መቻል ያገኘው የፎርፌ ውጤት ፀድቋል

የመቻል እና ለገጣፎ ለገዳዲ ጨዋታ በፎርፌ ውጤት መፅደቁ ይፋ ሆኗል።

\"\"

ከ15ኛ ሳምንት መርሐ-ግብሮች መካከል አንዱ የሆነው የመቻል እና ለገጣፎ ለገዳዲ ጨዋታ ለገጣፎ በሁለተኛው ዙር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ያስፈረማቸውን ተጫዋቾች የአንደኛው ዙር የሊጉ ውድድር ሳይጠናቀቅ መጠቀም አይችልም በሚል ውዝግቦች ተነስተውበት የጣፎ የቡድን አባላት ወደ ሜዳ መግባት ሳይችሉ ቀርተው የመቻል ተጫዋቾች እና የዕለቱ ዳኞች ግን ወደ ሜዳ በመግባት 30 ደቂቃ ከቆዩ በኋላ ጨዋታው በፎርፌ ውጤት እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ ሂደቶች ተከናውነው እንደነበር አይዘነጋም።

\"\"

የሊጉ የውድድር እና ሥነ-ስርዓት ኮሚቴም የጨዋታ ሳምንቱ ከተጠናቀቀ በኋላ ዛሬ ረፋድ 4 ሰዓት የኮሚሽነሮችን ሪፖርት ሲመለከት ነበር። በዚህም ለገጣፎ ለገዳዲ ከመቻል ጋር ባደረገው የ15ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ ቡድኑ ባለማቅረቡ ጨዋታው ሳይካሄድ ስለመቅረቱ ሪፖርት ተደርጎ ክለቡ በፎርፌ ተሸናፊ ሆኖ 0 ነጥብና 3 የግብ ዕዳ እንዲመዘገብበትና ተጋጣሚው መቻል በፎርፌ አሸናፊ ሆኖ 3 ነጥብና 3 ተደማሪ ግብ እንዲመዘገብለት እንዲሁም ተጨማሪ የዲሲፕሊን እርምጃዎች የለገጣፎ ቡድን ለፌዴሬሽን ያስገባው ኣቤቱታ ውሳኔ እስኪሰጠው ድረስ በይደር እንዲቆይ ተወስኗል፡፡