የለገጣፎን ጉዳይ በተመለከተ የአክሲዮን ማኅበሩን ሥራ-አስኪያጅ አቶ ክፍሌን አናግረናል

👉\”ጉዳዩ የህግ አተረጓጎም ችግር ነው\”

👉\”ሁለተኛ ዙር ላይ የሚመዘገበው ተጫዋች ሁለተኛ ዙር ውድድር ላይ እንደሚጫወት ነው የሚታወቀው\”

👉\”ጨዋታውን ተከትሎ የሚመጣውን የህግ አፈፃፀም በሂደት የምናየው ነው። የፊፋን ህግ ተከትሎ የተቀመጡ ደንቦች እና መመሪያዎች አሉ ፤ በእነሱ መሰረት በባለሙያዎች የሚታይ ይሆናል\”

ከ15ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነው የለገጣፎ ለገዳዲ እና መቻል ጨዋታ ከፍተኛ ውዝግብ ማስነሳቱ ይታወቃል። ለገጣፎ የመጀመሪያው ዙር የሊጉ ውድድር ሳይገባደድ በሁለተኛው ዙር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸውን ተጫዋቾች በጨዋታው ለመጠቀም በአሰላለፉ ውስጥ አስገብቶ ወደ ሜዳ ሊገባ ሲል የሊጉ አስተዳዳሪ ተጫዋቾቹን መጠቀም እንደማይችል ገልፆ ጨዋታው በመቻል የፌርፌ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል። ጉዳዩን በተመለከተ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በኩል ያለውን ሀሳብ ከሰዓታት በፊት ያቀረብን ሲሆን አሁን ደግሞ በሊጉ አስተዳደር በኩል ያለውን ነገር ለአንባቢያን እናደርሳለን። በዚህም በጉዳዩ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍሌ ሰይፈ ጋር ቆይታ አድርገናል።

\"\"

ጉዳዩ \”የህግ አተረጓጎም ችግር\” ነው ያሉት አቶ ክፍሌ ሊግ ካምፓኒው ፌዴሬሽኑን የሁለተኛ ዙር የዝውውር መስኮት እንዲከፈት ጠይቆ በከፈተው መሰረት 7 ክለቦች ዝውውር መፈፀማቸውን አንስተዋል። ይህንን ተከትሎም ተቋማቸው አዲስ ፈራሚ ተጫዋቾችን ክለቦች ከ16ኛ ሳምንት ጀምሮ መጠቀም እንዲጀምሩ በደብዳቤ ማሳወቁን አስረድተዋል።

በሊግ ካምፓኒው ዘንድ የሁለተኛ ዙር ዝውውር ስለሆነ ክለቦች አዲስ ተጫዋቾችን መች መጠቀም እንደሚገባቸው ያውቁታል የሚል አረዳድ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ ጥያቄዎች ሲመጡ እናስታውሳቸው በሚል ደብዳቤው መፃፉን ተናግረዋል። \”ተቋሙ የሁለተኛ ዙር ዝውውር ላይ አንድ ክለብ ብዙ ተጫዋች ያዘዋውራል የሚል ግምት የለውም ፤ ከዚህ ቀደም በነበረው ልምድም ሁለት ሦስት ተጫዋች እንደሚዘዋወር ነው። በዛ ላይ የደብዳቤው ሀሳብ አንድን ክለብ ለመጉዳት የወጣ አይደለም። እንዳይዘነጉት ለማስታወስ የወጣ ደብዳቤ ነው። ለገጣፎ ደግሞ ወደ ሰባት ስምንት ተጫዋቼች አዘዋውረዋል። እርግጥ እውነት ነው ብዙ ስላዘዋወሩ ይጎዳሉ። ግን ሁለተኛ ዙር ላይ የሚመዘገበው ተጫዋች ሁለተኛ ዙር ውድድር ላይ እንደሚጫወት ነው የሚታወቀው።\” ብለዋል።

