መረጃዎች | 58ኛ የጨዋታ ቀን

የ14ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ ቅድመ መረጃዎች እንደሚከተለው አሰባስበናል።

መቻል ከ ኢትዮጵያ ቡና

በአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ የሚመራው መቻል በመጨረሻው የሊጉ ጨዋታ ባህር ዳር ከተማ ላይ ጣፋጭ ድል ካስመዘገበ በኋላ ለተጫዋቾቹ የአስር ቀን የእረፍት ጊዜ ሰጥቶ ቀደም ብሎ ታኅሣሥ 22 ነበር ዝግጅቱን በመዲናው የጀመረው። አንድ ሳምንት አዲስ አበባ ላይ ከሰራ በኋላ ወደ ቢሾፍቱ በማምራት ረዘም ያለውን የልምምድ ወቅት በዐየር ኃይል ሜዳ አከናውኗል። በዚህ ጊዜም አዳማ እና ወንጂ ስታዲየም ከሲዳማ እንዲሁም ኢትዮ ኤሌክትሪክ ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታ አድርጓል። በአንፃራዊነት በእንቅስቃሴም ሆነ በውጤት ረገድ መሻሻል እያሳየ ሊጉ መቋረጡ መቻል ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ነገ የሚታይ ሲሆን ምናልባት በማጥቃቱ ረገድ የነበረበትን ክፍተት ግን ዕረፍቱ የማረሚያ ጊዜም ሊሆነው ይችላል።

ኢትዮጵያ ቡናም እንደ መቻል ቀደም ብሎ ዝግጅቱን ጀምሮ የነበረ ሲሆን ባሳለፍነው ሳምንትም በብዙዎች ዘንድ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን የሸገር ደርቢ ጨዋታ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር አከናውኖ አንድ አቻ ተለያይቷል። በጨዋታው በእንቅስቃሴ ደረጃ ቡድኑ ከፍተኛ መሻሻል ያሳየ ሲሆን እንደበፊቱ ከኳስ ጋር የሚያሳልፈውን ጊዜ በመቀነስ ተጋጣሚን ለስህተት እየዳረገ ሽግግሮችን ለመጠቀም የሚጥር ሆኖ ቀርቦ ነበር። ይህ አቀራረብ ጊዮርጊስን ፈትኖ የነበረ ሲሆን ነገም የሚደግመው ከሆነ ከውጤት ተኮርነቱ መነሻነት ምናልባት ሊጠቀምበት ይችላል። ከዚህ ውጪ በጨዋታ ሪትም ውስጥ ሆኖ ጨዋታውን መጀመሩም ሊጠቅመው ይችላል።

\"\"

መቻልም ሆነ ኢትዮጵያ ቡና በውድድር አጋማሹ የዝውውር መስኮት ምንም ተጫዋች አላስፈረሙም። ከጉዳት ጋር ተያይዞ በነገው ጨዋታ መቻል የተሾመ በላቸው እንዲሁም ግሩም ሀጎስን ግልጋሎት የማግኘቱ ጉዳይ እርግጥ አይደለም። ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ረጅም ጉዳት ላይ የሚገኘው አስራት ቱንጆን አያገኝም።

ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን በሊጉ 30 ጨዋታዎችን አድርገዋል። ኢትዮጵያ ቡና 15 ጊዜ በማሸነፍ የበላይ ሲሆን መቻል 7 ጊዜ ድል አድርጎ በ8 ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ቡና 42 መቻል ደግሞ 29 ግቦችን አስቆጥረዋል።

ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ በዋና ዳኝነት ሲመራው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ትግል ግዛው እና ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛ ተመስገን ሳሙኤል በረዳትነት እንዲሁም ኢንተርናሽናል ዳኛ በአምላክ ተሰማ በአራተኛ ዳኝነት ያገለግላሉ።

