ታክቲካዊ ትንታኔ : መከላከያ 1-0 ደደቢት

መከላከያ 1-0 ደደቢት
ቅዳሜ ህዳር 20 ቀን 2007

ካለፉት ሶስት ጨዋታዎች ሙሉ 9 ነጥቦችን ያሳካው ደደቢት ባለፈው ማክሰኞ ወላይታ ድቻን ካሸነፈበት ጨዋታ ከተጠቀመባቸው ተጫዋቾች መካከል ዳዊት ፍቃዱን በበረከት ይስሃቅ ተክቶ ከመግባቱ ውጪ ምንም ለውጥ ሳያደርግ ሲገባ መከላከያ በአንፃሩ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ካለ ግብ ከተለያየበት ጨዋታ ምንም ለውጥ ሳያደርግ ወደ ሜዳ ገብቷል፡፡

አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ በመቀጣታቸው ምክንያት በምክትል አሰልጣኙ ወደ ሜዳ የገባው መከላከያ በ4-4-2 አሰላለፍ ጀማል ጣሰውን በግብ ጠባቂነት፤ ሽመልስ ተገኝ ፣ ሲሳይ ደምሴ ፣ ተስፋዬ በቀለ እና ዮሃንስ ኃይሉን ከኋላ መስመር ፤ ተክለወልድ ፍቃዱ ፣ ሚካኤል ደስታ ፣ ሳሙኤል ታዬ እና ፍሬው ሰለሞንን በአማካይ መስመር ፤ ሙሉአለም ጥላሁን እና ሞሀመድ ናስርን በአጥቂ መስመር አሰልፈዋል፡፡

አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ በበኩላቸው እንደ መከላከያ ሁሉ በ4-4-2 አሳላለፍ (የደደቢት አማካይ ክፍል የዳይመን ድቅርፅ ሲኖረው፤ የመከላከያ ደግሞ ፍላት ነበር) በግብ ጠባቂነት ሲሰይ ባንጫን በተከላካይ መስመር ብሩክ አስጨናቂ ፣ አዳሙ ሞሃመድ ፣ አክሊሉ አየነው እና ብርሃኑ ቦጋለ ፤ በአማካይ ስፍራ ሳምሶን ጥላሁን ፣ ሽመክት ጉግሳ ፣ መስፍን ኪዳኔ እና ታደለ መንገሻ እንዲሁም በአጥቂ ስፍራ ላይ ሳሚ ሳኑሚ እና ዳዊት ፍቃዱ ተሰልፈዋል፡፡

(ምስል 1)

Dedebit 0-1 Mekelakeya (1)


የመከላከያ Narrow flat 4-4-2 vs የደደቢት diamond 4-4-2

ሁለቱም ፎርሜሽኖች በአለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ያገኙና የመደበኛው 4-4-2 አካል የሆኑ (variants) ሲስተሞች ናቸው፡፡
እንደሚታወቀው ጠባቡ ፍላት 4-4-2 መሃል ሜዳውን ተቆጣጥሮ የተጋጣሚ አማካዮች ላይ (እንደተጋጣመወው የመሃልሜዳ የአማካይ ተጫዋቾች ብዛትና የተጠቀሙት የፎርሜሽን አይነት ይለያያል) ብልጫን ለመውሰድ እንዲሁም ፉልባኮቹ የላይኛውን የሜዳ ክፍል ተጠግተው ለማጥቃት እንቅስቃሴው የማጥቃት አማራጮችን በማስፋት ፣ የመቀባበያ አማራጮችን በማብዛትና የተጋጣሚ የመስመር አማካዮችን በራሳቸው የሜዳ ክፍል እንዲገደቡ አፍነው በመያዝ (press በማድረግ) የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ለማድረግ ያስችላል፡፡
በእርግጥ አሰልጣኞች እንደየራሳቸው የጨዋታ ፍልስፍና ፣ በተጫዋቾች ጥራትና በተጋጣሚ ቡድን አጨዋወት ላይ ተመስርተው የጠባቡን 4-4-2 የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደር ሊተገብሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ፎርሜሽን በትክክል ካልተተገበረ ግን ለተጋጣሚ ቡድን የሚሰጠው የመስመር ላይ ሰፊ ክፍተት ፈጣን እና የሜዳውን መስመር ተጠግተው የሚጫወቱ የመስመር አማካዮች ባላቸው ቡድኖች ሊፈተኑ ይችላሉ፡፡

