ሪፖርት | የመጀመሪያው ዙር የመጨረሻ ጨዋታ ያለግብ ተጠናቋል

ምሽት ላይ ባህር ዳር ከተማ እና ወላይታ ድቻን ያገናኘው ጨዋታ 0-0 በሆነ ውጤት ተቋጭቷል።

ባህር ዳር ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥብ ሲጋራ ከተጠቀመበት አሰላለፍ ቻርለስ ሪባኑን በበረከት ጥጋቡ ቦታ በመጠቀም ለዛሬው ጨዋታ ቀርቧል። በወልቂጤ ከተማ ሽንፈት ያስተናገደው ወላይታ ድቻ ደግሞ በኬኔዲ ከበደ ፣ በኃይሉ ተሻገር እና ዘላለም አባቴ ምትክ ያሬድ ዳዊት ፣ አበባየሁ አጂሶ እና ስንታየሁ መንግሥቱን በመጀመሪያ አሰላለፉ ውስጥ አካቷል።

በጨዋታው ጅማሮ ቡድኖቹ በፍጥነት ወደ ግብ ለመድረስ የመጣር ምልክቶች አሳይተዋል። ባህር ዳር ከተማ ከተጋጣሚው በተሻለ ቅብብሎችን ለመከወን ሲሞክር ወላይታ ድቻ ደግሞ በቁጥር ባነሱ ንክኪዎች ከመስመር እና ከመሀል ኳሶችን ወደ ፊት ማድረስን ምርጫው አድርጓል። በዚህም ቡድኑ ቀዳሚውን ሙከራ 18ኛ ደቂቃ ላይ ሲያደርግ ቢኒያም ፍቅሩ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ ቃልኪዳን ዘላለም በግንባሩ ለመግጨት ሞክሮ አምክኖታል።

ከድቻ ሙከራ በኋላ ከቀድመው በተሻለ የኳስ ቁጥጥራቸው የተሻሻለው የጣና ሞገዶቹ 28ኛው ደቂቃ ላይ ጥሩ መከራ አድርገዋል። በግራ መስመር ከሄኖክ ኢሳይያስ የተሻገረውን ኳስ ሳጥን ውስጥ ፍፁም ጥላሁን አመቻችቶለት ፋሲል አበባየው ያደረገው ሙከራ በቢኒያም ገነቱ ድኗል። አጋማሹ የተመጣጠነ ፉክክር እየተደረገበት ሲቀጥል የወላይታ ድቻ ከመስመር የሚነሱ እና የመልሶ ማጥቃት ጥረቶች ጎልተዋል። 36ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየሁ መንግሥቱ ሳጥን ውስጥ ያወረደውን ረጅም ኳስ ሲያዘጋጅለት አናጋው ባደግ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት አጋጣሚ ደግሞ የተሻለው የጦና ንቦቹ ሙከራ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ጉሽሚያዎች በርክተውበት እና በቅጣት ምቶች ታጅቦ የጀመረ ነበር። ከእነዚህም መካከል 52ኛ ደቂቃ ላይ ፉዓድ ፈረጃ ወደ ግራ ካደላ ረጅም ቅጣት ምት ያሻገረውን ኳስ ፍፁም ጥላሁን በግንባሩ ቢጨርፈውም ቢኒያም ገነቱ ያዳነበት ከባዱ የግብ አጋጣሚ ነበር። ጨዋታው ቀስ በቀስ ወደ ቀደመ ፉክክሩ ቢመለስም የግብ ዕድል መፍጠር ግን ለተጋጣሚዎቹ ቀላል አልሆነም። ቃልኪዳን ዘላለም እና ዱሬሳ ሸቢሳ ከረጅም ርቀት የደረጓቸው ሙከራዎች ካልሆኑ በቀር ግብ ጠባቂ ፈታኝ ሙከራዎች አልተገኙም።

ጨዋታው አንድ ሰዓት ካለፈው በኋላ ሁለቱም ቡድኖች በአጥቂ ክፍላቸው ላይ ሁለት ሁለት ቅያሪዎች አድርገዋል። በባህር ዳር ተቀያሪዎች ህብረት ሀብታሙ ታደሰ በአየር ያደረሰውን ኳስ አደም አባስ 78ኛው ደቂቃ ላይ በግንባሩ ሞክሮ ቢኒያም ገነቱ ያዳነበት ሙከራ በሽግግሮች ፍትጊያ ውስጥ የቆየውን ፍልሚያ ከግብ ሙከራ ጋር ያገናኘ ቅፅበት ነበር። ከሙከራውም ባሻገር የጣና ሞገዶቹ በቀሪ ደቂቃዎች የተሻለ ጫና በሚፈጥሩ ቅብብሎች እና ተሻጋሪ ኳሶች በድቻ ሳጥን አቅራቢያ ተበራክተው ተንቀሳቅሰዋል። በአንፃሩ የማጥቃት ሽግግራቸው ጥራት በሚፈልጉት ልክ ያልሆነላቸው የጦና ንቦቹ ሙሉ ለሙሉ ባያፈገፍጉም ወደ መከላከሉ አድልተው በቀጥተኛ ኳሶች ወደግብ ለመድረስ ሞክረዋል። ሆኖም ጨዋታው ያለግብ ሊጠናቀቅ ችሏል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የባህር ዳር ከተማው አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ጨዋታው ጥሩ ፉክክር ማስተናገዱን ገልፀው የተጋጣሚ ተጫዋቾች ሰዓት ለማባከን መሞከራቸውን ኮንነዋል። በተጨማሪም በተቻለ መጠን አጥቅተው መጫወታቸውን እና የአቻ ውጤቱ እንደሚያንሳቸው ተናግረዋል። ከሽንፈት መምጣታቸው ጨዋታውን በጥንቃቄ እንዲቀርቡ እንዳደረጋቸው ያነሱት የወላይታ ድቻው አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም ውጤቱ ተገቢ መሆኑን እና ተጫዋቾቻቸው ታክቲካሊ ዲስፕሊንድ ሆነው እንደተንቀሳቀሱ አስረድተዋል።

ያጋሩ