መረጃዎች | 63ኛ የጨዋታ ቀን

የመላው ጥቁር ህዝቦች የድል በዓል በሆነው የዓድዋ ድል 127ኛ ዓመት መታሰቢያ ዕለት በልዩ ድምቀት እንደሚደረጉ የሚጠበቁት እና ሁለተኛው ዙር የሊጉ ውድድር የሚበሰርባቸውን ሁለት ጨዋታዎችን የተመለከቱ መረጃዎች በተከታዩ መልኩ ይነበባሉ።

ሀዲያ ሆሳዕና ከ መቻል

የሁለተኛው ዙር ጅማሮ በሚበሰርበት መርሃግብር በተፃራሪ ወቅታዊ ብቃት ላይ የሚገኙትን ሁለቱን ቡድኖች ያገናኛል።

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ከነበራቸው የተቀዛቀዘ ተሳትፎ አንፃር በብዙዎች ዘንድ አስቸጋሪ ዓመት ሊያሳልፉ ይችላሉ ተብለው የተገመቱት ሀዲያ ሆሳዕናዎች በሊጉ መልካም በሚባል ግስጋሴ ቢጀምሩም አሁን ላይ ግን ነገሮች መልካቸውን እየቀየሩ ያሉ ይመስላል።

\"\"

ከመጨረሻ ዘጠኝ የሊግ ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፉት ሆሳዕናዎች በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ የ1-0 ውጤት በኢትዮጵያ መድን እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ተሸንፈው ወደ ነገው ጨዋታ የሚያመሩ ሲሆን ቡድኑ አሁን ላይ በ21 ነጥቦች በሰንጠረዡ 5ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በሊጉ በመጀመሪያው ዙር 9 ግቦችን ብቻ ማለትም በአማካይ በጨዋታ 0.6 ግቦችን ብቻ በማስተናገድ በሊጉ 2ኛው ጠንካራ የመከላከልን የገነቡት አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ በተቃራኒው ደግሞ በሊጉ ከለገጣፎ ለገዳዲ ቀጥሎ ከወላይታ ድቻ ጋር በጣምራ የሊጉ 2ኛ ደካማ የማጥቃት አፈፃፀም የነበረው ቡድናቸውን ለማሻሻል በዝውውር መስኮቱ ይሳተፋሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሆሳዕናዎች ግን ባላቸው ስብስብ ለመቀጠል የወሰኑ ሲሆን በእጃቸው ላይ ያሉትን ግብዓቶች ተጠቅመው ቡድን በሁለተኛው ዙር እንዴት ያሻሽሉታል የሚለው ጉዳይ ግን ይጠበቃል።

በመጨረሻ ባደረጓቸው ስድስት የሊግ ጨዋታዎች ያልተሸነፉት መቻሎች በሦስቱ ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ይዘው በመውጣት(የለገጣፎ ለገዳዲውን ፎርፌ ጨምሮ) አሁን ላይ በ20 ነጥቦች በሰንጠረዡ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።

በክረምቱ ካደረጓቸው በርካታ ዝውውሮች አንፃር እንደ ቡድን ለመዋሀድ ብዙ ጊዜ የወሰደባቸው የሚመስሉት መቻሎች አሁን ላይ ግን ያንን ቀመር እያገኙት የመጡ ይመስላል በዚህም በሁለተኛው ዙር ከመጀመሪያው በተሻለ አስፈሪ ቡድን ሆነው እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።በተለይም ደግሞ በመጀመሪያዎቹ የጨዋታ ሳምንታት ከቀደመ ስማቸው አንፃር ስማቸውን ለመኖር ተቸግረው የነበሩት የቡድኑ ከወገብ በላይ ተሰላፊዎች እጅግ ጥሩ የሚባልን ለውጥ በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች እያስመለከቱ መገኘታቸው ለአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ይበልጥ የልብ ልብ የሚሰጥ ይሆናል።

መቻሎች በነገው ጨዋታ ዳዊት ማሞን በጉዳት የማያገኙ ሲሆን ከጉዳት ጋር እየታገለ የሚገኘው ወጣቱ አጥቂ ተሾመ በላቸው የመሰለፍ ነገርም አጠራጣሪ ሆኗል።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር ባደረጉት ጨዋታ መቻሎች በምንይሉ ወንድሙ ብቸኛ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ አሸንፈው መውጣት የቻሉ ሲሆን በድምሩ በሊጉ ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች መቻል በሦስቱ በማሸነፍ የበላይነት ሲይዙ ሀዲያ ሆሳዕናዎች አንዴ እንዲሁም ቀሪው አንድ ጨዋታ ደግሞ ነጥብ በመጋራት የተጠናቀቀ ነበር።

