መረጃዎች | 60ኛ የጨዋታ ቀን

የአንደኛ ዙር የመጨረሻ የጨዋታ ሳምንት ሁለተኛ የጨዋታ ቀን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ ፅሁፋችን ቀርበዋል።

ሀዲያ ሆሳዕና ከኢትዮጵያ መድን

የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር በሰንጠረዡ አናት በስድስት ነጥቦች ልዮነት 2ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙትን ኢትዮጵያ መድኖችን 4ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ያገናኛል።በ27 እና 21 ነጥቦች ላይ የሚገኙትን ሁለቱን ቡድኖች የሚያገናኘው ጨዋታ እኩሌታው ላይ በደረሰው የሊግ ውድድር ቡድኖቹ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ በሚኖራቸው ጉዞ ላይ በቅርብ ርቀት የሚገኝ ተጋጣሚ ላይ የሚገኝ ድል ከሚኖረው ጠቀሜታ አንፃር በከፍተኛ ትኩረት እንደሚያደርጉት ይጠበቃል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 በተረቱበት ጨዋታ ግብ ማስቆጠር ያልቻሉት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሊጉ የመጨረሻ ግባቸውን ካገኙ 417 የጨዋታ ደቂቃዎች ተቆጥረዋል።እንደ ቡድን የቡድኑ የማጥቃት ጨዋታ ከፍተኛ የጥራት ችግር እንዳለበት እያስተዋልን የምንገኝ ሲሆን በግል ግን በተለይ ፀጋዬ ብርሃኑ በመጨረሻው ጨዋታ ያሳየው እንቅስቃሴ ተስፋ የሚጣልበት ነበር።

አሁንም ቢሆን ከቅዱስ ጊዮርጊስ እኩል 8 ግቦችን ብቻ በማስተናገድ የሊጉን ጠንካራውን መከላከል በጣምራ የሚመሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች አሁንም ከጨዋታዎች ነጥቦችን ለማግኘት ከማጥቃታቸው ይልቅ በመከላከላቸው ላይ አብዝተው ይተማመናሉ።

\"\"

ሀድያ ሆሳዕናዎች በነገው ጨዋታ ግርማ በቀለን ከቅጣት መልስ የሚያገኙ ሲሆን በአንፃሩ ቤዛ መድህን ግን በጉዳት ምክንያት አይኖርም።

በሊጉ ከአስደናቂ ጉዟቸው ማግስት ተደጋጋሚ የአቻ ውጤቶችን እያስመዘገቡ የሚገኙት ኢትዮጵያ መድኖች በመጨረሻ ካደረጓቸው አምስት የሊግ ጨዋታዎች በሦስቱ ነጥብ ተጋርተው ለመውጣት ተገደዋል ፤ በተለይ በመጨረሻ ጨዋታቸው ከአዳማ ከተማ ጋር ነጥብ የጣሉበት መንገድ ደግሞ ለአሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ እምብዛም ምቾት የሚሰጥ እንደማይሆን ይጠበቃል።

ሁለት አቻ በተጠናቀቀው ጨዋታ በሁለት አጋጣሚዎች መምራት ቢችሉም መሪነታቸውን ማስጠበቅ ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን ምስጋና ለግብ ጠባቂያቸው አቡበከር ኑራ ይግባ እንጂ ሽንፈትም ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር ታድያ ነገሩን ደግሞ ከባድ የሚያደርገው ይህ የሆነው ከ40 በላይ ደቂቃዎችን በጎዶሎ ተጫዋች ከተጫወተ ተጋጣሚ ጋር መሆኑ ነው።

በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ላይ ግቦችን በማስቆጠር ሆነ አመቻችቶ በማቀበል ጥሩ ጊዜያትን ያሳለፈው ኪቲካ ጅማ ከሰሞኑ መጠነኛ የብቃት መቀዛቀዝ ላይ ያለ ይመስላል ፤ ነገርግን በዚህ ወቅት ደግሞ መድኖች ሌላ ጀግና ያገኙ ይመስላል በክረምቱ ከአርባምንጭ ከተማ መድንን የተቀላቀለው ሀቢብ ከማል ከሰሞኑ የሚያቆመው አልተገኘም። ቡድኑ በሊጉ ባደረጋቸው የመጨረሻ ስድስት ጨዋታዎች በአጠቃላይ ካስቆጠራቸው የመጨረሻ ስድስት ግቦች አምስቱ (83%) የሚሆኑት ኳሶች የተቆጠሩት በሀቢብ ከማል ስም ሲሆን በዚህም በአጠቃላይ በሊጉ ያስቆጠራቸውን የግብ ብዛቶች 7 በማድረስ በከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ዝርዝር ውስጥ ራሱን ማካተት ችሏል።

