ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ዙር በመሪነት አጠናቋል

በዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ድሬዳዋ ከተማን 2-1 በመርታት በመሪነቱ ሲቀጥል ድሬዳዋ ከተማ አራተኛ ተከታታይ ሽንፈት አስተናግዷል።

10፡00 ላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ ፈረሰኞቹ በ14ኛ ሣምንት ሀዲያ ሆሳዕናን 1-0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ግብ ጠባቂ ቦታ ላይ ቻርለስ ሉክዋጎ በባህሩ ነጋሽ ፣ ናትናኤል ዘለቀ በሀይደር ሸረፋ እና አማኑኤል ገብረሚካኤል በቸርነት ጉግሣ ተተክተው ገብተዋል።

\"\"

ብርቱካናማዎቹ በበኩላቸው በ14ኛ ሣምንት በአርባምንጭ ከተማ 3-1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የስድስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ግብጠባቂው ፍሬው ጌታሁን በአብዩ ካሳዬ ሲተካ መሐመድ አብዱለጢፍ ፣ አሳንቴ ጎድፍሬድ ፣ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ፣ ሙኸዲን ሙሳ እና ቢኒያም ጌታቸው ደግሞ በመሳይ ጳውሎስ ፣ ጫላ በንቲ ፣ ጋዲሳ መብራቴ ፣ አቤል ከበደ እና ቻርለስ ሙሴጌ ተተክተው ጀምረዋል።

ቀዝቃዛ በነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ እና በግብ ሙከራዎች ቅዱስ ጊዮርጊሶች ብልጫውን ሲወስዱ የጠሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን በሁለቱም በኩል የተጠበቀውን ጠንካራ ፉክክር አላስመለከተንም። 22ኛው ደቂቃ ላይ ጊዮርጊሶች በግራው የማጥቂያ ክፍላቸው በጥሩ ቅብብል የወሰዱትን ኳስ በመጨረሻም አማኑኤል ገብረሚካኤል ሳጥን ውስጥ ለነበረው ኢስማኤል ኦሮ አጎሮ ሲያቀብል ኳሱን ለማስቆጠር ማመቻቸት የቻለው አጎሮ ያደረገውን ሙከራ አሳንቴ ጎድፍሬድ ተደርቦ የኳሱን ኃይል ሲቀንሰው ያገኘው ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ይዞበታል።

\"\"

27ኛው ደቂቃ ላይ አማኑኤል ገብረሚካኤልን በጉዳት ምክንያት በቸርነት ጉግሣ ቀይረው ለማስወጣት የተገደዱት ፈረሰኞቹ 38ኛው ደቂቃ ላይም ጥሩ የግብ ዕድል አግኝተው ነበር። እንየው ካሳሁን በግንባሩ በመግጨት ለማራቅ የሞከረው ኳስ አቅጣጫ ቀይሮ ከማቀበል አማራጭ ጋር የደረሰው ሱሌማን ሀሚድ ኃይል በሌለው የግንባር ኳስ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ እጅግ የተቸገሩት ድሬዳዋ ከተማዎች 30ኛው ደቂቃ ላይ እንየው ካሣሁን ከቀኝ መስመር በግሩም ሁኔታ ወደ ሳጥን አሻግሮት ሙኸዲን ሙሳ በደካማ የጊዜ አጠባበቅ በግንባሩ ሳያገኘው የቀረው ኳስ በአጋማሹ የፈጠሩት የተሻለ የግብ ዕድል ነበር።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው እጅግ ተሻሽሎ ሲቀጥል አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ ያልተረጋጋውን የአማካይ እና የአጥቂ ቦታ ተጫዋቾች ግንኙነት ያሬድ ታደሠን በሙኸዲን ሙሳ ቀይረው በማስገባት ለማስተካከል ሲጥሩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩልም በመጠኑ ማሻሻል ችለዋል። ሆኖም ግን ቅዱስ ጊዮርጊስ 56ኛው ደቂቃ ላይ ጨዋታውን መምራት ጀምሯል። ረመዳን የሱፍ በግሩም ዕይታ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው አቤል ያለው በግንባሩ በመግጨት አስቆጥሮታል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በተሻለ የማጥቃት እንቅስቃሴ ፈታኝ እየሆኑ የሄዱት ብርቱካናማዎቹ 58ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ፍፁም ተቃርበው ነበር። አብዱለጢፍ መሐመድ በግራ መስመር ከተገኘ የማዕዘን ምት ያሻማውን ኳስ ያገኘው አሳንቴ ጎድፍሬድ በግንባሩ ገጭቶ ከግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ማሳለፍ ቢችልም ናትናኤል ዘለቀ በግሩም የጊዜ አጠባበቅ በግንባሩ በመግጨት ግብ ከመሆን ሲያግድበት በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት ግን የአቻነት ግብ አስቆጥረዋል። አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከቅጣት ምት የመታው ኳስ ነጥሮ ያገኘው ግብ ጠባቂው ቻርለስ ሉክዋጎ ሊቆጣጠረው ባለመቻሉ ኳሱ ሲመለስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረው ቢኒያም ጌታቸው ማስቆጠር ችሏል።

