መረጃዎች | 59ኛ የጨዋታ ቀን

የ15ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎችን እንደሚከተለው አሰናድተናል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ሀዋሳ ከተማ

በእስካሁን የሊጉ ጨዋታዎች ዕኩል 17 ግቦችን ያስቆጠሩት አርባምንጭ እና ሀዋሳ በኃይቆቹ ብልጫ በአምስት ደረጃ እና በአራት ነጥቦች ርቀት ላይ ሆነው ነገ የ15ኛውን ሳምንት የመጀመሪያ ጨዋታ ያደርጋሉ።

አዞዎቹ በ14ኛው ሳምንት ከሦስት ተከታታይ አቻዎች በኋላ ድል ቀንቷቸው ከአደጋው ዞን በጥቂቱም ቢሆን ፈቀቅ ብለዋል። ድንቅ ሁለተኛ አጋማሽ ባሳለፉበት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን ከኋላ ተነስተው 3-1 የረቱበት አኳኋን ለነገውም ፍልሚያ ጥሩ የሥነልቦና ስንቅ የሚሆን ይመስላል። ለተከታታይ ጨዋታ ሦስት ግቦችን ማስቆጠረቸው ሌላኛው የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድን ወቅታዊ ጠንካራ ጎን ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ሲሆን ለወትሮው በመከላከል ጥንካሬው የሚታወቀው ቡድን ለአራት ጨዋታዎች መረቡን ሳያስደፍር መውጣት አለመቻሉ በድክመት የሚወሰድ ነው።

ሀዋሳ ከተማ በሰንጠረዡ አጋማሽ ላይ ይገኛል። ቡድኑ ወደ ላይኛው ፉክክር ለመቅረብ የሚያደርገው ጥረት አሁን ላይ ወጥ አቋም እያሳየ ባለመገኘቱ ፍሪያማ እየሆነ አይገኝም። ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሦስት ግቦችን ብቻ ማስቆጠሩ ደግሞ ዋነኛው የኃይቆቹ ድክመት ይመስላል። ከኢትዮ ኤሌክትሪኩ የ1-0 ድል በኋላ ሁለት ተከታታይ የአቻ ውጤቶችን ያስመዘገበው ሀዋሳ ከተማ በሊጉ እስካሁን ከፍተኛ (7) የዕኩል ለዕኩል ውጤቶችን ካስመዘገበው አርባምንጭ ከተማ ጋር እንደምገጠሙ በቅርብ ጨዋታዎች በግብ ፊት የሚታይበትን ደካማ አጨራረስ ማስተካከል ለነገው ፍልሚያ ዋነኛ ትኩረቱ ይመስላል።

\"\"

አርባምንጭ ከተማ ከነገው ጨዋታ በፊት የጉዳት ዜና የሌለበት ሲሆን ሱራፌል ዳንኤልን በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ያጣል። ከዚህ ውጪ በግል ልምምድ እየሰሩ የሚገኙት አቤል ማሞ እና አዩብ በቀታም በነገው ስብስብ ውስጥ አይገኙም። በሀዋሳ ከተማ በከል የቀዶ ጥገና ያደረገው ብርሀኑ አሻሞ እና በብሔራዊ ቡድን ጉዳት የገጠመው ወንድማገኝ ኃይሉ እንዲሁም ወጣቱ ግብ ጠባቂ ምንተስኖት ጊምቦ በጉዳት አይኖሩም።

ቡድኖቹ እስካሁን 16 ጊዜ የመገናኘት ታሪክ አላቸው። ከዚህ ውስጥ ስድስቱ ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ ሀዋሳ ከተማ ስድስት ጊዜ አርባምንጭ ደግሞ አራት ጊዜ ድል ቀንቷቸዋል። በጨዋታዎቹ ከተቆጠሩ ግቦች 18ቱ የሀዋሳ 14ቱ ደግሞ የአርባምንጭ ሆነው ተመዝግበዋል።

ጨዋታውን ኢንተርናሽናል ዳኛ በላይ ታደሰ በመሀል ዳኝነት ፣ ሶርሳ ዱጉማ እና መሐመድ ሁሴን በረዳት ዳኝነት ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

አዳማ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

ምሽት ላይ የሚከናወነው ይህ ጨዋታ በተራራቀ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቡድኖችን ያፋልማል። ሆኖም በሊጉ እስካሁን ካላቸው የእርስ በርስ ግንኙነት ታሪክ አንፃር ጨዋታው ቀላል የማይባል ፉክክር እንደሚደረግበት ይጠበቃል።

