ሪፖርት | ሀዋሳ እና ባህርዳር ነጥብ ተጋርተዋል

የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማ እና ባህርዳር ከተማን አገናኝቶ 1ለ1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል።

የሁለተኛ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታ ሀዋሳ ከተማን ከባህርዳር ከተማ 10፡00 ሰዓት ሲል አገናኝቷል። ባህርዳር ከተማ አንፃራዊ የእንቅስቃሴም ሆነ የሙከራ ብልጫን ባሳየበት ቀዳሚው አርባ አምስት ከአማካይ ክፍሉ ፣ ከመስመር እና ከቆሙ ኳሶች የማጥቂያ መንገዶቻቸውን በማድረግ ሲጠቀሙ ቢታይም በተለይ በሁለቱ ኮሪደሮች በኩል በፍፁም እና ዱሬሳ አማካኝነት በይበልጥ የግብ አጋጣሚዎች ወደ ሳጥን ሰብሮ በመግባትም ጭምር ከግብ ጋር ለመገናኘት በድግግሞሽ ጥረቶች አልተለዩዋቸውም። የባህርዳርን የቅብብል ስህተት ተጠቅመው በተሻጋሪ ኳስ ለመጫወት ያሰቡት ሀዋሳዎች ቢተጉም ደካማ እንቅስቃሴ በተለይ አማካይ ክፍሉ ላይ በማድረጋቸው በተጋጣሚያቸው ብልጫ ሊወሰድባቸው ችሏል። የሜዳውን ክፍል በደንብ በመለጠጥ የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል በማስጨነቁ ረገድ የተሳካላቸው የጣና ሞገደኞቹ 14ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል ፍፁም ሞክሮ መሐመድ ሙንታሪ በጥሩ ቅልጥፍና ባወጣበት አጋጣሚ ቀዳሚውን ሙከራ አድርገዋል።

\"\"

20ኛው ደቂቃ ላይ አማካዩ አዲሱ አቱላ ከርቀት ሞክሮ የግቡን ቋሚ ታካ ኳሷ ከወጣችበት ሙከራ ውጪ በባህርዳር ቁጥጥር ስር የዋሉት ሀዋሳ ከተማዎች ተጨማሪ ዕድልን ለመፍጠር ቁጥብ ሆነው በአጋማሹ ታይተዋል። የአማካይ እና የመስመር ተጫዋቾቻቸው ተግባቦት ቶሎ ቶሎ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል እንዲደርሱ ያገዛቸው ባህርዳሮች 18ኛው ደቂቃ ላይ ፉአድ ፈረጃ ከቅጣት ምት አክርሮ መቶ ሙንታሪ የያዘበት እና 23ኛው ደቂቃ ላይ መነሻዋን ከዱሬሳ ካደረገች ተሻጋሪ ኳስ ፍፁም በግንባር ገጭቶ የሞከራት ሌላኛዋ የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ቡድን ሙከራዎች ነበሩ። በፉአድ ፣ ፍፁም እና ዱሬሳ ልዩ ቅንጅት ለስህተት ተጋላጭ የሆነውን የሀዋሳን የተከላካይ መስመር በቀላሉ ሲያስከፍቱ የታዩት ባህርዳር ከተማዎች በዚሁ ደካማ የሀዋሳ ተከላካዮች ዝንጉት 30ኛው ደቂቃ ላይ ኳሱን ከመረብ አዋህደዋል። ከቀኝ የሀዋሳ የግብ አቅጣጫ ዱሬሳ በጥሩ እይታ ለፉአድ ሰጥቶት አማካዩ በቶሎ ለፋሲል ሲሰጠው ተጫዋቹ ከቀኝ ወደ ውስጥ መሬት ለመሬት ሲያሻግር ነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ፍፁም ጥላሁን ደርሶት በአግባቡ ከመረብ ሳይቸገር ኳሷን አሳርፏል። በቀሩትም ደቂቃዎች ባህርዳሮች መሪነታቸውን የሚያሰፉበትን ዕድሎች በፍፁም እና ዱሬሳ አማካኝነት ቢያገኙም በ1ለ0 መሪነት አጋማሹ ተገባዷል።


