ከፍተኛ ሊግ | የ13ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ዛሬ 9 ጨዋታዎችን አስተናግዶ የመጀመሪያው ዙር ውድድር ተጠናቋል።

በቶማስ ቦጋለ ፣ ጫላ አቤ እና ተመስገን ብዙዓለም

የ04፡00 ጨዋታዎች

ባህርዳር ላይ በምድብ \’ሀ\’ ሀላባ ከተማ እና አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ ተገናኝተዋል። መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻሉ የነበሩት አቃቂዎች በቀኙ የማጥቃት መስመራቸው በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርሱ በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራም በኪሩቤል ይጥና የቅጣት ምት ኳስ አድርገዋል። ቀስ በቀስ በማራኪ ቅብብል ጨዋታውን እየተቆጣጠሩ የመጡት ሀላባዎች መኃል ሜዳው ላይ ብልጫ ቢወስዱም የጠሩ የግብ ዕድሎችን ግን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው ተሻሽሎ ሲቀጥል የጨዋታው የበላይነት በየ ጥቂት ደቂቃዎች በሁለቱም ቡድኖች ሲፈራረቅ ቆይቷል። 51ኛው ደቂቃ ላይም አቡሽ ደርቤ በግራ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ቢሞክርም ግብጠባቂው ቢንያም ሀብታሙ አስወጥቶበታል። አቃቂዎችም በበኩላቸው 77ኛው ደቂቃ ላይ በእሸቱ ጌታሁን ጥሩ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ 81ኛው ደቂቃ ላይ ፉዐድ ጀማል ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ ግብጠባቂው ደግነት ደቆሮ ይዞበታል። ክፍት በነበረው ጨዋታ ሁለቱም ቡድኖች ለማሸነፍ ባላቸው ብርቱ ፍላጎት ታጅቦ ሲቀጥል 87ኛው ደቂቃ ላይ የሀላባው ሙሉቀን ተሾመ ከግራ መስመር ያደረገው ሙከራ የግቡን የላዩ አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ጨዋታውም ያለግብ ተጠናቋል።

ጅማ ላይ ካፋ ቡና እና እንጅባራ ከተማ ሲገናኙ በመጀመሪያው አጋማሽ ከፋ ቡናዎች በመከላከል አጨዋወት በመንቀሳቀስ የግብ ዕድሎችን በመልሶ ማጥቃት ለመፍጠር ቢሞክሩም ያን ያህል አልተሳካላቸውም። በተቃራኒው እንጅባራዎች የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን ወደ ራሳቸው በማድረግ በቅብብል የግብ ማግባት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሲጥሩ ታይቷል። በ42ኛው ደቂቃም በአበበ ታደሰ አማካኝነት በተቆጠረ የፍፁም ቅጣት ምት መሪ የሆኑበትን ግብ አግኝተዋል። ግብ የተቆጠረባቸው ከፋ ቡናዎች ይባስ ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ የመስመር ተከላካያቸው የሆነውን ዘነበ ከበደ በቀይ ካርድ አተው በሁለተኛው አጋማሽ በቁጥር አንሰው ለመጫወት ተገደዋል።

የሚመሩት ከፋ ቡናዎች የቁጥር ብልጫ ቢወሰድባቸውም ተጨማሪ ግብ ላለማስተናገድ እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት ወደ ጨዋታው የሚመለሱበትን ግብ ፍለጋ ተንቀሳቅሰዋል። የሚፈልጉትን ያገኙት እንጅባራዎች በበኩላቸው እንደ መጀመሪያው አጋማሽ ከኳስ ጋር ጊዜ በማሳለፍ በእጃቸው የገባውን ውጤት አስጠብቀው በመውጣት ጨዋታውን ረተዋል።

\"\"