ግብ በተቆጠረባቸው ቅፅበት መረጋጋት ተስኗቸው ተጨማሪ ስህተት መሥራት የቀጠሉት የአሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ ተጫዋቾች ቀስ በቀስ ግን ወደ ነበራቸው ግለት በመመለስ ጨዋታውን መቆጣጠር ሲችሉ ሁለት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችም ማድረግ ችለው ነበር። በቅድሚያም 74ኛው ደቂቃ ላይ እስማኤል ኦሮ አጎሮ በሳጥኑ የግራ ክፍል ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ግብ ሲሞክር ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን መልሶበታል። ያንኑ ኳስ ያገኘው አቤል ያለው ሌላ ሙከራ ቢያደርግም ተከላካዩ አሳንቴ ጎድፍሬድ በግሩም ቦታ አያያዝ ግብ ከመሆን አግዶበታል። በስድስት ደቂቃዎች ልዩነትም አቤል ያለው ከሱሌይማን ሀሚድ ከረጅም ርቀት በተሻገረለት ኳስ ጥሩ ሙከራ ቢያደርግም ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን በጥሩ ቅልጥፍና መልሶበታል።

ያለማቋረጥ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን የቀጠሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች 85ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸው የማሸነፊያ ግብ አስቆጥረዋል። ሱሌይማን ሀሚድ በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻማውን ኳስ በፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባር ተጨርፎ ያገኘው እስማኤል ኦሮ አጎሮ በቀላሉ ማስቆጠር ችሏል።

የአቻነት ግብ ካስቆጠሩ በኋላ ከራሳቸው የግብ ክልል በቁጥር በዝተው በመገኘት መከላከልን የመረጡት ድሬዎች ግብ ካስቆጠሩ በኋላ 90ኛው ደቂቃ ላይ ዮሴፍ ዮሐንስ ከቅጣት ምት ካደረገው ፈታኝ ያልሆነ ሙከራ ውጪ የተሻለ ሙከራ ለማድረግ ሲቸገሩ ጨዋታውም በቅዱስ ጊዮርጊስ የ 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ውጤቱን ተከትሎም ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያውን ዙር በመሪነት አጠናቋል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የድሬዳዋ ከተማው አሰልጣኝ ዮርዳኖስ ዓባይ ከሌላው ጊዜ የተሻሉ እንደነበሩ እና ከመስመር የሚሻገሩ ኳሶች ላይ ልምምድ ላይ ቢሰሩም ግብ እያስተናገዱበት መሆኑ ለሽንፈታቸው እንደ ምክንያት ሲናገሩ የነበራቸውን የማሸነፍ ስሜት አለማስቀጠላቸው እንዳስከፋቸው ገልፀዋል። ድል የቀናቸው የቅዱስ ጊዮርጊሱ አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ በበኩላቸው ጨዋታው ላይ የፈለጉትን ነገር እንዳገኙ እና ውጤቱ እንደሚገባቸው ሲናገሩ ጥሩ ጨዋታ ተጫውተው ድል ማድረግ ግዴታቸው እንደነበር ገልጸዋል። ውጤቱንም ለደጋፊዎቻቸው በስጦታ አበርክተዋል።