ሁለተኛው አጋማሽ ተጀምሮ ሁለት ያህል ደቂቃ እንደ ተቆጠረ ሀዋሳ ከተማዎች ወደ ጨዋታ የመለሰቻቸውን ግብ ወደ ካዝናቸው ከተዋል። ከግራ የሜዳው ክፍል የተገኘን የቅጣት ምት አዲሱ አቱላ በረጅሙ ወደ ጎል አሻምቶ በረከት ሳሙኤል ሲጨርፋት ከጀርባው የነበረው ግብ ጠባቂ ታፔ አልዛየር ያደረገው የጊዜ አጠባበቅ ስህተት ብቻውን ለቆመው ሙጂብ ቃሲም ኳሷ ደርሳው አጥቂው በቀላሉ በማስቆጠር ቡድኑን ወደ አቻነት መልሷል። ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ሀዋሳዎች በመልሶ ማጥቃት አጨዋወት ለመጫወት ቢጥሩም የሚታይባቸው የመረጋጋት ችግር በተቃራኒው በባህርዳር የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እንዲወሰድባቸው ተገደዋል። ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻሻለ መልኩ የመሀል ሜዳ ክፍሉን ውህደት በበረከት ፣ አለልኝ እና ፉአድ ያዋሀዱት ባህርዳሮች ሁለተኛ ጎልን ለማስቆጠር የጣሩ ቢሆንም በአጋማሹ ተሻሻሎ የቀረበውን የሀዋሳን የተከላካይ ክፍል በማለፉ ረገድ ግን ተዳክመው ተስተውሏል።


የመጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ከሙከራዎች ይልቅ ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ ጨዋታው ቀጥሎ ሁለቱም ቡድኖች የተጫዋች ለውጥ በማድረግ አሸንፎ ለመውጣት ጥረቶች ታይቶባቸዋል። 83ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተጣለለትን ኳስ ተቀይሮ የገባው አደም አባስ በአግባቡ ተቆጣጥሮ የሞከራትን እና ኢላማዋን ሳትጠብቅ የወጣችበት እንዲሁም በመልሶ ማጥቃት ሽግግር ሀዋሳዎች አሸናፊ የሚሆኑበትን ዕድል መጠናቀቂያ ሽርፍራፊ ሰከንድ ላይ ቢያገኙም የመጨረሻዋ ኳስ የደረሰችው ሙጂብ ቃሲም በቀላሉ ካመከናት በኋላ 1ለ1 በሆነ ውጤት ጨዋታው ፍፃሜን አግኝቷል።


ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የሀዋሳው አሰልጣኝ ዘርዐይ ሙሉ ረጃጅም ኳሶችን ተጋጣሚያችን ለመጠቀም አስበው ከዕረፍት በፊት ብልጫም ወስደው ነበር ካሉ በኋላ ከዕረፍት በኋላ ግን የተጋጣሚን ሁለተኛ ኳሶችን በመቆጣጠር ለመጫወት አስበን ሜዳው በመድረቁ ኳስን ለመያዝ ምቹ አልነበረም ፤ በሒደት ረጃጅም ኳስን ለመጠቀም ተገደናል ውጤቱም ሜዳውን የሚገልፅ ነበር በማለት በቂ ነው ሲሉ ተደምጠዋል። የባህርዳር አቻቸው ደግአረገ ይግዛው በበኩላቸው ተጫዋቾቼ ጨዋታውን ለማሸነፍ ጥረት አድርገዋል ውጤቱ ግን ካደረግነው እንቅስቃሴ አንፃር አይገባንም ብለው ከገለፁ በኋላ እኛም ያገኘናቸውን መጠቀም አለመቻላችን የሚያስቆጭ ነው ይሄን አርሞ የመምጣቱ የቤት ስራ የእኛ ነው ብለዋል።

\"\"