ከላይ የተጠቀሱት የጠባብ 4-4-2 ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች በመከላከያ ላይ ዘንድሮ መመልከት ይቻላል፡፡ የጦሩ የመሃል ሜዳ የበላይነት ፣ የፉልባኮች በተደጋጋሚ ለማጥቃት ወደፊት መሄድ ፎርሜሽኑ ያስገኘላቸው ጥቅም ነው፡፡ በአንፃሩ የሜዳውን ስፋት በሚጠቀሙ ክለቦች አንዳንዴ ችግር ላይ ሲወድቁ ይስተዋላል፡፡

ወደ ደደቢት ዳይመንድ ስናመራ በዚህ ፎርሜሽን በአብዛኛው በቡድናቸው የሚገኘውን ፈጣሪ የአማካይ ተጫዋች (ታደለ መንገሻ) ከሁለቱ አጥቂዎች ጀርባ በማሰለፍ የተጋጣሚ ቡድኖች ተከላካዮች ላይ ከፍተኛ ጫና እና የመከላከል ቅርፃቸው ላይ ከቅርብ ርቀት በ3 ተጫዋቾች ተፅእኖ ለማሳረፍ የሚያስችል ነው፡፡ በተጨማሪም ተጫዋቾች በመሃለኛው የሜዳ ከፍል ብዙ ሶስት ማዕዘን በመስራት የመቀባበያ አማራጮች ለማስፋት ይረዳል፡፡ (በምስል 2 ላይ በ16 ቁጥሩ ታደለ ዙርያ የተሰመሩትን መስሮች ይመልከቱ)

የደደቢት ወደ መሃል ሜዳ ተጠግቶ መከላከል


የደደቢት አራት ተከላካዮች እጅግ ወደ አማካዩ መስመር ቀርበው ሲከላከሉ ነበር፡፡የቀድሞው የመከላከያ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ይህንን ያደረጉት በአማካዩ እና በተከላከዩ መካከል ያለውን ክፍተት በማጥበብ በበርካታ ቅብብል ወደ ጎል የሚደርሰው መከላከያን የመቀባበያ አማራጭ ለማሳጣት አስበው ሊሆን ይችላል፡፡ በተጨማሪም ደደቢት ያሰለፋቸው ሁለት የመስመር አማካዮች የተለያየ ሚና ለቡድኑ መመጣጠንን አምጥቶለታል፡፡ በተለይም በመጀመርያው አጋማሽ መስፍን ኪዳኔ በግራ መስመር በኩል የሚፈጥረው ጫና ወደ ፊት በማጥቃት (overlap በማድረግ) የሚታወቀው ሽመልስ ተገኝን እንቅስቃሴ እንዲገደብና ከሳሙኤል ጋር የነበረው ግንኙነት እንዲቋረጥ አስገድዶታል፡፡ (በምስል 2 ላይ በ4 ማዕዘን የተሰመረውን ይመልከቱ..)
በተጨማሪም በማጥቃት ወቅት የመስፍን በተደጋጋሚ ወደ ውስጥ ሰብሮ መግባትና የሁለቱ አጥቂዎች ተለዋዋጭነት ባህርይ በመጀመርዎቹ 20 ደቂቃዎች መከላከያ ላይ ችግር ፈጥሮ ነበር፡፡ በተለይም በ11ኛው ደቂቃ መስፍን ወደ መሃል ሰብሮ ሲገባ ዳዊት ፍቃዱ ወደ ግራ መስመር በመውጣት ነፃ ሆኖ ኳሱን የተቀበለበትና ጥሩ የማግባት አጋጣሚ የፈጠረበት እንቅስቃሴ ለዚህ እንደ ማስረጃ ትቀርባለች፡፡

