አዳማ ከተማ ተሽሎ በቀረበበት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማን 3ለ1 በመርታት አንደኛውን ዙር ፈፅሟል።
ወልቂጤ ከተማዎች ወላይታ ድቻ ላይ ድል ሲቀናጁ የተጠቀሙበትን ቋሚ አሰላለፍ ሳይለውጡ ለጨዋታው ሲቀርቡ አዳማ ከመድኑ ጨዋታ አንፃር በአራቱ ላይ ለውጥ አድርጓል። በቅጣት በሌለው ሚሊዮን ሰለሞን ምትክ እዮብ ማቲዮስን ፣ በአማኑኤል ጎበና አድናን ረሻድን ፣ በዲሲፕሊን ምክንያት የታገዱት አብዲሳ ጀማል እና አሜ መሐመድን ደግሞ በዮሴፍ ታረቀኝ እና አቡበከር ወንድሙን ተተክተው ለጨዋታው ቀርበዋል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አዳማ ከተማዎች በመስመር ላይ ባደረጉት ግሩም የሆነ እንቅስቃሴ የጀመረ ነበር። 2ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ታረቀኝ ከቀኝ መስመር ወደ ግብ ክልል ሲያሻማ ቦና አሊ ኳሷ መሬቱን ሳትነካ በፍጥነት ወደ ግብ በመታት እና ጀማል ጣሰው በተቆጣጠራት ፈጣን አጋጣሚ ጉዞውን ቀጥሏል። ወጣቱ ዮሴፍ ታረቀኝ በተሰለፈበት የቀኝ ኮሪደር በኩል ይበልጥ መነሻቸውን አድርገው ሲንቀሳቀሱ አስተውለናል። አዳማዎች 7ኛው ደቂቃ ላይም ተስፋዬ መላኩ በመስዑድ መሐመድ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ የተገኘን የቅጣት ምት አቡበከር ወንድሙ በቀጥታ ወደ ጎል ሲመታ ጀማል በቀላሉ የያዘች ሁለተኛዋ ሙከራቸው ሆናለች። ደቂቃዎች እየገፉ ሲመጡ በአዳማ በእንቅስቃሴ በመበለጣቸው በቅብብል ወቅት የሚፈጠሩ ስህተቶትን በመጠቀም በተወሰነ መልኩ ቅኝት ውስጥ ለመግባት የሞከሩት ወልቂጤ ከተማዎች 13ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ የሜዳው ክፍል አቡበከር ሳኒ የደረሰው ኳስ ጥሩ አቋቋም ላይ ለነበረው ጌታነህ ሲያቀብለው አጥቂው ወደ ጎል በቀጥታ አክርሮ ሲመታው ሰይድ ሀብታሙ በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቶበታል።
ከፉክክር አንፃር የተገደበ ቢመስልም መሀል ሜዳ ላይ መስዑድ እና አድናንን በመጠቀም ለሁለቱ የመስመር አጥቂዎች ኳስን በማድረስ ዮሴፍ እና አቡበከርን በይበልጥ ተጠቅመው የወልቂጤን የተከላካይ ክፍል ለመስበር ተደጋጋሚ ትጋቶች ያልተለያቸው አዳማ ከተማዎች 21ኛው ደቂቃ ላይ መነሻዋን ከዮሴፍ ያደረገች እና ቦና አስቆጥሮ ከጨዋታ ውጪ የተባለበት እንዲሁም ደግሞ 23ኛው ደቂቃ ላይ አድናን ከአቡበከር ጋር በግራ የወልቂጤ የግብ አካባቢ አንድ ሁለት ተቀባብለው በመጨረሻም መስዑድ ጎል ላይ መቶ ስትመለስ ቦና በግንባሩ ገጭቶ በቀላሉ አስቆጠረው ሲባል ወደ ላይ የሰደዳት አፋጣሚ ጥሩ ነበሩ። የሚያገኙትን አጋጣሚ ለመጠቀም በፈጣን መልሶ ማጥቃት ከመጫወት ወደ ኋላ የማይሉት ወልቂጤዎች 35ኛው ደቂቃ ከጀሚል ጀርባ የኋላሸት ሰለሞን የጣለውን ኳስ አቡበከር ሳኒ ተቆጣጥሮ ያዘጋጀለትን በቀጥታ ጌታነህ መቶ ሰይድ ሀብታሙ ለሁለተኛ ጊዜ በድጋሚ መልሶበታል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ ግን ጨዋታው ጎል አስመልክቶናል። ከማዕዘን ምት መስዑድ በጥሩ ዕይታ የሰጠውን ኳስ ወጣቱ ዮሴፍ ታረቀኝ ኳሷ አየር ላይ እንዳለች ወደ ጎል ሲመታት በብዙአየው ሰይፉ ተጨርፋ መረብ ላይ አርፋ አዳማዎች መሪ ሆነው አጋማሹ ተገባዷል።
ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ ወልቂጤ ከተማዎች ክፍተት በተስተዋለበት የመሀል ሜዳ ክፍላቸው ላይ ብዙአየው ሰይፉን በአፈወርቅ ሀይሉ ሲተኩ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻው ደቂቃ ላይ ጉዳት በገጠመው አቡበከር ሳኒ ምትክ ተመስገን በጅሮንድ በማስገባት ጨዋታውን ለመቆጣጠር ያለሙ ቢመስልም አምስት ያህል ደቂቃዎችን ጨዋታው እንደ ተጓዘ ግን ሁለተኛ ጎል አስተናግደዋል። ከቅጣት ምት ቦና አሊ ወደ ጎል በቀጥታ ሲመታ ተቀይሮ የገባው አፈወርቅ ሀይሉ ኳስን በእጅ በሳጥኑ ውስጥ በመንካቱ የመሀል ዳኛዋ ሊዲያ ታፈሰ የሰጠችውን የፍፁም ቅጣት ምት ደስታ ዮሐንስ ከመረብ በቀላሉ አገናኝቶ አዳማን ወደ 2ለ0 አሸጋግሯል። ወልቂጤዎች የሳሳውን የአማካይ እና የአጥቂ ክፍልን ለማረም ተጨማሪ ቅያሪዎችን ቢያደርጉም የሁለተኛዋ ጎል መቆጠር ቡድን ይበልጥ ያወረደች ስትሆን አዳማ ከተማዎች በበኩላቸው ተጨማሪ ግቦችን ለማግኘት የቦና አሊን ሚና ለመጠቀም በድግግሞሽ ጥረት አልተለያቸውም።
ወደ ጨዋታ ለመመለስ መልሶ ማጥቃትን የመጨረሻዎቹን ሀያ ደቂቃዎች የተጠቀሙት ወልቂጤ ከተማዎች 72ኛው ደቂቃ ላይ በራሳቸው የግብ ክልል ቢኒያም አይተን ጌታነህ ከበደ ላይ ጥፋት በመስራቱ በረዳት ዳኛው ዕገዛ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ራሱ ጌታነህ የውድድር ዓመቱ 11ኛ ጎሉ አድርጎታል። ጎል ካስቆጠሩ በኋላ ወልቂጤዎች በተደጋጋሚ ወደ አዳማ የግብ ክልል መድረስ ቢችሉም በመልሶ ማጥቃት 86ኛዎ ደቂቃ ላይ አዳማ ከተማዎች ከግራ መነሻዋን አድርጋ የመጣችን ኳስ መስዑድ ለቦና ሰጥቶት ቦናም በቀጥታ መቶት ጀማል ሲተፋው መስዑድ የተተፋውን ለቢኒያም አቀብሎት ወጣቱ አጥቂ ሦስተኛ ጎል አድርጓት ጨዋታው 3ለ1 ተጠናቋል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የወልቂጤ ከተማው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የተጫዋቾች የዕረፍት ጊዜ ማነስ ድካም እንደፈጠረባቸው እና በመጀመሪያው አጋማሽ በመስመር የመረጡትን አጨዋወት አለመተግበራቸው ድል ላለማስመዝገባቸው እንደ ዋና ምክንያት ሲያቀርቡ የውድድሩ የመጀመሪያ ዙር ቡድኑ ካሉበት በርካታ ችግሮች አንፃር ስኬታማ እንደነበር በተጨማሪም በቀጣይ ጨዋታዎች ለተጋጣሚያቸው ብለው የሚቀይሩት የጨዋታ መንገድ እንደሌለ አበክረው ገልጸዋል። ድል የቀናው አዳማ ከተማ አሰልጣኝ ይታገሡ እንዳለ በበኩላቸው ተጋጣሚያቸው ጠንካራ እንደሆነ ሲገልጹ በተለይም በታዳጊ ተጫዋቾች ማመን እንደሚገባ እና በውድድሩ የመጀመሪያ ዙር ውጣ ውረድ ቢያጋጥማቸውም ቡድኑ የያዘውን የጨዋታ መንገድ ሳይለቅ መቆየቱን ሲናገሩ ያሉበት ደረጃ እንደማይመጥናቸው ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።