ሆሳዕና ላይ ነገሌ አርሲ እና ሮቤ ከተማ በጎሎች የታጀበ ጨዋታ አድርገዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ አጨዋወት የተመለከትንበት እና የነጌሌ አርሲ የበላይነት የታየበት ሲሆን ቡድኑ የበላይነቱንም በግብ በማጀብ አሳይቷል። የመጀመሪያ ግብ እስክንመለከት ድረስ በሁለቱም በኩል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የነበረ ሲሆን በ29ኛው ደቂቃ ያሬድ መሐመድ ግብ በማስቆጠር ነጌሌ አርሲን መሪ ማድረግ ችሏል። የግቧ መቆጠር በኋላ የነጌሌ አርሲ ሙሉ በሙሉ የበላይነት ታይቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ያሬድ መሐመድ በድጋሚ ግብ በማስቆጠር ነጌሌ አርሲ እየመራ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽም በአብዛኛው የነጌሌ አርሲ የበላይነት የነበረ ሲሆን በ58ኛው ደቂቃ ከመዕዘን የተሻማውን ኳስ የሮቤ ከተማ ተጫዋች የሆነው ታሪኩ እሸቱ በራሱ ግብ ላይ በማስቆጠር ነጌሌ አርሲን በሦስት ግብ ልዩነት እንዲመሩ አድርጓቸዋል። ጨዋታው በዚህ እነደቀጠለ ብዙም ሳይቆይ በ64ኛው ደቂቃ የነጌሌ አርሲን አራተኛ ግብ ምንተስኖት ተስፋዬ በማስቆጠር የግብ ልዩነቱን ከፍ ያረገ ቢሆንም ሮቤ ከተማዎች በ69ኛው ደቂቃ በዑስማን ሻሚል እና በ77ኛው ደቂቃ በአብዱላዚዝ ኦማር በማስቆጠር የግብ ልዩነቱን ዝቅ አድርገዋል። ጨዋታውም በነጌሌ አርሲ አሸናፊነት ተጠናቋል።

የ08፡00 ጨዋታዎች

ባህርዳር ላይ በምድብ \’ሀ\’ የምድቡን መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ከሚገኘው ሰንዳፋ በኬ አገናኝቷል። በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ቢታይበትም የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ንግድ ባንኮች የተሻሉ ነበሩ። በተለይም 14ኛው ደቂቃ ላይ ልዑልሰገድ አስፋው የግብጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ከፍ አድርጎ የሞከረውና የግቡን አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰው ኳስ በአጋማሹ የተሻለው ሙከራ ነበር። 26ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ማሙሽ በግሩም ፍጥነት ወደ ሳጥን ይዞት በገባው ኳስ ትልቅ የግብ ዕድል ፈጥሮ የሰንዳፋው ተከላካይ ኤርሚያስ ብርሃኑ በተረጋጋ ቦታ አያያዝ ሲያመክናባቸው በስድስት ደቂቃዎች ልዩነትም አብዱለጢፍ ሙራድ በተመሳሳይ ሁኔታ ገፍቶ የወሰደውን ኳስ እንዳልክ ሰይፉ በግሩም ፍጥነት አስወጥቶባቸዋል። በእንቅስቃሴ ደረጃ ጠንካራ የነበሩት እና የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ፈታኝ ያልነበሩት ሰንዳፋ በኬዎች በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራ 42ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ መሳይ ሰለሞን ከረጅም ርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት በአስደናቂ ሁኔታ ሞክሮት የግቡን የቀኝ ቋሚ ታክኮ ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ሰንዳፋዎች እጅግ ተሻሽለው በመቅረብ ጨዋታውን መቆጣጠር ሲችሉ በመጀመሪያው አጋማሽ ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች ያልተጠቀሙት ንግድ ባንኮች በጨዋታው እየተቸገሩ ሲሄዱ 67ኛው ደቂቃ ላይ አቤል ማሙሽ ከቅጣት ምት ካደረገው ሙከራ ውጪ በአጋማሹ የተሻለ የግብ ዕድል ሳይፈጥሩ ቀርተዋል። በዕለቱ ኮከብ የነበረው እና ከተመልካቾች ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው የሰንዳፋ በኬው መሳይ ሰለሞን 88ኛው ደቂቃ ላይ ከረጅም ርቀት ከቅጣት ምት ግሩም ሙከራ ቢያደርግም የግቡን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል። በሚያሳዩት እንቅስቃሴ ስታዲየም ውስጥ የሚገኘውን ተመልካች ትኩረት መሳብ የቻሉት ሰንዳፋዎች የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃ ላይም በፋሲል ደስታ አማካኝነት ከሳጥን ውጪ ግሩም ሙከራ አድርገው በግብጠባቂው አላዛር ማረኔ መክኖባቸዋል። ጨዋታውም ያለ ግብ ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነጥቡን 28 በማድረስ ከተከታዩ ቤንች ማጂ ቡና በአንድ ነጥብ በመብለጥ የመጀመሪያውን ዙር የምድቡ መሪ ሆኖ አጠናቋል።