ሌላው በመጀመርያው አጋማሽ የደደቢት መልካም ጎን የነበረው የአጥቂዎቹ ሚና ነበር፡፡ ሁለቱ አጥቂዎች በመከላከል ወቅት ወደ መከላከያ የግብ ክልል በመጠጋት ተከላካዮቹ በማጥቃት እንቅስቃሴ እንዳይሳተፉ ገድበዋቸዋል፡፡ ኳስ በደደቢት እግር በምትገባበት ወቅትም እግራቸው ስር በምትገባበት ጊዜም በመከላከያ አማካዮች እና ተከላካዮች መካከል የሚፈጠረውን ሰፊ ሰፊ ርቀት የነበረ በመሆኑ በርካታ የደደቢት የማጥቃት ባህርይ ያላቸው ተጫዋቾች በመስመሮች መካከል እንዲገኙ አግዟቸዋል፡፡

ለድሉ ወሳኝ የነበረው የሁለቱ የመስመር አማካዮች እና አጥቂዎች ሚና


የመከላከያ ሁለት የመስመር አማካዮች (ሳሙኤል እና ፍሬው) እንደቀደሙት ጨዋታዎች ሁሉ በInverted winger ሚና (የቀኝ እግር ተጨዋች በግራ መስመር ፣ የግራ መስመር ተጨዋች በቀኝ መስመር) በመጫወታቸው እንደ ባለፉት ጨዋታዎች ቡድኑ የስፋት (width) ችግር እንዳይገጥመው ተፈርቶ ነበር፡፡ ነገር ግን የሁለቱ አጥቂዎች ሚና ከአማካዮቹ የሚጠበቀው ስፋትን ሲፈጥርለት ተስተውሏል፡፡

ኳስ በመከላከያ አማካዮች ስር ስትገኝ ሲገኝ ሁለቱ የመከላከያ አጥቂዎች በተደጋጋሚ ወደ መስመሮች የሚያደርጉት ሩጫ የደደቢትን የመከላከል ቅርፅ እንዲበታተንና በመሃል ተከላካዮች መካከል ሰፊ ክፍተት እንዲፈጠርና ከሁለቱ ፉልባኮች ጋር ያላቸው ክፍተት እንዲሰፋ ሲያደርግ ሁለቱ የመከላከያ የመስመር አማካዮች በክፍተቱ ተጠቅመው ወደ መሃል ሰብረው የሚገገቡበትን በር ከፍቶላቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የመከላከያ የመስመር አማካዮች በእንቅስቃሴ ወደ አጥቂነት የሚቀየሩበት አጋጣሚ ብዙ ነበር፡፡

ደደቢት ወደ ሜዳው ተጠግቶ በመጫወቱና በተከላከይ መስመሩ እና በመጨረሻዎቹ አጥቂዎች መካከል የነበረው ርቀት አጭር መሆን ለመከላከያዎች እንደ ልብ የመቀባበያ ክፍተት ባለማስገኘቱ ሁለቱ አጥቂዎች የሚበታትኑትን የተከላከይ መስመር ክፍተት ተጠቅመው በረጃጅም ኳሶች አደጋ ለመፍጠር ሞክረዋል፡፡

የደደቢት ተከላካዮች ከጀርባቸው ብዙ ቦታ ትተው (ከግብ ጠባቂው ርቀው) የሚከላከሉ በመሆኑ የመከላከያ ተጫዋቾች ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ የሚገናኙበትን እድሎችንም መፍጠር ችለው ነበር፡፡

