ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ14ኛ ሳምንት ምርጥ 11

ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 14ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን በመመርኮዝ ቀጣዮቹን ምርጥ 11 እና አሰልጣኝ መርጠናል።

አሰላለፍ – 4-3-3

ግብ ጠባቂ

አቡበከር ኑራ – ኢትዮጵያ መድን

ኢትዮጵያ መድን ከአዳማ ከተማ ጋር ባደረገው ጨዋታ ድል ባይቀናውም አንድ ነጥብ ይዞ እንዲወጣ የአቡበከር ሚና ከፍተኛ ነበር። ግብ ጠባቂው በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ አምስት ደቂቃዎች ውስጥ ግብ ከመሆን ያገዳቸው አራት ፈታኝ ሙከራዎች ተመራጭ አድርገውታል።

\"\"

ተከላካዮች

ሙና በቀለ – አርባምንጭ ከተማ

አርባምንጭ ከተማ ከመመራት ተነስቶ በድሬዳዋ ላይ ጣፋጭ ድል ሲጎናፀፍ የመስመር ተከላካዩ ሚና ላቅ ያለ ነበር። ከተፈጥሮአዊው የመከላከል ሚናው በተለየ የመስመር ማጥቃት ሚናውን በአግባቡ ሲወጣ የተስተዋለው ተጫዋቹ ቡድኑ በሰነዘራቸው ጥቃቶች ላይ ከነበረው ብርቱ ትጋት አንፃር በምርጥነት አካተነዋል።

ዋሁቡ አዳምስ – ወልቂጤ ከተማ

ወልቂጤ ከተማዎች ገና በጊዜ ጎል ካገኙ በኋላ በጥልቅ መከላከል ሦስት ነጥብ ይዞ ለመውጣት የጋናዊው የመሀል ተከላካይ አስደማሚ የመከላከል ብስለት እና በጫና ውስጥ የቡድኑ የመከላከል ቅርፅ መዘናፍ እንዳይታይበት ሽፋን በመስጠት ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ እስኪጠናቀቅ ድረስ ያሳየው የነቃ የተሳትፎ የጎላ ድርሻ ነበረው።

አሸናፊ ፊዳ – አርባምንጭ ከተማ

አርባምንጭ ከተማ ገና በጊዜ ተከላካዩ አሸናፊ ኳስን በእጅ በመንካቱ በሳጥኑ ጠርዝ ከተገኘ ቅጣት ምት ጎል እንዲቆጠር ምክንያት የነበረ ቢሆንም በቀሩት የጨዋታ ደቂቃዎች ግን በሂደት ቡድኑን ለመካስ ባደረገው የመከላከልም ሆነ የማጥቃት ተሳትፎ ጥሩ አበርክቶ ሰጥቷል። ከእንቅስቃሴ ባለፈ ሦስተኛዋን የአርባምንጭ ግብ ከመረብ ማሳረፍ በመቻሉ የሳምንቱ ምርጥ ላይ ልናካትተው ችለናል።

አምሳሉ ጥላሁን – ፋሲል ከነማ

ዐፄዎቹ ኢትዮ ኤሌክትሪክን ስያሸንፉ አምሳሉ የግል ብቃቱን ያሳየበት ማራኪ ግብ ከማስቆጠሩም በላይ የተጋጣሚ መልሶ ማጥቃት መከላከል እና የግብ ዕድሎች መፈጠርም ላይ ትልቅ ድርሻ ነበረው። ካስቆጠረው ግብ ባሻገር በተለይም በጨዋታው ሁለተኛው አጋማሽ የመጀመርያ ደቂቃዎች ላይ የፈጠራት አንድ ንፁህ የግብ ዕድል ተጫዋቹ በማጥቃቱ ላይ ለነበረው ውጤታማነት ምስክር ነች።

\"\"

አማካዮች

አማኑኤል ዮሐንስ – ኢትዮጵያ ቡና

ረዘም ያሉ ሳምንታትን ከሜዳ ርቆ የሰነበተው አማካዩ ወደ ሜዳ ሲመለስም በጥሩ አቅሙ እንደ ተመለሰ የመቻሉ ጨዋታ ማሳያ ነበር። የቡድኑ አጨዋወት በአግባቡ ተቆጣጥሮ ሚዛን በመጠበቅ ለተከላካዮች ጥሩ ሽፋን በመስጠት እንዲሁም ለአጥቂዎች ቀጥተኛ ኳስን በማከፋፈል ያማረ የጨዋታ ጊዜ የነበረው አማካዩ በምርጥ ስብስብ ውስጥ አካተነዋል።

