ሪፖርት | ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና ነጥብ ተጋርተዋል

በ11ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ ወላይታ ድቻ እና ሲዳማ ቡና በመጀመሪያው አጋማሽ በተቆጠሩ ሁለት ሳቢ ግቦች አቻ ተለያይተዋል።

በተስተካካይ መርሐ-ግብር የተያዘው የሁለቱ ቡድኖች የ11ኛ ሳምንት ፍልሚያ 11 ሰዓት ሲል ተጀምሯል። በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች የሀይል ሚዛኑን ወደ ራሳቸው አድርገው መጫወት የጀመሩት ሲዳማ ቡናዎች በተሻለ የማጥቃት አጨዋወት በጊዜ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ነበር። በ12ኛው ደቂቃም ውጥናቸው ሰምሮ በቶሎ ወደ መሪነት ተሸጋግረዋል። በዚህም መሐሪ መና ያሻገረውን የመዓዘን ምት የመስመር ተከላካዩ አማኑኤል እንዳለ በጥሩ የጭንቅላት አመታት ኳሱን መሬት አንጥሮ ቢኒያም ገነቱ መረብ ላይ አሳርፎታል።

ወደ ጨዋታው ለመመለስ ከስድስት ደቂቃዎች በላይ ያልፈጀባቸው ወላይታ ድቻዎች በ18ኛው ደቂቃ አቻ ሆነዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም አናጋው ባደግ ከግራ መስመር ያሻማውን ኳስ ራሱን ነፃ አድርጎ በሩቁ ቋሚ የነበረው ዘላለም አባተ መዳረሺያውን መረብ አድርጎታል። የአሠልጣኝ ፀጋዬ ተጫዋቾች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ብልጫ ቢወሰድባቸውም ቀስ በቀስ ወደ ሪትም እየገቡ አቻ ከዛም ወደ መሪነት ለመምጣት መጣራቸውን ተያይዘዋል። የአቻነቱን ግብ ካገኙ በኋላም ቀጣዩን ሙከራ በቢኒያም ፍቅሬ የፎርቢች ሙከራ በ30ኛው ደቂቃ አድርገው የግብ ዘቡ መክብብን ፈትነው ተመልሰዋል። ሲዳማዎች በአንፃሩ እንደ አጀማመራቸው አጨራረሳቸውንም ለማሳመር በተለይ በመስመር በኩል ትኩረት ሰጥተው ለማጥቃት ቢያስቡም ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። በጭማሪው ደቂቃ ግን ቢኒያም ሁለተኛ ጎል ሊያስቆጥርባቸው ነበር።

\"\"

የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ በጭማሪው ደቂቃ የተከላካዮችን አለመናበብ ተከትሎ ሙከራ ያደረገው ቢኒያም ሁለተኛው አጋማሽ ገና እንደተጀመረ በሦስተኛው ደቂቃ ከጊት ጋትኩት የተረከበውን ኳስ በመጠቀም የአጋማሹን የመጀመሪያ ሙከራ አድርጓል። ይህ ኳስ ወደ ውጪ ወጥቶ በሲዳማዎች ሲመለስ ዳግም ያገኘው የግቡ ባለቤት ዘላለም በበኩሉ አጋሩ በሞከረው ቦታ ላይ በመሆን ሌላ የሰላ ጥቃት ሰንዝሮ ነበር። የመስመር ተከላካይ በማስወጣት የመስመር አጥቂ ያስገቡት ሲዳማ ቡናዎች ለማጥቃት ፍላጎት ቢያሳዩም በተናበበ ሁኔታ የመጨረሻው የማጥቃት ሲሶ መድረስ ቀላል አልሆነላቸውም። እርግጥ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቢኖራቸውም በሽግግሮች እና ተጋጣሚን ለስህተት በመዳረግ ረገድ ጥሩ በነበሩት ድቻዎች በአደገኛ ቦታዎች ብልጫ ተወስዶባቸዋል።

የጠሩ የግብ ሙከራዎች ያልበረከቱበት የሁለተኛው አጋማሽ መሐል ሜዳ ላይ ያተኮረ የሜዳ ላይ ፍልሚያ ተዘውትሮበታል። በአንፃራዊነት ድቻዎች ወደ ፊት በመሄድ የተሻሉ ቢሆኑም ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም። ሲዳማ ቡናዎችም ኳሱን በተሻለ ቢቆጣጠሩም እስከ 83ኛው ደቂቃ ድረስ አንድም ለግብ የቀረበ ጥቃት አልፈፀሙም። በዚህ ደቂቃ ግን ተቀይረው የገቡት ፍሬው እና እንዳለ በጥሩ መናበብ ተከላካይ በመቀነስ ወደ ሳጥን የላኩትን ኳስ ሳላዲን አግኝቶት ቢሞክረውም ንቁ የነበረው ቢኒያም ከግብነት ታድጎባቸዋል። በጭማሪው ደቂቃ ደግሞ አቤልን ቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው አቤኔዘር በሰከንዶች ልዩነት በግራ እግሩ እና በግንባሩ ሁለት ሙከራዎች አድርጎ ቡድኑን አሸናፊ ሊያደርግ ቢሞክርም ጥሩ ጥሩ ዕድሎችን ሲያድን የነበረው ግብ ጠባቂ ቢኒያም መልሶበታል። ጨዋታውም ተጨማሪ ግቦች ሳይስተናገዱበት አንድ አቻ ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ የወላይታ ድቻው አሠልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ጨዋታው ጥሩ ፉክክር የታየበት እንደሆነ አንስተው በስብስብ ረገድ ከተጋጣሚያቸው ጋር ልዩነት ቢኖርም በፍላጎት ረገድ ተሽለው በመጫወት አንድ ነጥብ እንዳሳኩ በመግለፅ ከተጋጣሚያቸው ጥንካሬ አንፃር የዛሬው አንድ ነጥብ ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ተናግረዋል። የሲዳማ ቡናው አሠልጣኝ ሥዩም ከበደ በበኩላቸው በጨዋታው ከአንድ ነጥብ በላይ እንደሚገባቸው ገልፀው በማጥቃቱ ረገድ ጥሩ እንቅስቃሴ ቢኖርም ከዚህ የበለጠ እድገት እንደሚገባ በማመን ክፍተቶችን በቀጣይ አሻሽለው እንደሚመጡ ተናግረዋል።

\"\"