ተጨማሪ ሙከራዎች ለማድረግ ሞክረዋል።
በሁለተኛ አጋማሽ ነቀምቶች የበለጠ ተሽለው የቀረቡ ሲሆን በ54ኛው ደቂቃም በተመስገን ዲባ አማካኝነት ሁለተኛ ጎል አስቆጥረዋል። ጎል ማስቀጠር ከቻሉ በኋላ ኳሱን በመቆጣጠር የበላይነቱን ሲወስዱ በተደጋጋሚ የጎል ሙከራም ማድረግ ችለዋል። ከንባታ ሺንሽቾዎች ደካማ እንቅሰቃሴ የታየባቸው ሲሆን ኳስ ለመጫወትም በመልሶ ማጥቃት ጎል ለማግባትም ሲንቀሳቀሱ አልተመለከትንም። በደካማ እንቅስቃሴም በጨዋታው እጅ ሰጥተው ወጥተዋል።
ጅማ አባ ጅፋር እና ስልጤ ወራቤ በምድብ ሐ ከምሳ በኋላ ተገናኝተዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ሚዛናዊ የሆነና በሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ጥሩ የግብ ሙከራዎች ሲያደርጉ ተስተውሏል። በፃዲቅ ሲቾ የሚመራው ስልጢ ወራቤ የተሻለ የኳስ ቁጥጥር በመያዝ እና ወደ ግብ በመድረስ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በአንፃሩ ጅማ አባ ጅፋሮች በመልሶ ማጥቃት ጥሩ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ተስተውሏል። በ39ኛው ደቂቃ የጅማ አባጅፋሩ ተከላካይ ልመንህ ታደሰ ላይ በደረሰ ከፍተኛ የጭንቅላት ጉዳት ደርሶበት ከሜዳ መውጣት ችሏል። አጋማሹም ያለ ግብ ተጠናቆ ወደ መልበሻ ክፍል አቅንተዋል።
ሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ተመሳሳይ አጨዋወት ያየን ሲሆን ስልጢ ወራቤ ኳስን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረው በሙሉ የበላይነት ተጫውቷል። ጅማ አባ ጅፋሮች የገኙትን የመልሶ ማጥቃት ወደ መሰመር በመውሰድ በአየር ኳስ ለመጠቀም ሲሞክሩ ተስተውሏል። ጨዋታውም ምንም ግብ ሳይቆጠር በአቻ ውጤት ተጠናቆ ነጥብ ተጋርተዋል።
የ10፡00 ጨዋታዎች
ባህርዳር ላይ በምድብ \’ሀ\’ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የወሎ ኮምቦልቻ እና የቡታጅራ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ ብርቱ ፉክክር ቢያስተናግድም የግብ ዕድሎች ግን ያልተፈጠሩበት ነበር። 36ኛው ደቂቃ ላይ የወሎው ሰለሞን ጌዲዮን ከ ግብጠባቂው ከፍ አድርጎ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ብሩክ ዋኮ በፍጥነት ደርሶ በግንባሩ በመግጨት አስወጥቶታል። ይህም በአጋማሹ የተፈጠረ የተሻለው የግብ ዕድል ነበር።
ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀጥል 48ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂያቸውን ክንዴ አብቹን በቀይ ካርድ ያጡት ቡታጅራዎች ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ወደ ራሳቸው የግብ ክልል ተጠግተው አሳልፈዋል። 50ኛው ደቂቃ ላይም የቡታጅራው ግብጠባቂ ምንተስኖት የግሌ በሠራው ስህተት ኳሱን ያገኘው ሰለሞን ጌዲዮን ሳይጠቀምበት ቀርቶ ትልቅ የግብ ዕድል አባክኗል። ኮምቦልቻዎች የቁጥር ብልጫውን ተጠቅመው ተጭነው በመጫወት በርካታ የግብ ዕድሎችን ፈጥረዋል። በተለይም 87ኛው ደቂቃ ላይ መሐሪ ዮሴፍ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው ምንተስኖት የግሌ አስወጥቶበታል። ቀስ በቀስ እየተዳከሙ የመጡት ቡታጅራዎች ጥሩ የኳስ ቅብብል ቢያደርጉም የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ተስፋ ባለመቁረጥ በተደጋጋሚ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉት ወሎ ኮምቦልቻዎች ተሳክቶላቸው 96ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው የሱፍ መሐመድ ባስቆጠራት ግብ ጨዋታውን 1-0 ማሸነፍ ችለዋል።
በምድብ ለ የዕለቱ የመጨረሻ ጨዋታ ንብ እና አዲስ አበባ ከተማ ተገናኝተዋል። ክከዕረፍት በፊት ሁለቱም ቡድኖች ለማሸነፍ ያላቸው ፍላጎት የተለየ ስሜት ሲነበብባቸው ከኳስ ቁጥጥር ይልቅ ቶሎ ቶሎ ኳስ የመነጣጠቅ እንቅስቃሴ ሲታይባቸው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ግን ማድረግ አልቻሉም።
በሁለተኛው አጋማሽም የቡድኖቹ የመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ጎልቶ ሲታይ ከመጀመሪያው በተሻለ ለተመልካች ሳቢ ፉክልር ታይቷል። ጨዋታው በዚሁ ቀጥሎ ያለግብ ሊጠናቀቅ ሲቃረብ በጭማሪ ደቂቃ
በንብ ግብ ጠባቂ ስህተት መነሻነት ከማል ሀጂ ለአዲስ አበባዎች ብቸኛውን ግብ በማስቆጠር የቡድን አጋሮቹን ማስፈንጠዝ ችሏል ፤ ጨዋታውም በአዲስ አ በባ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ምድብ \’ሐ\’ ኮልፌ ክ/ከተማ እና ኦሜድላን ባገናኘው ጨዋታ ነበር ዕለቱን ያጠናቀቀው። የጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ በኮልፌ ክ/ከተማ የበላይነት የታየበት እና በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ በግብ ሙከራም የተሻሉ የነበሩበት ነበር። ኦሜድላዎች ሙሉ በሙሉ በማፈግፈግ ግብ እዳይቆጠርባቸው የጣሩ ሲሆን ጥረታቸውም ተሳክቶ ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል ።
ሁለተኛው አጋማሽ ተመሳሳይ አጨዋወት የነበረ ሲሆን ኦሜድላዎች በመልሶ ማጥቃቱ የተሻሉ ሆነው በመግባታቸው ጨዋታው ውበትን ተላብሶ ታይቷል። ጨዋታው በተመጣጣኝ ሁኔታ እየቀጠለ በ76ኛው ደቂቃ እንዳልካቸው ጥበቡ የተገኘውን የመልሶ ማጥቃት የግብ እድል ወደ ግብ በመቀየር ኦሜድላን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ኮልፌ ክ/ከተማዎች ኋላቸውን ከፍተው ሙሉ በሙሉ በማጥቃት ላይ ሳሉ በ90ኛው ደቂቃ ኦሜድላዎች ተጨማሪ ግብ በማስቆጠር አሸናፊነታቸውን አረጋግጠዋል።