መረጃዎች | 57ኛ የጨዋታ ቀን

14ኛ የጨዋታ ሳምንት ነገ በሚደረጉ ሁለት ጨዋታዎች ቀጥሎ የሚውል ሲሆን በተከታዩ ፅሁፍም የነገዎቹን መርሃግብሮች የተመለከቱ መረጃዎች አሰናድተናል።

ሲዳማ ቡና ከ ለገጣፎ ለገዳዲ

በሰንጠረዡ ግርጌ የሚገኙትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር ለቡድኖች ካለው ትርጉም አንፃር በጉጉት ይጠበቃል።

በ13 ነጥቦች በሰንጠረዡ 14ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ሲዳማ ቡናዎች ከወላይታ ድቻ ጋር ነጥብ የተጋሩበትን ጨዋታ ጨምሮ ባደረጓቸው የመጨረሻ ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተው መውጣት ችለዋል። ይህም ለአሰልጣኝ ስዩም ከበደ በተደጋጋሚ ሽንፈቶች የራስ መተማመኑ ወርዶ ለነበረው ስብስባቸው አውንታዊ ጠቀሚታ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሲዳማ ቡናዎች ለገጣፎ ለገዳዲን የሚገጥሙበት እንዲሁም በቀጣይ የጨዋታ ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክ የሚገጥሙባቸው ሁለቱ የመጀመሪያ ዙር የመጨረሻ ጨዋታዎች በተመሳሳይ የወራጅነት አደጋ ከተጋረጠባቸው ተጋጣሚዎች ጋር እንደመሆኑ በጨዋታዎቹ ነጥቦችን መውሰድ የሚችሉ ከሆነ በቀጣይ ጉዟቸው ፈርጀ ብዙ ጥቅም እንደሚኖራቸው ይታመናል።

ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ጨምሮ አረጋዊ ወንድሙን በተጨማሪ ረዳት አሰልጣኝነት እንዲሁም ኢሳያስ ኃይሌ (ረዳት ፕሮፌሰር) በሥነ ምግብ ባለሙያነት በመቅጠር ጭምር የአሰልጣኝ ቡድን አባላታቸውን ለማስፋት ጥረት አድርገዋል። ቡድኑ በነገው ጨዋታ ከወላይታ ድቻ ጋር በሳምንቱ መጨረሻ በነበራቸው መርሃግብር በ5 ቢጫ ካርድ ያመለጠው ይገዙ ቦጋለ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

\"\"

በአንፃሩ በ6 ነጥቦች በሊጉ ግርጌ የሚገኙት ለገጣፎ ለገዳዲዎች ከቻን አፍሪካ ዋንጫ መልስ ቡድኑን በሊጉ ለማቆየት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስን በዋና አሰልጣኝነት የሾሙ ሲሆን የጥራት ጥያቄ የሚነሳበትን ስብስባቸውን ለማሻሻል እንዲሁ ሰባት ተጫዋቾችን ማስፈረም ቢችሉም አዳዲስ ፈራሚ ተጫዋቾችን ግን ከየካቲት 17 አስቀድሞ መጠቀም ባለመቻላቸው ለነገው ጨዋታ አስቀድመው ባስመዘገቧቸው ተጫዋቾች የሚጠቀሙ ይሆናል።

የመጀመሪያው ዙር ለማጠናቀቅ ከሲዳማ ቡና እና መቻል ጋር ጨዋታ የሚጠብቃቸው ለገጣፎዎች ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ውስጥ ከወዲሁ በብዙ ነጥቦች ላለመራቅ በአዲሱ አሰልጣኛቸው እየተመሩ ትግላቸውን ነገ ይጀምራሉ።

የአሰልጣኙም ተቀዳሚ የቤት ስራም የሚሆነው እስካሁን 32 ግቦችን ያስተናገደውን የሊጉን ደካማውን የመከላከል ውቅር ማስተካከል እንደሚሆን ይጠበቃል። ለገጣፎ ለገዳዲዎች ለነገው ጨዋታ ከጉዳት እና ቅጣት የፀዳ ስብስብን ይዘው የሚቀርቡ ይሆናል።

