ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ጣፋጭ ድል አስመዝግቧል

በዕለቱ ቀዳሚ መርሐ ግብር ኢትዮጵያ መድን በያሬድ ዳርዛ የ95ኛ ደቂቃ ግብ ሀዲያ ሆሳዕና ላይ የ1-0 ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል።

10፡00 ሲል የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ በሀዲያ ሆሳዕና እና ኢትዮጵያ መድን መካከል ሲደረግ ነብሮቹ በ14ኛ ሳምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ 1-0 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ፍሬዘር ካሳ በቃለአብ ውብሸት ባዬ ገዛኸኝ ደግሞ በሪችሞንድ ኦዶንጎ ተተክተው ጀምረዋል። በአንጻሩ ኢትዮጵያ መድኖች በ14ኛ ሳምንት ከአዳማ ከተማ ጋር 2-2 ሲለያዩ የተጠቀሙትን አሰላለፍ ሳይለውጡ ገብተዋል።

\"\"

መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ገና በሁለተኛው ደቂቃ ለግብ የቀረበ ሙከራ በነብሮቹ በኩል አስመልክቶናል። ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን ከፀጋዬ ብርሃኑ በተቀበለው ኳስ ከተጋጣሚ ሳጥን አጠገብ አክርሮ በመምታት ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው አቡበከር ኑራ በግሩም ቅልጥፍና መልሶበታል። በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ሀዲያዎች 13ኛው ደቂቃ ላይም በፀጋዬ ብርሃኑ ተጨማሪ ሙከራ ማድረግ ሲችሉ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው የተመለሱት መድኖች በአጋማሹ የተሻለውን ሙከራ 16ኛው ደቂቃ ላይ አድርገዋል። ሀቢብ ከማል የግል ክህሎቱን ተጠቅሞ ተከላካዮችን አታልሎ በማለፍ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ በኳሱ አቅጣጫ የነበረው ግብ ጠባቂው ፔፔ ሰይዶ ይዞበታል።

ጨዋታው በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ተጋግሎ ሲቀጥል 21ኛው ደቂቃ ላይ የአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ቡድን ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር። ብርሃኑ በቀለ ተቀዛቅዞ በነበረው የቀኙ የማጥቃት ክፍላቸው ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ውስጥ ሲያሻግር ኳሱን ሳይዘጋጅ ያገኘው ተመስገን ብርሃኑ በደካማ አጨራረስ ወርቃማውን ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በርካታ ስኬታማ ቅብብሎችን በማድረግ ለመውጣት የሚሞክሩት መድኖች አሚር ሙደሲር ከቅጣት ምት ካደረገው ዒላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ውጪ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ይባስ ብሎም 35ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስተናገድ ተቃርበው ነበር። ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን በግሩም ዕይታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ባዬ ገዛኸኝ ከግብ ጠባቂ ጋር ቢገናኝም ሳይረጋጋ አክርሮ በመምታት ያደረገው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። ይህም በሀዲያዎች በኩል ሌላኛው አስቆጪ አጋጣሚ ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል 56ኛው ደቂቃ ላይ የሀዲያ ሆሳዕናው ተከላካይ ፍሬዘር ካሳ ሳይመን ፒተር ላይ በሰራው ጥፋት በሁለት ቢጫ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ በተጫዋች ቁጥር ብልጫ የተወሰደባቸው የማይመስሉት ነብሮቹ በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ፍቅረየሱስ ተወልደብርሃን በመጀመሪያው አጋማሽ ካደረገው ሙከራ በተመሳሳይ ከሳጥን አጠገብ አክርሮ በመምታት ግሩም ሙከራ ቢያደርግም የወቅቱ ምርጥ ግብ ጠባቂ አቡበከር ኑራ በግሩም ቅልጥፍና መልሶበታል።

በተጫዋች ቁጥር ያገኘውን ብልጫ የታሰበውን ያህል ያልተጠቀመው የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ቡድን ተቀዛቅዞ በቀረበበት የሜዳ ክፍል የተጫዋቾች ቅያሪ በማድረግ የተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማሳየት ሲሞክር ተቀይሮ የገባው ብሩክ ሙሉጌታ ከራሳቸው የሜዳ ክፍል የተሻማውን ኳስ በሌላ ተጫዋች ተጨርፎ አግኝቶት ያደረገውን ሙከራ ከግብ ክልሉ በጥሩ የጊዜ አጠባበቅ የወጣው ግብጠባቂው ፔፔ ሰይዶ መልሶበታል።

\"\"

ጨዋታው በተደጋጋሚ በሚከሰቱ አካላዊ ንክኪዎች እየተቀዛቀዘ ሲሄድ ነብሮቹ ውጤቱን አስጠብቆ ከጨዋታው አንድ ነጥብ ለመውሰድ ከራሳቸው የግብ ክልል በቁጥር በዝተው በመገኘት መከላከልን ሲመርጡ መጠነኛ መነቃቃት ታይቶበታቸው የነበሩት መድኖችም ባልተረጋጋ የማጥቃት እንቅስቃሴ የጠራ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ሆኖም ጨዋታው ሊጠናቀቅ የዋና ዳኛው አሸብር ሰቦቃ ፊሽካ ሲጠበቅ 95ኛው ደቂቃ ላይ ባሲሩ ኡማር በድንቅ ዕይታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ያገኘው ተቀይሮ የገባው ያሬድ ዳርዛ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥሮት ኢትዮጵያ መድንን የ1-0 ጣፋጭ ድል ባለቤት አድርጓል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የሀዲያ ሆሳዕናው አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በመጀመሪያው አጋማሽ የተሻሉ ሆነው የግብ ዕድሎችን መፍጠራቸውን ሲናገሩ የተቆጠረባቸውን ግብ ከተጨመረው ደቂቃ በላይ ተጫውተው መቆጠሩ እንዳስከፋቸው እና በጨዋታው ሦስት ነጥብ ይገባቸው እንደነበርም ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። ድል የቀናቸው የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ በበኩላቸው ከዕረፍት መልስ ያደረጓቸው ቅያሪዎች ውጤታማ እንደነበሩ ሲናገሩ ሜዳ ላይ የታየው የተጋጣሚ ቡድን ዲስፕሊን ጥሩ አለመሆን ንዴት ውስጥ ከቷቸው እንደነበር እና ያሳዩት የደስታ አገላለጽ ምክንያት ያ መሆኑንም በግልፅ ተናግረዋል።