በኢትዮጵያ መድን በኩል ረዘም ላለ ጊዜ በጉዳት ከጨዋታ ከራቀው ሳሙኤል ዮሀንስ በተጨማሪ የግራ መስመር ተከላካዩ ያሬድ ካሳዬ ከነገው ጨዋታ ውጭ መሆኑ ታውቋል።

10 ሰዓት ላይ ጅማሮውን የሚያደርገውን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኢንተርናሽናል ዳኛ አሸብር ሰቦቃ በዋና ዳኝነት ሲመራው ፣ ታምሩ አደም እና እሱባለው መብራቱ በረዳትነት እንዲሁም ኢያሱ ፈንቴ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት እንደሚመሩት ይጠበቃል።

ለገጣፎ ለገዳዲ ከመቻል

የምሽቱ መርሃግብር ደግሞ በሊጉ ግርጌ የሚገኙትን ለገጣፎ ለገዳዲዎችን አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው መቻል የሚያገናኝ ይሆናል።

በሊጉ ብቸኛ ድላቸውን ካስኩ 13 የጨዋታ ሳምንታትን ያስቆጠሩት እንዲሁም የመጨረሻ ነጥባቸውን ካሳኩ ደግሞ 3 የጨዋታ ሳምንታትን ያሳለፉት ለገጣፎ ለገዳዲዎች በአዲሱ አሰልጣኛቸው ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ እየተመሩ ያደረጉት የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታቸውን እንዲሁ 2-0 በሆነ ውጤት በሲዳማ ቡና ተረተዋል።

በሊጉ እስካሁን 29 የተለያዩ ተጫዋቾችን የተጠቀመው ቡድኑ በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸውን ተጫዋቾችም በነገው ጨዋታ መጠቀም የማይችል ይሆናል።

ለገጣፎ ለገዳዲዎች በነገው ጨዋታ በጉዳት መሀመድ አበራን ከማጣታቸው ውጭ በተሟላ ስብስብ የነገውን ጨዋታ የሚያደሬጉ ይሆናል።

በብዙ መመዘኛዎች ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች መሻሻሎችን እያሳዩ የሚገኙት መቻሎች በመጨረሻ ጨዋታቸው ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ሦስት አቻ ሲለያዩ በሙሉ ዘጠና ደቂቃ የነበራቸው የማሸነፍ ፍላጎት እና ትጋት እጅግ አስገራሚ ነበር።

\"\"

በተለይ በቂ ግቦችን በማስቆጠር ረገድ ድክመት የነበረበት ቡድኑ የእሁዱን ጨዋታ ጨምሮ ባደረጓቸው የመጨረሻ አራት የሊግ ጨዋታዎች ዘጠኝ ግቦች ማስቆጠራቸው ስለቡድኑ መሻሻል ጠቋሚ እውነታ ነው።ይህም ማለት ቡድኑ እስካሁን በሊጉ በድምሩ ካስቆጠራቸው 15 ግቦች (60%) የሚሆኑት የተቆጠሩት በእነዚሁ አራት የመጨረሻ ጨዋታዎች ነው።

ነገርግን ቡድኑ አሁንም በተለይ በመከላከሉ ረገድ ያሉበት እንደ ቡድን የመከላከል ድክመት ግን እንደቀጠለ ነው። በአማካይ በጨዋታዎች ከ1.2 ገድማ ግቦችን እያስተናገደ የሚገኘው ቡድኑ መከላከሉን ይበልጥ ጠበቅ ማድረግ ይኖርበታል።

በመቻል በኩል ምንይሉ ወንድሙ ፣ ዳዊት ማሞ በጉዳት የማይኖሩ ሲሆን የተሾመ በላቸውም መሰለፍ ነገር አጠራጥሏል።ነገርግን ሁለገቡ አማካይ ግሩም ሀጎስ ከጉዳት የማገገሙ ነገር ለአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ መልካም ዜና ነው።

የምሽቱን መርሃግብር ሰለሞን አሸብር በታሪኩ የመጀመሪያ የሊግ ጨዋታውን እንዲመራ ሲመደብ አስቻለው ወርቁ እና ማህደር ማረኝ በረዳትነት ፣ ኢንተርናሽናል ዳኛ ማኑሄ ወልደፃዲቅ አራተኛ ዳኛ በመሆን ይመሩታል።