ወልቂጤ ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

ወልቂጤ ከተማ ዘለግ ያለቀናት በነበረው የውድድር አጋማሽ የዝግጅት ጊዜ ነገሮች ባሰበው መልኩ አልተጓዙለትም። ክለቡ ለተጫዋቾች ዕረፍት ከሰጠ በኋላ ከጥር 10 ጀምሮ በመሰባሰብ ለተከታታይ አምስት ቀናት ልምምዱን የሰራ ሲሆን ከክፍያ ጋር በተያያዘ ግን ተጫዋቾች ቅሬታ ገብቷቸው ሆቴል ለቀው በመውጣታቸው ዝግጅቱን በሚገባ መከወን አልቻለም። ከዘጠኝ ቀናት በኋላም ገሚሶቹ ተጫዋቾች መጥተው በከፊል ልምምዱን የጀመረ ሲሆን በበላይ አመራሮቹ አግባቢነት ሁሉም ተጫዋቾች ተሰባስበው መደበኛ ዝግጅት የተጀመረው ከጥር 27 አንስቶ ነው። ይህ ቡድኑ ላይ ከዝግጁነት ጋር ተያይዞ ተፅዕኖ የሚያመጣ ሲሆን ሊጉ በተለያዩ ምክንያቶች ተራዘመ እንጂ ቀድሞ በታሰበው ጊዜ ቢከወን ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳ ነበር። የሆነው ሆኖ በተጠቀሰው ጊዜ ዝግጅቱን አዳማ ላይ አከናውኖ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር አንድ የአቋም መፈተሻ ጨዋታ በማድረግ ውድደሩ ወደሚከናወንበት ድሬዳዋ አምርቷል።

\"\"

በይደር ቆይቶ የነበረውን የደርቢ ጨዋታ ከሲዳማ ቡና ጋር ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ያደረጉት ወላይታ ድቻዎች ፍልሚያውን በአቻ ውጤት መፈፀማቸው ይታወሳል። ድቻዎች በጨዋታው ቀድሞ ግብ ቢቆጠርባቸውም በእንቅስቃሴ ረገድ ፈጣን ምላሽ በመስጠት ከጨዋታው አንድ ነጥብ ያገኙበትን ጎል አስቆጥረዋል። በተለይ ደግሞ ፈጣኖቹን የመስመር ተጫዋቾች በመጠቀም ተደጋጋሚ የግብ ማግባት ዕድሎችም በሽግግሮች እንዲሁም በረጃጅም ኳሶች ሲሞክሩ ተስተውሏል። ከላይ እንደገለፅነው ተጋጣሚያቸው ወልቂጤ በተሟላ መንገድ ዝግጅቱን አለማድረጉ እና አሁናዊ ብቃቱን በሚገባ አለመፈተሹ መጠነኛ ተፅዕኖ ሊፈጥርበት ስለሚችል ከጥር 2 ጀምሮ በልምምድ የቆዩት እና ከወዳጅነት ጨዋታዎች ባለፈ የነጥብ ጨዋታ ያደረጉት ድቻዎች ምናልባት ከጨዋታ ዝግጁነት ጋር ተያይዞ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ።

ወልቂጤ ከተማ በዝውውር መስኮቱ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ፍላጎት ቢኖረውም በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እግድ ስለተጣለበት ውጥኑ ሳይሰምር ቀርቷል። ወላይታ ድቻም እንደ ወልቂጤ እግድ ባይኖርበትም አንድም አዲስ ተጫዋች ሳያስፈልም ወደ ውድድር ገብቷል።

በነገው ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ የቴዎድሮስ ሀሙ እና አንዋር ዱላን ግልጋሎት በጉዳት ምክንያት የሚያጣ ሲሆን ግልፅ ባልሆነ ምክንያት እስካሁን ቡድኑን ያልተቀላቀለው ሮበርት ኦዶንካራም በፍልሚያው አይኖርም። በወላይታ ድቻ በኩሉ ደጉ ደበበ እና አንተነህ ጉግሳ በጉዳት ምክንያት እንደማይጠቀም ተገልጿል።

ሁለቱ ክለቦች እስካሁን በሊጉ አራት ጊዜ የተገናኙ ሲሆን ወልቂጤ ሁለት ወላይታ ድቻ ደግሞ አንድ ጊዜ ድል ቀንቷቸው በቀሪው አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል። በእነዚህ አራት ጨዋታዎች ወልቂጤ አምስት ወላይታ ድቻ ደግሞ ሦስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ሄኖክ አበበ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታውን በዋና ዳኝነት ነገ ሲመራ ሙሉነህ በዳዳ እና ሸረፈዲን አል ፈኪ በረዳትነት እንዲሁም ተካልኝ ለማ በአራተኛ ዳኝነት እንዲያገለግሉ ተመድበዋል።