በመቀመጫ ከተማቸው ቀጣይ ጨዋታዎቻቸውን የማድረጋቸው ውጥን ያልሰመረላቸው አዳማዎች የዳግም ድሬ ቆይታቸውን ከኢትዮጵያ መድን ጋር ነጥብ በመጋራት ጀምረዋል። በ15 ነጥቦች በወራጅ ቀጠናው ውስጥ የሚገኘው አዳማ በመጨረሻ ባደረጋቸው አራት ጨዋታዎች ሽንፈት አለማስተናገዱ በበጎ የሚነሳለት ነው። ከአጠቃላይ የነጥብ ስብስቡ ግማሹን በእነዚህ ጨዋታዎች ላሳካው አዳማ ከመድኑ ጨዋታ አስቀድሞ በሦስት ዘጠና ደቂቃዎች ግብ አለማስተናገዱ የቡድኑ የመከላከል አወቃቀር ላይ መሻሻሎች እንዳሉ የሚጠቁም ነው። በተመሳሳይ ግብ በማስቆጠሩ በኩልም ጥሩ ዕምርታን ያሳየ ቢሆንም ራሱን ከስጋት ለማላቀቅ ግን የነገውን የወልቂጤን ፍልሚያ ጨምሮ ለመጪዎቹ ሳምንታት ወጥ አቋም የማሳየት ግዴታ ውስጥ ይገኛል።

በንፅፅር ጥሩ የሊግ አጀማመር የነበራቸው ወልቂጤ ከተማዎች ለአምስት ሳምንታት ከድል ጋር ከተራራቁ በኋላ ወላይታ ድቻን በመርታት ሙሉ ሦስት ነጥብ አሳክተዋል። ለተከታታይ ሁለተኛ ጊዜ ግብ ሳይቆጠርባቸው የወጡት ሠራተኞቹ የ12ኛ ደቂቃዋን የኋላሸት ሰለሞን ግብ አስጠብቀው በድል መጨረሳቸው በመከላከሉ ረገድ ለነገው ጨዋታ የሚተርፍ መስመር ላይ ስለመገኘታቸው መናገር ይቻላል። የአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ ቡድን ከድቻው ድል የሚወስደው ሌላው በጎ ነገር ከጌታነህ ከበደ ውጪ ባሉ ተጫዋቾቹ ግቦች ድል አስመዝግቦ የመውጣቱ ጉዳይ ነው። ቡድኑ ይበልጥ ራሱን ወደ ፉክክሩ ለማስጠጋትም በሌሎች የሜዳ ክፍሎች ላይ ከሚሰለፉ ተጫዋቾችም ግቦችን ይፈልጋል።

\"\"

የወልቂጤ ከተማዎቹ ቴዎድሮስ ሰሙ እና አንዋር ዱላ በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጪ ሲሆኑ ሮበርት ኢዶንካራም ቡድኑን አልተቀላቀለም። በአዳማ ከተማ በኩል ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ የራቀው ዳዋ ሆቴሳ እና አማኑኤል ጎበና የነገው ጨዋታ በጉዳት ሳቢያ የሚያመልጣቸው ሲሆን የዲሲፕሊን ጥሰት ፈፅመው የተገኙት ዊልያን ሰለሞን ፣ አሜ መሐመድ እና አብዲሳ ጀማል ደግሞ ከቡድኑ ስብስብ ተነጥለው ከክለቡ አመራሮች የሚተላለፍባቸውን አስተዳደራዊ ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ መሆኑን ተከትሎ ነገ ለቡድናቸው ግልጋሎት አይሰጡም።

በሊጉ ታሪካቸው አራት ጨዋታዎችን ያደረጉት ሁለቱ ቡድኖች ሦስት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። የመጀመሪያ ግንኙነታቸውን ማሸነፍ የቻለው ወልቂጤ ከተማ ሦስት ግቦች እንዲሁም አዳማ ከተማ ሁለት ግቦችን አስመዝግበዋል።

ጨዋታው በኢንተርናሽናል ዳኛ ሊዲያ ታፈሰ መሪነት ሲደረግ ዳንኤል ጥበቡ እና የመጀመሪያ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታውን የሚያደርገው ሚፍታ ሁሴን ረዳቶች ፣ አዳነ ወርቁ አራተኛ ዳኛ ሆነው ተመድበዋል።