ፉዐድ ፈረጃ – ባህር ዳር ከተማ

ክለቡ ባህርዳር ከተማ ምንም እንኳን ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ተጋርቶ ቢወጣም የተጫዋቹ የሜዳ ላይ ቆይታ አስደናቂ ነበር ማለት ይቻላል። የባህር ዳርን የመሀል ሜዳ ክፍል ሚዛናዊ በማድረግ እና የሚገኙ ዕድሎችን ለመፍጠር በጥልቀት ተስቦ ወደ ሳጥኑ በመጠጋት ሲያደርጋቸው ከነበሩ ወጥ እንቅስቃሴዎች እና ሙከራዎች አንፃር አማካዩን በምርጥ ስብስባችን ውስጥ አካተነዋል።

ታፈሰ ሰለሞን – ፋሲል ከነማ

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የመጀመርያ ድላቸውን ሲቀዳጁ ትልቅ ድርሻ በነበረው አማካይ ክፍል ውስጥ ታፈሰ ሰለሞን ትልቅ ድርሻ ነበረው። ታፈሰ አንድ ለግብ የሆነ ኳስ ከማመቻቸትም አልፎ በተለይም በሦስተኛ የሜዳ ክፍል ላይ የነበረው ውጤታማነት በርካታ ንፁህ የግብ ዕድሎች እንዲፈጥር አስችሎታል።

አጥቂዎች

መሀመድኑር ናስር – ኢትዮጵያ ቡና

በሊጉ ፈጣን ከሚባሉ አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው መሀመድኑር ናስር በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ይህንኑ አቅሙን በመቻሉ ጨዋታ ላይ አሳይቷል። ክለቡ ያደረገውን ጨዋታ በአቻ ውጤት በፈፀበት ዕለት ጎል ከማስቆጠሩም ባሻገር በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ማሳየት ችሏል።

ይገዙ ቦጋለ – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና ለገጣፎ ለገዳዲ ላይ የ2ለ0 ድል ሲቀዳጅ በሁለቱም ግቦች ላይ  በማስቆጠር እና አመቻችቶ በማቀበል ቀጥተኛ ተሳትፎ ያደረገው አጥቂው በዕለቱ ያደረገው ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ በቦታው ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ ያደርገዋል።

እስራኤል እሸቱ – መቻል

መቻል ኢትዮጵያ ቡናን ገጥሞ 3ለ3 ጨዋታውን ሲፈፅም የአጥቂው እስራኤል እሸቱን ያህል የተሳካለት አልነበረም። ግዙፉ የፊት መስመር ተጫዋች በተደጋጋሚ ለኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች የራስ ምታት ሆኖ ከማሳለፉ በዘለለ ቡድኑ ምንም እንኳን የሦስት ነጥብ ባለ ዕድል ባይሆንም በአቻ ውጤት ሲፈፅም ሁለት ግሩም ጎሎችን ማስቆጠሩ የሳምንቱ ምርጥ ቦታን ሊያገኝ ችሏል።

\"\"

አሰልጣኝ – መሳይ ተፈሪ

አርባምንጭ ከተማ በመቀመጫ ከተማው የሚጫወተው ድሬዳዋ ከተማን ሲገጥም ቀድሞ ግብ ማስተናገዱ እና እስከ 13ኛው ሳምንት በደካማ ውጤት ውስጥ መቆየቱ ጨዋታውን በሽንፈት እንደሚጨርስ የሚያስገምት ነበር። ሆኖም በሁለተኛው አጋማሽ ውጤታማ የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ እና የቡድኑን የማጥቃት ኃይል በመጨመር ከመመራት ተነስቶ እንዲያሸንፍ ሆኗል። በዚህ ሂደት ትልቁን ድርሻ የተወጠት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪም የሳምንቱ ምርጥ አሰልጣኝ ሆነዋል።

ተጠባባቂዎች

ባህሩ ነጋሽ – ቅዱስ ጊዮርጊስ
ተስፋዬ መላኩ – ወልቂጤ ከተማ
ዓለምብርሀን ይግዛው – ፋሲል ከነማ
መስዑድ መሐመድ – አዳማ ከተማ
እንዳልካቸው መስፍን – አርባምንጭ ከተማ
ሀቢብ ከማል – ኢትዮጵያ መድን
ፍፁም ጥላሁን – ባህር ዳር ከተማ
የኋላሸት ሰለሞን – ወልቂጤ ከተማ
ተመስገን ደረሰ – አርባምንጭ ከተማ