የሊጉ ክለቦች አዲስ ያስፈረሟቸውን ተጫዋቾች መቼ መጠቀም ይችላሉ?

ከታኅሣሥ 18 እስከ ጥር 18 በቆየው የሁለተኛ ዙር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ተሳትፎ ያደረጉ ክለቦች አዳዲሶቹን ተጫዋቾቻቸው መቼ መጠቀም ይጀምራሉ?

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቻን ተሳትፎ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከነገ በስትያ አዳማ ላይ ጅማሮውን ያደርጋል። ሊጉ በተጠቀሰው ምክንያት ሲቋረጥ አክሲዮን ማኅበሩ እና እግርኳስ ፌዴሬሽኑ የሁለተኛው ዙር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከታኅሣሥ 18 ጀምሮ ለአንድ ወር እንደሚቆይ የገለፁ ሲሆን በመስኮቱም ፋሲል ከነማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ፣ አርባምንጭ ከተማ እና ሲዳማ ቡና አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርመዋል።

\"\"

ታዲያ ከላይ የተጠቀሱት ክለቦች አዳዲስ ያስፈረሟቸውን ተጫዋቾች ቅዳሜ እና እሁድ በሚደረጉት ተስተካካይ ጨዋታዎች እንዲሁም የመጀመሪያው ዙር ውድድር አካል በሆኑት የአስራ አራተኛ እና አስራ አምስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች መጠቀም አይችሉም። ይህንን ተከትሎ ሰባት ተጫዋቾችን በማስፈረም በዝውውሩ የነቃ ተሳትፎ ያደረጉት ለገጣፎ ለገዳዲ የካቲት 17 ከሀዋሳ ከተማ ጋር እንዲሁም በተመሳሳይ ሰባት ተጫዋቾችን የግሉ ያደረገው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከሁለት ቀን በኋላ የካቲት 19 ከባህር ዳር ከተማ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ አዲሶቹን ተጫዋቾች መጠቀም እንደሚችሉ ተጠቁሟል።

\"\"

ሁለት ሁለት ተጫዋቾችን ያስፈረሙት አርባምንጭ ከተማ የካቲት 16 ከወልቂጤ ከተማ፣ ሲዳማ ቡና የካቲት 18 ከድሬዳዋ ከተማ እንዲሁም ፋሲል ከነማ የካቲት 19 ከአዳማ ከተማ ጋር ሲጫወቱ አዲስ የፈረሙ ተጫዋቾቻቸውን በህጋዊነት ሜዳ ላይ ማሰለፍ ይችላሉ።