ዋልያዎቹ ወሳኞቹን ጨዋታዎች የሚያደርጉበት ስታዲየም ታውቋል

በቀጣዩ ወር ከጊኒ ብሔራዊ ቡድን ጋር ወሳኝ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ጨዋታ የሚጠብቀው ዋልያው በሜዳው ማድረግ የነበረበትን ፍልሚያ የሚያደርግበት ስታዲየም ይፋ ሆኗል።

በአይቮሪኮስት አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የ2023 የአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የምድብ ጨዋታዎችን እያደረገ እንደሆነ ይታወቃል። ከግብፅ፣ ማላዊ እና ጊኒ ጋር የተደለደለው ቡድኑም በሁለት ጨዋታዎች ሦስት ነጥብ በማግኘት በግብ ልዩነት ቀዳሚ ደረጃን የያዘ ሲሆን በመጋቢት ወር ባለው የብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ደግሞ የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ እና በሜዳው ለማድረግ መርሐ-ግብር ተይዟል። ታዲያ በሀገራችን የካፍን መስፈርት የሚያሟላ ስታዲየም ባለመኖሩ ለስደት የተዳረገው ቡድኑ ቀጣይ ጨዋታውን በደጋፊው ፊት እንደማያደርግ ከቀናት በፊት ዘገባ አቅርበን ነበር።

\"\"

ከደቂቃዎች በፊት ይፋ በሆነ መረጃ ብሔራዊ ቡድኑ ከጊኒ አቻው ጋር የሚያደርገውን ጨዋታ ሞሮኮ ላይ እንደሚከውን ተረጋግጧል። በዚህም በሞሮኮ ዋና ከተማ ራባት በሚገኘው ልዑል ሞውሊ አብደላ ኮምፕሌክስ ጨዋታው ይደረጋል። በቀደመው ዘገባችን እንዳስነበብነው የጊኒ ብሔራዊ ቡድንም በሀገሩ መጫወት የማይችል ሲሆን የሜዳውን ጨዋታም በተመሳሳይ በሞሮኮ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።

\"\"

የሁለቱ ቢድኖች የመጀመርያው ጨዋታ መጋቢት 15 (ባለሜዳ ጊኒ) ሲደረግ ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ መጋቢት19 (ባለሜዳ ኢትዮጵያ) ይከናወናል።