ነገ በተስተካካይነት የሚደረገው የወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡናን ጨዋታ የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።
13 የጨዋታ ሳምንታትን በተጓዘው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በብቸኝነት የቀረው የወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ተስተካካይ ጨዋታ ነገ ይደረጋል። የ11ኛ ሳምንት መርሐግብር የነበረው ይህ ጨዋታ ሊጉ ከአዳማ ወደ ድሬዳዋ መመለሱን ተከትሎ ቀድሞ እንዲደረግ በታሰበበት የድሬዳዋ ስታዲየም 11:00 ላይ ይከናወናል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለቻን ውድድር ከመጓዙ በፊት በነበረው የሊጉ ቆይታ ሁለቱ ተጋጣሚዎች ተቃራኒ መልክ የነበረው ጊዜን አሳልፈዋል። በ19 ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ወላይታ ድቻ በተለይም በድሬዳዋ ቆይታው 17ቱን ነጥቦች ማሳካት ችሏል። በከተማዋ አንድ ጊዜ ብቻ ሽንፈት ላስተናገደው ወላይታ ድቻ ጠንካራ አቋም እያሳየ ባለበት ሰዓት የውድድሩ መቋረጥ መልካም ዜና አይመስልም። በአንፃሩ ውድድሩ የድል ቀመሩን ባገኘበት ከተማ መቀጠሉ ደግሞ ለድቻ መልካም ዜና ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ሲሆን የነበረበትን የተሻሻለ አቋም ማስቀጠል ዋነኛ ዓላማው ይሆናል።
እንደተጋጣሚው ሁሉ በሊጉ ጥሩ አጀማመር ያልነበረው ሲዳማ ቡና የመጀመሪያ ድሉን ለማግኘት አምስት ሳምንታት አስፈልገውት ነበር። ክለቡ አሰልጣኝ ወንድምአገኝ ተሾመን አሰናብቶ አሰልጣኝ ሥዩም ከበደን እስኪቀጥር ድረስ አራት ነጥብ ብቻ ላይ የቆየ ሲሆን በድሬዳዋ ቆይታው ከአዲሱ አሰልጣኙ ጋር በሰባት ጨዋታዎች ስምንት ነጥቦችን ጨምሯል። ሆኖም የነጥብ ስብስቡ ከወራጅ ቀጠናው ሊያወጣው ባለመቻሉ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። በዚህም በውድድሩ መሀል የተፈጠረው ሰፊ ክፍተት ለአሰልጣኝ ሥዩም ነገሮችን ለማስተካከል ጥሩ አጋጣሚ እንደሆነላቸው መገመት ይቻላል።
ውድድሩ ከተቋረጠ በኋላ ለተጨዋቾቻቸው ዕረፍት የሰጡት ወላይታ ድቻዎች ከጥር ሁለት ጀምሮ መደበኛ ልምምዳቸውን ሲያደርጉ ሰንብተው ሐሙስ ዕለት ድሬዳዋ ተገኝተዋል። በዝውውር መስኮቱ በስብስቡ ላይ አዲስ የተጨመረ ተጫዋች የሌለ ሲሆን ጉዳት ላይ የሰነበቱት ደጉ ደበበ እና አንተነህ ጉግሳ ለነገው ጨዋታም እንደማይደርሱ ታውቋል።
ትናንት ወደ ድሬዳዋ የገቡት ሲዳማ ቡናዎች ደግሞ ከታህሳስ 23 ጀምሮ በሀዋሳ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ቆይተዋል። በነገው ጨዋታ ይገዙ ቦጋለ በ5 ቢጫ ካርድ የማይሰለፍ ሲሆን አዲስ ፈራሚዎቹ ደስታ ደሙ እና ጋናዊው አጥቂ ፒሊፕ አጃህም ቡድኑ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር እስከሚያደርገው የሁለተኛ ዙር የመጀመሪያ ጨዋታው ድረስ ለአዲሱ ክለባቸው መጫወት እንደማይችሉ ታውቋል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ እስካሁን 16 ጊዜ ተገናኝተው ወላይታ ድቻ ሁለት ጨዋታ ሲያሸንፍ በአምስት ጨዋታ አቻ ተለያይተው ሲዳማ ቡና ዘጠኝ ጊዜ አሸንፏል። በሁለቱ ግንኙነት እስካሁን 25 ጎሎች ሲቆጠሩ ወላይታ ድቻ 8 ፣ ሲዳማ ቡና 17 ጎሎች ማስቆጠር ችለዋል።
ጨዋታውን ቢኒያም ወርቅአገኘሁ በመሀል ዳኝነት ሲመራው ፣ ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ይበቃል ደሳለኝ እና አብዱ ይጥና ረዳቶች ፣ ኤፍሬም ደበሌ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል።