በነገው ጨዋታ ከሜዳ ውጪ በስታዲየሙ ውስጥ ሊደረጉ የታሰቡ ነገሮች…

በተጠባቂው የመዲናይቱ ደርቢ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ነገ ሲመለስ ከሜዳ ውጪ በስታዲየሙ ውስጥ ሊደረጉ የታሰቡ ጉዳዮችን ምንድን ናቸው?

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና በሚያደርጉት ተጠባቂ ጨዋታ ነገ ከእረፍት ይመለሳል። በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ በሚደረገው የነገ ተጠባቂ ጨዋታ ተጋጣሚዎቹ ካላቸው ከፍተኛ ደጋፊዎች መነሻነት በስታዲየሙ ጥሩ ድባብ ይኖራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን የውድድሩ የበላይ የሆነው አክሲዮን ማኅበርም እንደተለመደው አዘጋጅ ከተሞች የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ሲያስተናግዱ የሚያደርገውን የመክፈቻ ሥነ-ስርዓት ለማድረግ እየተሰናዳ ይገኛል።

\"\"

ከጨዋታው መጀመር በፊት ከሚደረገው የተለመደው የመክፈቻ ትርዒት በተጨማሪ በነገው ዕለት ደጋፊዎች ወደ ስታዲየም በሚገቡበት ወቅት (ከስታዲየም ውጪ) ከአልኮል ነፃ የሆኑ የማልት መጠጦችን በነፃ እየተጠቀሙ ወደ ስታዲየም እንዲገቡ ከስፖንሰር አድራጊ ተቋማት ጋር ንግግሮች እንደተገባደዱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የህዝብ ግንኙነት ሀላፊ አቶ ሙሉጌታ ደሳለኝ ነግረውናል። የተፈቀደላቸው አካላት ብቻ ከሚጠቀሙበት ዋናው መግቢያ ውጪ ካለው አንድ የደጋፊዎች መግቢያ በተጨማሪ የተዘጋጀው ሌላ አዲስ የደጋፊዎች መግቢያ (የሁለቱ ቡድን ደጋፊዎች የሚገቡበትን መንገድ ለመለየት) ጋር በርካታ ከአልኮል ነፃ የሆነውን መጠጥ ለደጋፊዎች የሚያቀርቡ ማከፋፈያዎች እንደተሰናዱም ተጠቁሟል።

በርካታ ተመልካቾች እንደሚታደሙበት የሚጠበቀው ጨዋታው 9 ሰዓት ከመጀመሩ ከሦስት ሰዓታት በፊት የመግቢያ ትኬቶች መሸጥ የሚጀምሩ ሲሆን የስታዲየሙ በሮችም በተመሳሳይ 6 ሰዓት እንደሚከፈቱ ሀላፊው ገልፀውልናል። የሁለቱ ክለብ ደጋፊዎች ተወካዮችም በዛሬው ዕለት በአዳማ ከፀጥታ እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እንዳደረጉ ተመላክቷል።

\"\"

የውድድሩ የቀጥታ ስርጭት ባለመብት የሆነው ዲ ኤስ ቲቪ በበኩሉ የሀገር ውስጥ ጨዋታዎች ብቻ የሚተላለፉበት አዲስ ቻነል (ሱፐር ስፖርት ልዩ 2) በነገው ጨዋታ ለተመልካቾቹ ይፋ እንደሚያደርግ ገልጿል።

በተያያዘ ከስታዲየም መግቢያ ጋር በተገናኘ አጠቃላይ የመግቢየ ትኬት አሻሻጡ እጅ በእጅ ሲሆን ክቡር ትሪቡን በባጅ ብቻ የሚገባ ሲሆን ጥላ ፎቅ 200 ብር ፣ ከማን አንሼ 100 ብር ፣ ካታንጋ 50 ብር እንዲሁም ዳፍ እና ሚስማር ተራ መግቢያ 20 ብር እንደሆነ ተጠቁሟል።