ለአጨዋወታቸው ስኬታማ መሆን የመከላከያ አጥቂዎች ትጋት የሚጠቀስ ቢሆንም የደደቢት ፉልባኮች ከመሃልተከላካዮች ጋር ያላቸው መናበብ ዝቅተኛ መሆን በትልቁ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡ በ32ኛው ደቂቃ ሙሉአለም ጥላሁን ግብ ያስቆጠረውም በአዳሙ ሞሃመድ እና ብርሃኑ ቦጋለ መካከል ያለውን ክፍተት ተጠቅሞ ነው፡፡ (በአረንጓዴ መስመር የተሰመረውን ይመልከቱ)
መከላከያዎች ይህንን አጨዋወት ከቅዱስ ጊዮርጊሶች ጋር የተገበሩት ቢሆንም ጊዮርጊሶች ይበልጥ የመከላከል ባህርይ ያለው ሆልዲንግ አማካይ በማሰለፋቸውና በፉልባኮቹና የመሃል ተከላካዮቹ መካከል ክፍተት ላለመፍጠር በመሞከራቸው የደደቢትን ያህል አልተፈተኑም፡፡

(ምስል 2)

Dedebit 0-1 Mekelakeya (2)


በሁለተኛው አጋማሽ

የመከላከያ ቅያሪና ፍሬው ሰለሞን

በሁለተኛው አጋማሽ ጥሩ ሲንቀሳሰቀስ የዋለው መሃመድ ናስር በምንይሉ ወንድሙ ተቀይሮ ወጣ፡፡ የምንይሉ መግባትም የመከላከያን አጨዋወት ወደ 4-4-1-1 ቅርፅ ለውጦታል፡፡ ምንይሉ ከሞሃመድ ይበልጥ ቀጥተኛ ሲሆን በመከላከሉና የፊት አጥቂው ሙሉአለምነን ከአማካዮቸ ጋር በማገናኘት ላይ የነበረው ተሳትፎ መልካም ነበር፡፡ ይህም የመከላከያ ሁለት አጥቂዎች በእለቱ ሲተገብሩት ከነበረው ተመሳሳይ አጨዋወት የተለየ መልክ እንዲኖረው አድረጎታል፡፡ ምንይሉ የሁለቱን የመስመር አማካዮች በተለይም የፍሬው ሰለሞንን የማጥቃት ሚና በመቀነስ ወደ መከላከሉና ፉልባኮቹን ወደማገዙ እንዲሸጋገሩ መንገድ ከፍቷል፡፡ (ምስል 3 በቀይ መስመር የተከበበው 14 ቁጥርን ይመልከቱ) ፍሬው ሰለሞን በሁለተኛው አጋማሽ በማጥቃት ላይ ከነበረው ድንቅ ተሳትፎ በተጨማሪ በመከላከሉ ላይም ታታሪ ሆኗል፡፡ በተደጋጋሚ ወደ ኋላ በመመለስ ለዮሃንስ ኃይሉ ሽፋን ከመስጠቱ በተጨማሪ በፍጥነት ወደ ማጥቃት በመሸጋገር የመከላከያን የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማቀጣጠል የሚያደርገው ጥረት የሚደንቅ ነበር፡፡ (ምስል 3 ላይ በቀይ የተከበበውን 10 ቁጥር ይመልከቱ ይመልከቱ…) ከዚህ በተጨማሪi የማራኪ ወርቁ(15 ቁጥር) በ ሳሙኤል ታዬ ተቀይሮ መግባት በደደቢት የቀኝ መስመር ላይ የነበbረውን ሰsፊ ክፍተት ለማጥበብና ብርሃኑ ቦጋለ ወደፊት እንዳይጓዝ አፍኖ በመያዝ ጥሩ አስተዋፅኦ አድርጓል፡፡
ደደቢት በአመዛኙ የተመሳሳይ ቅያሪን በማድረጉ ጨዋታው ላይ የጎላ ለውጥ መፍጠር አልቻለም፡፡ መስፍን ኪዳኔ በ ሰለሞን ኃ/ማርያም ፣ በረከተ ይሳቅ በሽመክት ጉግሳ ተቀይረው ቢገቡም የሚታይ ታክቲካዊ ለውጥ ሳይፈጥሩ ጨዋታው በመከላከያ የበላይነት ተጠናቋል፡፡

 

Dedebit 0-1 Mekelakeya (3)

ያጋሩ