ለገጣፎ ለገዳዲ በአራት ተጫዋቾች ጉዳይ ውሳኔ ተላለፈበት

በርከት ያሉ ተጫዋቾችን የሸኘው ለገጣፎ ለገዳዳዲ በአራት ተጫዋቾች ክስ ቀርቦበት የዲሲፕሊን ኮሚቴ ውሳኔ አሳልፎበታል።

በዘንድሮው የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለመጀመርያ ጊዜ እየተሳተፈ የሚገኘው ለገጣፎ ለገዳዲ በቅርቡ ከስምንት ተጫዋቾች ጋር በስምምነት ሲለያይ አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ መቀላቀሉ ይታወቃል። በዚህ ሂደት ወንድወሰን ገረምው፣ አንተነህ ናደው፣ ዳዊት ቀለመወርቅ እና አንዋር አብዱልጃባድ \”እስከ ነሐሴ 2015 ድረስ ኮንትራት እያለን ክለቡ አሰናብቶናል\” በማለት አቤቱታቸውን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ሲያቀርቡ ቆይተዋል።

\"\"

ጉዳዩን የመረመረው የዲሲፒሊን ኮሚቴም ለገጣፎ ለገዳዲ በቀረበበት ክስ ዙርያ የመከላከያ ምላሽ እንዲሰጥ በደብዳቤም ሆነ በስልክ ቢጠየቅም ምላሽ ሊሰጠው እንዳልቻለ በመግለፅ ዲሲፕሊን ኮሚቴው በክለቡ ላይ ውሳኔ አሳልፏል።

\"\"

በዚህም መሠረት ተጫዋቾቹን ያሰናበተበት መንገድ የህግ መሰረት የሌለው እንደሆነ በመጥቀስ ተጫዋቾቹን ወደ ስራ እንዲመልስ እና ለተጫዋቾቹ ያልከፈላቸው ደሞዝ በአንዴ እንዲከፍል ተወስኗል። በተጨማሪም ክለቡ ተጫዋቾቹን ለመመለስ ፍቃደኛ ሆኖ ካልተገኘ ለቀሪ የውል ወራት ደሞዛቸውን በመክፈል መልቀቂያ በመስጠት እንዲያሰናብታቸው ሲወሰን ይህን ውሳኔ በሰባት ቀን ውስጥ ክለቡ ተፈፃሚ እንዲያደርግ እና ይህ የማይፈፀም ከሆነ ክለቡ ከፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ምንም አይነት አገልግሎት እንዳያገኝ እና ከተጫዋቾች ምዝገባና ዝውውር እንዲታገድ ተብሏል። በመጨረሻም ክለቡ ውሳኔው የማይቀበል ከሆነ ይግባኝ የመጠይቅ መብት እንዳለው በደብዳቤ ላይ ተመላክቷል።