ሪፖርት | ዐፄዎቹ ደረጃቸውን ያሻሻሉበት ድል አስመዝግበዋል

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በመጀመርያው ጨዋታቸው ድል አስመዝግበዋል።

ሁለት የተለያየ አቀራረብ ያላቸውን ቡድኖች በታዩበት የመጀመርያው አጋማሽ ዐፄዎቹ ኳስ ተቆጣጥረው ለመጫወት ጥረት ስያደርጉ ኤሌክትሪኮችም ከተከላካይ ጀርባ በሚጣሉ ኳሶች እና በመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት አድርገዋል። በአጋማሹ ከታዩት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችም አብዛኞቹ በዐፄዎቹ በኩል የተደረጉ ነበሩ ፤ በተለይም ሽመክት ጉግሳ ከተከላካዮች ጀርባ ያገኘውን ሰፊ ክፍተት ተጠቅሞ ወደ ሳጥን አሿምቷት አጥቂው ናትናኤል ገ\\ጊዮርጊስ ያልተጠቀመባት ዕድል የአጋማሹ ወርቃማ ዕድል ነበረች።

\"\"

በአማካይ መስመር ላይ የሰመረ ጥምረት የነበራቸው ፋሲሎች በሦስተኛው የሜዳው ክፍል ላይ የነበራቸው ደካማ ተግባቦት ግብ እንዳያገኙ ከማድረጉም ባለፈ ቡድኑ ከረጅም ርቀት ወደሚደረጉ ሙከራዎች ፊቱን እንዲያዞር አስገድዶታል። ከሳጥን ውጭ በተደረጉ ሙከራዎችም በሱራፌል ዳኛቸው እና ዓለምብርሃን ይግዛው በቁጥር በርካታ ሙከራዎች አድርገዋል።

ፋሲሎች ከተጠቀሱት ሙከራዎች ውጭም
መሀል ለመሀል ጥቂት የማይባሉ ያለቀላቸው ዕድሎች ፈጥረው ነበር። በተለይም በጨዋታው ጥሩ የነበረው ሱራፌል ለናትናኤል አሾልኮለት ንቁ ያልነበረው አጥቂው ያመከናት ኳስ እና በተመሳሳይ ሁኔታ ናትናኤል ከሽመክት የተላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ያደረጋት ሙከራ በዐፄዎቹ በኩል አስቆጪ ነበሩ።

\"\"

በአጋማሹ ከኳስ ውጭ ጥሩ መታተር የታየባቸው ኤሌክትሪኮች በአመዛኙ መርጠው በተጫወቱት ከፋሲል ተከላካይ ክፍል ጀርባ የሚገኘውን ቦታ የመጠቀም አዝማምያ በዐፄዎቹ ግብ ጠባቂ ጥሩ የጊዜ አጠባበቅ ብቃት እና ንቃት መክነዋል።
ሆኖም በመልሶ ማጥቃት ጥቂት ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም ልደቱ በመልሶ ማጥቃት የተገኘችውን ኳስ ተጠቅሞ ለኢብራሂም አሻግሮለት አማካዩ በጫና ውስጥ ሆኖ ያደረጋት ሙከራ እና ያሬድ በተመሳሳይ በመልሶ ማጥቃት ያገኛትን ከመስመር አሻምቶ ልደቱ ያደረጋት ሙከራ ይጠቀሳሉ።

ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ በጀመረው ሁለተኛ አጋማሽ በመጀመርያዎቹ ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ተዳክመው የታዩበት ነበር። ሆኖም ፋሲል ከነማዎች ቶሎ አንሰራርተው ጫናዎች ፈጥረው ሙከራዎችም አድርገዋል። ከታዩት ሙከራዎችም ሱራፌል ዳኛቸው አክሮባቲክ በሆነ መንገድ ያደረጋት ሙከራ እና ናትናኤል ከአምሳሉ የተሻገረለትን ኳስ መትቶ ዘሪሁን ወደ ውጭ ያወጣት ኳስ ይጠቀሳሉ። በዚሁ ቅፅበት በኢትዮ ኤሌክትሪክ በኩልም አንድ ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ተደርጓል ፤ ሙከራውም ሚክያስ መትቶ ወደ ውጭ ያወጣው ሙከራ ነበር።

በስልሳ ዘጠነኛው ደቂቃ ፋሲሎች መልሶ ማጥቃት ያገኙትን ዕድል ወደ ግብነት ቀይረዋል። በተጠቀሰው መንገድ ሽመክት ይዞት ወደ ተጋጣሚ ክልል የሄደው ኳስ ታፈሰ ሰለሞን በግሩም መንገድ አቅጣጫ አስቀይሮ ለአምሳሉ የሰጠው ኳስ ተከላካዩ ተጫዋቾች አልፎ ግሩም ግብ አስቆጥሯል። ከደቂቃ በኋላም ናትናኤል በግሉ ጥረት እና በኤሌክትሪክ ተከላካዮች ስህተት ያገኛትን ኳስ ተረጋግቶ በማስቆጠር የቡድኑ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ዐፄዎቹ ተጋጣሚ መረጋጋት በተሳነበት ግዜም በሽመክት እና በናትናኤል አማካኝነት ጥሩ ጥሩ ሙከራዎች አድርገዋል።

በሰባ ዘጠነኛው ደቂቃ ላይ ኤሌክትሪኮች ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ግብ አስቆጥረዋል። አብነት ተከላካዩ አንዳርጋቸው ከመሀል ሜዳ ያሻገረውን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር በማስቆጠር ልዩነቱን ማጥበብ ችሏል። በጎሏ ሂደት የሚካኤል ሳማኪ ግልፅ ስህተትም ተስተውልዋል። 

ኤሌክትሪኮች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ያፈገፈገውን የተጋጣሚ አደረጃጀት ለመስበር በርካታ ጥረቶች ብያደርጉም ሊሰምርላቸው አልቻለም ፤ ይህንን ተከትሎም ጨዋታው በዐፄዎቹ የሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ አስተያየታቸው የሰጡት የፋሲል አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በዕረፍት ሰዓት በትእግስት ለማጥቃት መወሰናቸውን እንደጠቀማቸው ገልፀው ተጋጣምያቸው ጥቅጥቅ ብሎ መጫወቱ ነገሮች ከባድ እንዳደረገባቸውም ገልፀዋል። በመጨረሻም ድሉ ጣፋጭ ነበር ብለዋል። የኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ገዛኸኝ ከተማ በበኩላቸው \”ጎል እስከተቆጠረበት ግዜ ጥሩ ነበርን\” ብለው የተጋጣሚያቸው አጨዋወት ዕቅድ እንዲቀይሩ እንዳስገደዳቸውም አክለዋል። በቀጣይም በአጥቂ ቦታ ላይ ያላቸውን ክፍተት ለማሻሻል እንደሚሰሩ ገልፀዋል። በመጨረሻም \” በእርግጠኝነት ከዚህ ሁኔታ እንወጣለን\” ሲሉ ሀሳባቸውን ቋጭተዋል።

\"\"