ሪፖርት | ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ፈረሰኞቹን ነጥብ ከመጣል ታድጓል

የቶጓዊው አጥቂ የመጨረሻ ደቂቃዎች ግብ ፈረሰኞቹን ወደ ሰንጠረኙ አናት መልሳለች።

\"\"

ፈረሰኞቹ በአመዛኙ ከተጠቀሙበት አቀራረብ ምኞት ደበበ እና ጋቶች ፓኖም በበረከት ወልዴ እና አማኑኤል ተርፉ ተክተው ሲገቡ ሀድያዎች በበኩላቸው ብርሃኑ በቀለ እና ሳምሶን ጥላሁን ወደ ቋሚነት መልሰው ጨዋታቸውን ጀምረዋል።

የሀድያ ሆሳዕና ፍፁም ብልጫ በታየብት የመጀመርያው አጋማሽ ፈረሰኞቹ ተዳክመው የታዩበት ሆኗል። ሆሳዕናዎች ብልጫ ወስደው በርካታ ሙከራዎች ያደረጉበትም ነበር። ሆኖም እንደወሰዱት ብልጫ ጥራት ያላቸው ሙከራዎች ማድረግ አልቻሉም።

በአጋማሹ ብልጫ የነበራቸው ሀድያዎች ብሩክ ማርቆስ እና ሬችሞንድ አዶንጎ ባደረጓቸው ሙከራዎች ወደ ግብ መድረስ ጀምረው በርካታ ተጨማሪ ዕድሎችም ፈጥረዋል። ከነዚህም ተመስገን በጊዮርጊስ ተጫዋች ስህተት ያገኝውን ኳስ መትቶ ያደረገው ሙከራ እና ብርሃኑ የግብ ጠባቂው መውጣት ተከትሎ መትቶት ባህሩ በጥሩ መንገድ ያወጣው ኳስ ይጠቀሳሉ።

የፈረሰኞቹ የአማካይ አደረጃጀት ከጨዋታ ውጭ በማድረግ ጥሩ አጋማሽ ያሳለፉት ሀድያዎች ከኳስ ውጭ የነበራቸውን ስኬት ከኳስ ጋር ባይደግሙትም ከመስመር በሚሻገሩ ረጃጅም ኳሶች ጥቂት የማይባሉ ሙከራዎች አድርገዋል። ከነዚህም አዶንጎ ከመስመር የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ በግንባር ያደረገው ሙከራ ፤ በተመሳሳይ ኦዶንጎ ከመስመር የተሻገረለት ኳስ ሞክሮ ተከላካዮች ተድርበውበት ፀጋዬ አግኝቶ ሞክሮት ባህሩ በጥሩ ብቃት ያዳነው ኳስ ለግብ የቀረቡ ነበሩ። በአጋማሹ ድካማ እንቅስቃሴ ያደረጉት ፈረሰኞቹ ምንም ዓይነት ሙከራ ሳያደርጉ ወደ ዕረፍት ወጥተዋል ፤ ለዚህም የአማካይ ክፍሉ አደረጃጀት መፋለስ እንደ ትልቅ ምክንያት ይጠቀሳል።

የሁለተኛው አጋማሽም በተመሳሳይ የሀድያ ብልጫ የታየበት ቢሆንም ፈረሰኞቹ በተለይም የተጫዋቾች ቅያሬ ካደረጉ በኋላ በአንፃራዊነት የተሻለ እንቅስቃሴ አድርገዋል። አጋማሹ ከመጀመርያው አጋማሽ አንፃር ሲታይ እጅግ ጥቂት ሙከራዎች የታዩበት ነበር ፤ በሀድያዎች በኩል ተመስገን ከሄኖክ የተሻገረለትን ኳስ ለፍቅረየሱስ አመቻችቶለት አማካዩ ሞክሮ ወደ ውጭ ያወጣው እና ሄኖክ ከማዕዘን አሻምቶት ቃልአብ በግንባር ያደረገው ሙከራ ይጠቀሳሉ።

ዕድሎች ከመፍጠር አልፈው ዕድሎቹን ወደ ሙከራነት ለመቀየር ሲቸገሩ የተስተዋሉት እና በአጠቃላይ በጨዋታው ሁለት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ብቻ ያደረጉት ፈረሰኞቹ በሰማንያኛው ደቂቃ ላይ በቶጓዊው አጥቂ አማካኝነት ግብ አስቆጥረው መሪ መሆን ችለዋል። አቤል እና አማኑኤል ተቀባብለው ወደ ሳጥን ይዘዋት ከገቡ በኋላ ተጨራርፋ ወደ አጥቂው ስትደርስ ነው አይምሬው አጥቂ የጊዮርጊስን አሸናፊነት ያወጀቺውን ኳስ ወደ ግብነት የቀየራት። 

 

ጥሩ ፉክክር የታየበት ጨዋታ በፈረሰኞቹ አሸናፊነት ከተጠናቀቀ በኋላ የሁለቱም ቡድኖች አሰልጣኞች የሚከተለውን አሰተያየት ሰጥተዋል። \”ዕድል ከእኛ ጋር ስላልነበረች ተሽንፈናል\” ያሉት አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ \”የአጨራረስ ችግር አለብን ፤ ከጨዋታ በፊት ችግራን ለመቅረፍ ብዙ ጥረት አድርገን ነበር ግን ችግሩ አልተቀረፈም። በጨዋታው ጥሩ ነበርን ግን እነሱ በልምድ በልጠውን ጨዋታውን አሸንፈው ወጥተዋል።\” በማለት ሀሳባቸውን ቋጭተዋል። አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ጨዋታው ጠንካራ እንደሚሆን መገመታቸውን ጠቁመው \”በዕረፍት ችግራችንን ለመቅረፍ ተነጋግረን ስለገባን በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ተንቀሳቅሰናል። ጨዋታው ሚዛናዊ ነበር ፤ ስለ መሪነታችን ምንም ማለት አልፈልግም።\” ብለዋል።

\"\"