በተጨማሪ አቶ ክፍሌ የዝውውር መስኮቱ ቀድሞ የተከፈተው ብሔራዊ ቡድኑ የማጣሪያ ጨዋታ ምክንያት ሊጉ ዘንድሮ ብዙ የሚቆራረጥ በመሆኑ ክለቦች ነፃ በሆኑበት ሰዓት ተጫዋቾችን ያዘዋውሩ በሚል እንደሆነ አንስተዋል። \”ይህን ስንጠይቅ ደግሞ ፌዴሬሽኑ \’አይሆንም\’ ማለት ይችል ነበር። ምክንያቱም ስልጣኑ የእሱ ስለሆነ\” ያሉት አቶ ክፍል \”የበላይ አካል ፌዴሬሽኑ ነው። ጨዋታውን ተከትሎ የሚመጣውን የህግ አፈፃፀም በሂደት የምናየው ነው። የፊፋን ህግ ተከትሎ የተቀመጡ ደንቦች እና መመሪያዎች አሉ ፤ በእነሱ መሰረት በባለሙያዎች የሚታይ ይሆናል። በዛ መንገድ መልስ ያገኛል ብለን እናስባለን።\” በማለት በቀጣይ ጉዳዩ ወዴት ሊያመራ እንደሚችል ጠቁመዋል።

ከዝውውር ተገቢነት ባለፈ በትናንትናው ዕለት ጨዋታው በፎርፌ እንዲጠናቀቅ የሆነበትን ምክንያት በተከታይነት ሲያስረዱ \”እኛ እንደተቋም የ16ቱም ክለቦች የተጫዋቾች ዳታ አለን። በዛ መሰረት ክለቡ የመጀመሪያ ዙር ላይ የተመዘገቡ አምስት ተጫዋቾች ነው ያቀረበው። ስለዚህ የጨዋታ አመራሮቹ በእግርካሱ ህግ መሰረት ከሰባት በላይ ተጫዋች ያላሰለፈ ቡድን መጫወት ስለማይችል ጨዋታው እንዳይካሄድ ወስነዋል።\” በማለት አስረድተዋል።

\"\"

በዕለቱ የመቻል ተጫዋቾች በህጉ መሰረት ሜዳ ገብተው ሠላሳ ደቂቃ ከቆዩ በኋላ የፎርፌ ውጤት አግኝተው ወጥተዋል። ይህ ሂደት ግን እንደወትሮው የቀጥታ የቴሌቭዢን ሽፋን አላገኘም። ይህንን በመንተራስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሥራ አስኪያጁ ብሮድካስት የማድረጉ ኃላፊነት የሊግ ካምፓኒው መሆኑን አስታውሰው ያልተላለፈበትን ምክንያት እንዲህ በማለት አስረድተዋል። \”በወቅቱ አለመግባባት ስለነበር ያንን ለዓለም ማሳየት ስለሌለብን ነው። ከመጀመሪያው ዳታ ከሚያስገቡ ባለሙያዎች ጋር አለመግባባት ነበር። በመሆኑም ጨዋታው ከተካሄደ ቀርፀን ለማስተላለፍ ካልሆነ ደግሞ ትናንት በሄደበት መንገድ እንዲቀጥል ነው ያደረግነው። ይህ የሆነው ሊጉን ከመጠበቅ ጋር ተያይዞ ነው።\”

በመጨረሻም ሥራ-አስኪያጁ ከለገጣፎ ጋር የተፈጠረው ችግር በተቀመጡ የፌዴሬሽኑ ህጎች በዲስፕሊን እና በይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ አለፍ ሲልም እስከ ካስ ድረስ የእግርኳስ የችግር መፍቻ ሂደትን ተከትሎ ሊፈታ እንደሚችል ጠቁመዋል። \”ስራ ሲሰራ ብዙ ክስተቶች ይኖራሉ ፤ ጠንካራም ደካማም። ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ነገሮች በደንብ በሰነድ መቀመጥ አለባቸው። አንዱም የሰነዱ ክፍተትም ስለሆነ አፈፃፀማችን ላይ ችግር የፈጠረው\” በማለት በቀጣይ ተቋሙ በቅርቡ በተደረገው ጥናት መሰረት ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ ወደ ፊት መሰል ችግሮች እንዳይፈጠሩ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።