በምድብ \’ለ\’ ጅንካ ከተማ እና ሻሸመኔ ከተማ ተገናኝተዋል። በጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እና ፈጣን እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን በተለይ ጅንካዎች ምንም እንኳን ያገኙትን ዕድል መጠቀም ባይችሉም በተደጋጋሚ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርሱ ነበር። ሻሸመኔዎች በበኩላቸው ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም በዋናነት በመስመር ተከላካያቸው ጌትነት ታፈሰ አማካኝነት ጥሩ ጥሩ የቅጣት ምቶችን በመጠቀም ቀዳሚ ለመሆን ጥረው የጅንካው ግብ ጠባቂ አቤል በላይ ውጥናቸውን አምክኖባቸዋል።

በሁለተኛ አጋማሽ የማሸነፍ ግለት በሁለቱም ቡድኖች በኩል የተመለከትን ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎችም ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ተስተውሏል። በአንፃራዊነት ጅንካዎች በተደጋጋሚ ጎል ጋር መድረስ ቢችሉም ኳስን ከመረብ ጋር ማገናኘት አልቻሉም። በተቃራኒው ሻሸመኔዎች ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት ለመከተል በመሞከር እምብዛም ወደ ተቃራኒ ግብ ክልል መድረስ ባይችሉም በ69ኛው ደቂቃ ግን በጌትነት ተስፋዬ ጥሩ አጨራረስ መሪ ሆነዋል። ጅንካዎች ጎል ከተቆጠረባቸው በኋላ በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ ቢሆኑም ጠንካራውን የሻሸመኔ የተከላካይ መስመር ሰብሮ መግባት ተስኗቸው ተሸንፈው ወጥተዋል።

ገላን ከተማ እና ዳሞት ከተማ የምድብ \’ሐ\’ የምሳ በኋላ ተጋጣሚዎች ነበሩ። የመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ የሆነ ጨዋታ እና ተመጣጣኝ የአጨዋወት ስልቶች የተመለከትንበት አጋማሽ ሲሆን በኳስ ቁጥጥሩ ገላን ከተማዎች የተወሰነ የተሻሉበት አጋማሽ ንነበት። በአንፃሩ ዳሞት ከተማዎች በጥብቅ መከላከል ግብ እንዳይቆጠርባቸው በመድረግ በመልሶ ማጥቃት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ተመልክተናል። የመጀመሪያው አጋማሽም ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በግብ የታጀበ እና ፈጣን አጨዋወት የተመለከትንበት አጋማሽ ሲሆን በ53ኛው ደቂቃ ከማል አቶመ ያገኘውን የግብ ዕድል ወደ ግብ በመቀየር ገላን ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ ዳሞት ከተማዎች የተሻለ አጨዋወት በመጫወት በ76ኛው ደቂቃ በተስፋሁን ታደለ ግብ በማስቆጠር አቻ መሆን የቻሉ ሲሆን ነገር ግን ብዙም ሳይቆይ በ81ኛው ደቂቃ የገላን ከተማው ተጫዋች የኋላሸት ፍቃዱ ግብ አስቆጥሮ ገላን ከተማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል። ጨዋታውም ቀጥሎ መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ በተጨማሪ ደቂቃ ራሱ የኋላሸት ፍቃዱ ድጋሚ በማስቆጠር የገለን ከተማ አሸናፊነት ማረጋገጥ ችሏል። ጨዋታው በገላን ከተማ ድል አድራጊነት ተጠናቋል።