አርባምንጭ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

የዕለቱ ሁለተኛ መርሃግብር በሦስት ነጥቦች ልዩነት ብቻ 14ኛ ደረጃ የሚገኙትን አርባምንጭ ከተማዎችን 9ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች ያገናኛል።

አርባምንጭ ከተማዎች በመጀመሪያው ዙር የሊግ ውድድር ካደረጓቸው አስራ አምስት ጨዋታዎች ሦስቱን ብቻ ድል ሲያደርጉ ቡድኑ በሊጉ ካሉ አስራ ስድስት ክለቦች ከፍተኛውን የአቻ መጠን ማለትም ስምንት ጨዋታዎችን(53.4%) በአቻ ውጤት ሲፈፅሙ በተቀሩት አራት ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፈዋል።

በመከላከሉም ሆነ በማጥቃቱ በብዙ ረገድ መሻሻል የሚገባው ቡድኑ በተለይ ዓምና በሙሉ የውድድር ዘመን 26 ግቦችን ብቻ ያስተናገደ ጥሩ የሚባል የመከላከል መዋቅር መገንባታቸው ለቡድኑ በሊጉ ጥሩ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቅ ቁልፍ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ግን ከወዲሁ በመጀመሪያ ዙር ብቻ 20 ግቦችን ማስተናገዳቸው በተለይ በመከላከሉ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ብዙ ስራዎች እንዳሉበት ማሳያ ነው።

\"\"

ለዚህም ይመስላል በአጋማሹ የዝውውር መስኮት የተከላካይ መስመራቸውን ለማጠናከር በማሰብ አበበ ጥላሁንን ከኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ዮሀንስ ተስፋዬን ከቤንች ማጂ ቡና ማስፈረም የቻሉ ሲሆን የሁለቱን ተጫዋቾች ግልጋሎት ከነገ አንስቶ ማግኘት የሚጀምሩ ይሆናል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በነገው ጨዋታ ሙና በቀለን በአምስት ቢጫ ካርድ ቅጣት ከማጣቱ በቀር ሙሉ ስብስቡ ለጨዋታው ብቁ መሆኑ ታውቋል።

በሰንጠረዡ በ20 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ወልቂጤ ከተማዎች በመጀመሪያ ዙር ያደረጋቸውን አስራ አምስት የሊግ ጨዋታዎችን በእኩል መጠን ለሦስቱም ውጤቶች ማከፋፈል ችለዋል። በሰንጠረዡ ወገብ ላይ የሚገኘው ቡድኑ ከሊጉ መሪ በ12 ነጥብ ዝቅ ብሎ ሲቀመጥ ከ14ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው አርባምንጭ ደግሞ በ3 ነጥቦች ከፍ ብለው የተቀመጡ ሲሆን ሊጉ በክለቦች መካከል ካለው የነጥብ መቀራረብ አንፃር በመጨረሻው ጨዋታ በአዳማ ከተማ ካስተናገዱበት ሽንፈት በፍጥነት ማገገም ይጠበቅባቸዋል።

በወልቂጤ ከተማዎች በኩል የቡድኑ አምበል እንዲሁም ወሳኝ ተጫዋች የሆነው ጌታነህ ከበደ ኢትዮጵያ መድን ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ግብ ካስቆጠረ በኃላ በመጨረሻ ሦስት ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥር ቢቆይም በመጨረሻው ጨዋታ በአዳማ ከተማ ሲረቱ ብቸኛዋን የማስተዛዘኛ ግብ በማስቆጠር ወደ አግቢነት የተመለሰ ሲሆን በ11 ግቦች የሊጉ 2ኛ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ጌታነህ ወደ አግቢነት መመለስ ለወልቂጤዎች ተስፋን የሚፈነጥቅ ዜና ነው።

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በነገው ጨዋታ በርከት ያሉ ተጫዋቾቻቸውን በጉዳት አያገኙም ፤ አስራት መገርሳ ፣ ተመስገን በጅሮንድ ፣ አቡበከር ሳኒ ፣ ቴዎድሮስ ሀሙ ፣ አንዋር በጉዳት ከነገው ጨዋታ ውጭ ሲሆን ዩጋንዳዊው የግብ ዘብ ሮበርት ኦዶንካራ ደግሞ ቡድኑን እስካሁን መቀላቀል ባለመቻሉ በነገው ጨዋታ አይኖርም።

ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያ ዙር የመክፈቻ የጨዋታ ሳምንት ሲገናኙ ወልቂጤ ከተማዎች በጌታነህ ከበደ ብቸኛ ግብ ማሸነፍ ችለው የነበሩ ሲሆን በሊጉም እስካሁን በድምሩ ለሦስት ያክል ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን በዚህም ወልቂጤ ከተማዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፉ ቀሪው አንድ ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት የተጠናቀቀ ነበር።