ነገ በሚጀምረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አዲስ የዳኝነት አመዳደብ ሂደት ተግባራዊ እንደሚሆን ተጠቁሟል።
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በቻን የውድድር ከተቋረጠ በኋላ ነገ በሸገር ደርቢ ደማቅ የመክፈቻ ስነስርዓት መካሄድ ይጀምራል። ከ2012 ጀምሮ ሊጉ በአዲስ የውድድር አቀራረብ መካሄድ ከጀመረበት ወቅት አንስቶ የጨዋታ ዳኞች እንዲሁም ታዛቢዎች ምደባ በተመረጠው ከተማ ተሰባስበው በመግባት እስከ ተመደቡበት የጨዋታ ሳምንታት በሆቴል ቆይተው በሌሎች ተተክተው የሚቀየሩበት አሰራር እንደነበረ ይታወሳል።
በነገው ዕለት በአዳማ ሳይንስ እና ቴክሎኖጂ ጀምሮ መጋቢት 3 ድረስ በሚኖሩት ጨዋታዎች ግን ከዚህ ቀደም ከሚኖረው የዳኞች እና የጨዋታ ታዛቢዎች ድልደላ የተለየ አካሄድ እንደሚኖር ታውቋል። ይሄውም ከሐሙስ እስከ እሁድ በሚደረጉ ጨዋታዎች ስምንት ዋና ስምንት ረዳት ዳኞች እና አራት የጨዋታ ታዛቢዎች ብቻ የሚመደቡ ሲሆን እነዚህም የአንድ ሳምንት ጨዋታቸውን ሲያጠናቅቁ ተሸኝተው ለቀጣዩ ሳምንት በተመሳሳይ ሌሎችን እንዲገቡ እንደሚደረግና ይህ አካሄድ በየሳምንቱ እንደሚከወን አውቀናል። ይህ አዲስ የዳኞች አደላደል መንስኤው ምንድን ነው ስንል የሚመለከታቸውን አካላት አነጋግረናል።
በመጀመርያ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈፃሚ አባል እና የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑትን አቶ ሸረፋ ዶሌቾ ከዚህ ቀደም ከነበረው የዳኞች ምደባ የአሁኑ ሊቀየር የቻለው የሊጉ አክስዮን ማኅበር ባቀረበው ጥያቄ መሰረት እንደነሆነ ጠቀስው ይህ መሆኑ ጥቅምም ጉዳትም እንደሚኖረው አክለው ምደባው ለአዳማ ውድድር ብቻ የሚሆን ጊዜዊ አሰራር እንደሚሆን እና በቀጣይ የዚህኛው አፈፃፀም ታይቶ ማሻሻያ እንደሚደረግበት ገልፀውልናል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክስዩን ማኅበር ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ክፍሌ ሰይፈ በበኩላቸው የምደባው አሰራር እንዲቀየር የተፈለገበትን ምክንያት ሲያብራሩ \”አዳማ በሚኖረን የስድስት ሳምንታት ቆይታ ከሌሎቹ ጊዜያት በተለየ ፎርማት ከሐሙስ እስከ እሁድ ብቻ ጨዋታዎች የሚካሄዱ በመሆኑ የሚመጡት ዳኞች ሦስት ቀን ያለ ምንም ምክንያት እንዳይቀመጡ በማሰብ ነው።\” ብለዋል።