ይህን ጨዋታ ዮናስ ካሳሁን በዋና ዳኝነት ሲመራው ፣ አሸብር ታፈሰ እና ሲራጅ ኑርበገን በረዳትነት እንዲሁም ባህሩ ተካ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት እንደሚመሩት ይጠበቃል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ሀዳያ ሆሳዕና

በምሽቱ መርሃግብር ዳግም የሰንጠረዡን አናት መቆናጠጥን የሚያልሙትን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ወደ መሪዎቹ ይበልጥ ለመጠጋት ከሚጥሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ጋር ያገናኛል።

የአምና የሊጉ አሸናፊዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች ምንም እንኳን ባሳለፍነው ቅዳሜ በደርቢ ጨዋታው ያሳዩት የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አመርቂ ያልነበረ ቢሆንም አሁን ላይ በ26 ነጥቦች በሰንጠረዡ 2ኛ ደረጃ ሲገኙ በነገው ጨዋታ ድል ማድረግ የሚችሉ ከሆነ ግን ዳግም የሊጉን መሪነት በሁለት ነጥብ ልዩነት መረከብ ይችላሉ።

\"\"

በጨዋታዎች ፈጠን ያለ አጀማመርን በማድረግ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግብን ለማስቆጠር የሚጥሩት ፈረሰኞቹ ተጋጣሚዎች ይህን ማድረግ ሲከለክሏቸው በተወሰነ መልኩ ሊቸገሩ እንደሚችል እየተመለከትን የምንገኝ ሲሆን በነገው ጨዋታም ሆሳዕናዎች ይህን ጥንካሬያቸው ለማምከን እንደሚገቡ ይጠበቃል።

ፈረሰኞቹ በነገው ጨዋታም የዳዊት ተፈራን ግልጋሎት አያገኙም ተጫዋቹ ከጉዳት ሙሉ ለሙሉ ቢያገግምም ለጨዋታው ግን እንደማይደርስ ሲረጋገጥ ሻሂዱ ሙስጠፋም እንዲሁ በጉዳት ምክንያት ከነገው ስብስብ ውጭ ሆኗል።

በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ያላደረጉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በ21 ነጥቦች 4ኛ ደረጃ ላይ ቢገኙም በመጨረሻ ጨዋታዎች ግን የነበራቸው እንቅስቃሴም ሆነ ውጤት ከአስደናቂ የሊጉ አጀማመራቸው አንፃር እምብዛም አመርቂ አይደለም። ከመጨረሻ ሰባት የሊግ ጨዋታዎች በአምስቱ አቻ የተለያየው ቡድኑ ከዚህ ባለፈም ግን ግቦች ላይ አይናፋር የመሆኑ ነገር እጅግ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። ሊጉ ከመቋረጡ በፊት ባደረጓቸው ስድስት የሊግ ጨዋታዎች አንድ ግብን ብቻ የማስቆጠራቸው ነገር በፍጥነት እልባትን ይሻል። በሊጉ ከወገብ በላይ ከሚገኙ ቡድኖች ውስጥ እንደ ወላይታ ድቻ ሁሉ 12 ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው ሀዲያ ሆሳዕና ሁነኛ የግብ አስቆጣሪዎችን ይሻል።

በጨዋታው ነብሮቹ ቤዛ መድህንን በጉዳት እንዲሁም ግርማ በቀለን ደግሞ በቅጣት የማያገኙ ይሆናል።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ በስድስት ጨዋታዎች የተገናኙ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ሁለት ጊዜ እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደግሞ አንድ ጊዜ ማሸነፍ ሲችሉ የተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ በመጋራት የተጠናቀቁ ነበሩ።

በድሬዳዋ ስታዲየም የሚደረገውን የምሽቱ መርሃግብር
ኢንተርናሽናል ዳኛ ለሚ ንጉሴ በመሀል ዳኝነት ሲመሩት ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ሙስጠፋ መኪ እና ኤፍሬም ኃይለማርያም ረዳቶች እንዲሁም ተከተል ተሾመ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆኖ ይመሩታል።