የ10:00 ጨዋታዎች

ባህርዳር ላይ የምድብ \’ሀ\’ የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ የሆነው የአዲስ ከተማ ክ/ከተማ እና የጋሞ ጨንቻ ጨዋታ ሲደረግ መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ማራኪ የማጥቃት እንቅስቃሴ የታጀበ ነበር። 12ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ ከተማው እስማኤል ነጋሽ ከሳጥን ውጪ ያደረገው እና ግብጠባቂው የመለሰበት ኳስ የተሻለው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። በምድቡ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ወደር የማይገኝላቸው እና ለተመልካች አዝናኝ በሆነ ጨዋታቸው የሚታወቁት ጋሞዎች 24ኛው ደቂቃ ላይ በምትኩ በንዳ የግንባር ኳስ ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ ሲችሉ 45ኛው ደቂቃ ላይም የግብጠባቂው የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ተጨምሮበት ፍስሐ ቶማስ በግንባሩ ጨርፎ የሞከረው ኳስ በቀኙ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በተመሳሳይ ሂደት ሲቀጥል 58ኛው ደቂቃ ላይ የጋሞው ምትኩ በንዳ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ላይ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው ሀይደር ሙደሲር መልሶበታል። እንደነበራቸው የኳስ ቁጥጥር የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የተቸገሩት አዲስ ከተማዎች አቤል ፀጋዬ እና አመዴን ገረመው ከሳጥን ውጪ ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ ፈታኝ ሙከራ ለማድረግ ተቸግረዋል። 70ኛው ደቂቃ ላይም የጨንቻው ፊናስ ተመስገን በግራ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ቢሞክረውም የግቡን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶበታል። ይህም የመጨረሻው የተሻለ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው ያለ ግብ ተጠናቋል።

\"\"

ጉለሌ ክ/ከተማ እና ቂርቆስ ክ/ከተማ ጅማ ላይ የምድብ \’ለ\’ን የመጨረሻ ጨዋታ አድርገዋል። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በእንቅስቃሴ ረገድ የተሻለ እና ለተመልካች አዝናኝ ነበር። በጎል ሙከራዎች በኩል ጉለሌዎች የተዳከሙ ሲሆኑ ቂርቆሶችን ግን በአንፃራዊነት ጥሩ ነበሩ። ቂርቆሶች ገና ጨዋታው በተጀመረ በ11ኛው ደቂቃም አብዱልከሪም ቃሲም ባስቆጠረው ጎል መሪ ሆነዋል። ከግቡ በኋላም ተጨማሪ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረው መሪነታቸውን ለማሳደግ ተንቀሳቅሰዋል።

\"\"

በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ጨዋታው ለመመለስ መንቀሳቀስ የጀመሩት ጉለሌዎች በኳስ ቁጥጥሩም ሆነ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ ብልጫ ወስደዋል። ይህ ቢሆንም ግን በ56ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ለራሱ እና ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል። ከጨዋታው አንዳች ነገር ለማግኘት መንቀሳቀሳቸውን የቀጠሉት ጉለሌዎች ሙሉ የጨዋታው ደቂቃ ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ የማስተዛዘኛ ግብ አስቆጥረው ጨዋታው ተጠናቋል።

ሆሳዕና ላይ የምድቡን የማሳረጊያ ጨዋታ የከወኑት ሀምበርቾ ዱራሜ እና የካ ክፍለከተማ ነበሩ። የመጀመሪያው አጋማሽ ውጥረት የተሞላበት እና ለመሸናነፍ እልህ አስጨራሽ ትግል የታየበት አጋማሽ እና ሁለቱም ግብ እንዳይቆጠርባቸው የኋላ ክፍላቸውን አጠናክረው ሲጫወቱ ነበር። በእንዳለ ዮሐንስ የሚመራው የሀምበሪቾ ዱራሜ የኋላ መስመር በብስራት በቀለ የሚመራውን የየካ ክ/ከተማን የፊት መስመር በመቋቋም በፊት መስመራቸው ግብ ለማስቆጠር ሲሞክሩ ተስተውሏል። በአጋማሹም ምንም ግብ ሳይቆጠር ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማስቆጠር የበለጠ ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋለ ሲሆን ሀምበሪቾ ዱራሜዎች በተሻለ ጫና በመፍጠር ግብ ለማስቆጠር የሚያደርጉት ጥረት በ58ኛው በአየር የተላከውን ኳስ የቡድኑ መሪ የሆነው የሀምበሪቾ ዱራሜው ተከላካይ እንዳለ ዮሐንስ በግንባሩ በማስቆጠር መሪ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ የካ ክ/ከተማዎች ግብ ለማስቆጠር ሲጫወቱ ሀምበሪቾ ዱራሜዎች በጥንቃቄ በመጫወት ምንም ግብ ሳይቆጠርባቸው ጨዋታውን በማሸነፍ ጣፋጭ ሦስት ነጥብ በማሳካት በውድድሩ በሁሉም ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ሳያስተናግዱ ምድቡን በመሪነት አጠናቀዋል።