በብርቱ ፉክክር ታጅቦ ለተመልካች አዝናኝ የነበረው የኢትዮጵያ ቡና እና የመቻል ጨዋታ 3-3 ተጠናቋል።
ሁለቱም ቡድኖች በመረጡት ጥንቃቄ የተሞላበት አጨዋወት ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው ጨዋታ የጠሩ የግብ ዕድሎች ባይፈጠሩበትም ቀስ በቀስ ግን መኃል ሜዳው ላይ ብልጫ ለመውሰድ ፉክክር ታይቶበታል። በኳስ ቁጥጥሩ የተሻሉ የነበሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች የመቻልን የተከላካይ መስመር ለማለፍ ይቸገሩ እንጂ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውሏል። 21ኛው ደቂቃ ላይም መቻሎች ከማዕዘን ባሻሙት እና እስራኤል እሸቱ በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠራት ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።
ከግቧ መቆጠር በኋላም ጨዋታው በተሻለ ግለት ሲቀጥል ብልጫ እየወሰዱ የመጡት መቻሎች የጠሩ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ በአንጻሩ ጨዋታውን ሲጀምሩ ከነበራቸው እንቅስቃሴ እየተቀዛቀዙ የመጡት ቡናማዎቹ በመቻል ተከላካዮች መፈተናቸውን ቀጥለዋል። 36ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤል ተክለሚካኤል ከማዕዘን በተሻገረለት ኳስ በግንባሩ በመግጨት የግቡን የላይ አግዳሚ ታክኮ ለጥቂት የወጣ ሙከራ ማድረግ ሲችል በተመሳሳይ መንገድ 41ኛው ደቂቃ ላይ ራምኬል ጀምስ በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮ ኢትዮጵያ ቡናን አቻ ማድረግ ችሏል።
ጨዋታው በአቻ ውጤት ወደ ዕረፍት ለማምራት የዳኛው ፊሽካ በሚጠበቅበት ሰዓት መቻሎች ግብ አስቆጥረው በድጋሚ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በዚህም 47ኛው ደቂቃ ላይ ከነዐን ማርክነህ ከተስፋዬ አለባቸው በተቀበለው ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ሕዝቄል ሞራኬ ሲመልስበት ፍጥነቱን ተጠቅሞ ኳሱን ያገኘው እስራኤል እሸቱ ማስቆጠር ችሏል።
ጨዋታው ከዕረፍት መልስ በብርቱ ፉክክር በመታጀብ ለተመልካች እጅግ አዝናኝ ሆኖ ሲቀጥል አስደናቂ አጀማመር ያደረጉት ኢትዮጵያ ቡናዎች 49ኛው ደቂቃ ላይ መሐመድ ኑር ናስር ከማዕዘን የተሻገረው ኳስ በተከላካዮች ተጨርፎ አግኝቶት በግንባሩ ገጭቶ ባስቆጠረው ግብ ወደ ጨዋታው መመለስ ሲችሉ ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠርም ድንቅ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። 56ኛው ደቂቃ ላይም ተሳክቶላቸው ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል።
ብሩክ በየነ ተከላካዮችን እና ግብ ጠባቂውን አታልሎ በማለፍ በግሩም ሁኔታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው መስፍን ታፈሰ ማስቆጠር ችሏል። ለግቧ መቆጠር ትልቁን ሚና የተጫወተው ብሩክ በየነም ባሳየው ክህሎት ከተመልካቾች አድናቆት ተችሮታል።
መቻሎች መሪነታቸውን ከተነጠቁ በኋላ የማጥቃት ባሕርይ ያላቸውን ተጫዋቾች ቀይረው በማስገባት የተሻለ ለመንቀሳቀስ ያደረጉት ሙከራ 77ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። በዚህም ተቀይሮ የገባው ግርማ ዲሳሳ ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት ያሻገረለትን ኳስ ያገኘው በተመሳሳይ ተቀይሮ የገባው በረከት ደስታ መረቡ ላይ አሳርፎታል። አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ላሰቡት በመስመር የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጓቸው ቅያሬዎችም ውጤታማ አድርጓቸዋል። በመጨረሻም ጨዋታው 3-3 ተጠናቋል።