ሪፖርት | 45ኛው የሸገር ደርቢ ጨዋታ በአቻ ውጤት ተጠናቋል

ቀዝቃዛ የነበረው እና በበርካታ ደጋፊዎች ሳይታጀብ የተከናወነው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ ቡና ጨዋታ አንድ ለአንድ ተጠናቋል።

11፡00 ሲል በተደጋጋሚ በይደር እየተያዘ የነበረው ተጠባቂው የሸገር ደርቢ ጨዋታ በቅርቡ በህይወት ያጣነውን አንጋፋ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ በማሰብ ተጀምሯል። ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ፉክክር ሲታይበት በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ እና የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን ኢትዮጵያ ቡናዎች የተሻሉ ሆነው አልፈውበታል። ቡናማዎቹ የጨዋታውን የተሻለ የመጀመሪያ ሙከራ 6ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ጫላ ተሽታ ወደቀኝ ካደላ የሳጥኑ ጫፍ ግሩም ሙከራ አድርጎ የግቡን የቀኝ ቋሚ ገጭቶ ወጥቶበታል።

\"\"

ጨዋታው በሚቆራረጡ ቅብብሎች ታጅቦ ሲቀጥል 35ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድኑር ናስር ከተከላካዮች ጀርባ በመሮጥ ያገኘውን ኳስ ብሩክ በየነ ተቀብሎ ለአብዱልከሪም ወርቁ ሰጥቶት የአጥቂ አማካዩ ጥሩ ሙከራ አድርጎ ነበር። ከደቂቃ በኋላም ቡናማዎቹ በተቃራኒ አቅጣጫ ሌላ የተሻለ የግብ ዕድል ፈጥረው ተመልሰዋል።

ቀስ በቀስ መሀል ሜዳው ላይ ብልጫውን በመውሰድ ጨዋታውን እየተቆጣጠሩ የመጡት ቡናማዎቹ 43ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። መሐመድኑር ናስር የምኞት ደበበን ደካማ የሆነ የኳስ አገፋፍ ተመልክቶ ጫና ውስጥ በመክተት የቀማውን ኳስ ለብሩክ በየነ ሲያቀብል ብሩክ በድጋሚ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል።

ሁለተኛው አጋማሽም በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ ከሚደረጉ ፉክክሮች ውጪ የጠሩ የግብ ዕድሎች ያልተፈጠሩበት ነበር። ከሚታወቁበት ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ እጅግ ተዳክመው የቀረቡት ፈረሰኞቹ የመጀመሪያውን የተሻለ ሙከራቸውን 58ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ቢንያም በላይ በግራ መስመር የተገኘውን የማዕዘን ምት ሲያሻማ ያገኘው ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባሩ ገጭቶ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም የግቡን የቀኝ ቋሚ ገጭቶ ተመልሶበታል።

የተጫዋች ለውጦችን እና የቦታ ሽግሽጎችን በማድረግ መሀል ሜዳው ላይ የተወሰደባቸውን ብልጫ እያስመለሱ የመጡት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 73ኛው ደቂቃ ላይ አቻ ሆነዋል። ሀይደር ሸረፋ ወደ ሳጥን ያሻማውን ኳስ የቡናው ግብጠባቂ ህዝቄል ሞራኬ በእጁ ለማስወጣት ሲሞክር የኳሱ ኃይል የለሽነት ተጨምሮበት ቸርነት ጉግሣ አግኝቶት ማስቆጠር ችሏል።

ከዕረፍት መልስ በመጠኑ ተቀዛቅዘው የቀረቡት ኢትዮጵያ ቡናዎች በአጋማሹ የማጥቃት እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ ታይቷል። ይባስ ብሎም 82ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ሊያስተናግዱ ነበር። አማኑኤል ገብረሚካኤል ከሳጥኑ የቀኝ ክፍል ወደ ውስጥ ያሻገረውን ኳስ ተከላካዩ ኩዋኩ ዱሃ በጥሩ ቦታ አያያዝ አስወጥቶበታል። ኢትዮጵያ ቡናዎች በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራ 90ኛው ደቂቃ ላይ ሲያደርጉ ኃይለሚካኤል አደፍርስ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ብሩክ በየነ በግንባሩ ገጭቶ ሙከራ ቢያደርግም ግብጠባቂው ባህሩ ነጋሽ በጥሩ ቅልጥፍና አስወጥቶበታል። ጨዋታውም 1-1 ተጠናቋል።

\"\"

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ቡድናቸው በጨዋታው ጥሩ እንዳልነበር እና ልምምድ ላይ ሠርተው የመጡትን ነገር እንደጠበቁት እንዳላገኙት ሲናገሩ የኢትዮጵያ ቡናው አሰልጣኝ ዮሴፍ ተስፋዬ በበኩላቸው ጨዋታው ጥሩ እንደነበር እና ቡድናቸው እየተሻሻለ እንደመጣ ገልፀው ጨዋታውን ማሸነፍ ይገባቸው እንደነበር እና ከዚህ በኋላም ከቡድኑ የተሻለ ነገር እንደሚጠብቁ አመላክተዋል።