የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ የሁለተኛ ዙር መርሐግብር ዛሬ ሲጀመር ድሬዳዋ ከተማ ፣ ይርጋጨፌ ቡና እና መቻል ድል ቀንቷቸዋል።
ድሬዳዋ ከተማ 1-0 ቅዱስ ጊዮርጊስ
የሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን ከቅዱስ ጊዮርጊስ አገናኝቷል። ጨዋታው የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቶ ባሕሩ ጥላሁን እና አንተርናሽናል ዋና ዳኛ ሊዲያ ታፈሰን ጨምሮ ሌሎች የክብር እንግዶች በተገኙበት የመክፈቻ ፕሮግራም ተደርጓል። ጨዋታው ገና በ7ኛው ደቂቃ ግብ ሲያስመለክተን ሜላት ደመቀ በግራ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት በድንቅ ሁኔታ አስቆጥራው ደሬዳዋን መሪ ማድረግ ችላለች። ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ለተመልካች እጅግ ማራኪ የሆነ የኳስ ቅብብል በማድረግ ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉት እንስት ፈረሰኞች 11ኛው ደቂቃ ላይ ቃልኪዳን ወንድሙ እና 23ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ ገብርኤላ አበበ ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ ግን የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል።
በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ የተወሰደባቸው ድሬዎች 31ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ፀሐይ ኢፋሞ በቀኝ መስመር ከተገኘ የቅጣት ምት ያሻገረችውን ኳስ ብቻዋን ያገኘቸው አምበሏ መስከረም ኢሳያስ በግንባሯ ገጭታ ያደረገችው ሙከራ ዒላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል። ከዕረፍት መልስ ጨዋታው በመጠኑ ተቀዛቅዞ ሲቀጥል የጨዋታው መጠናቀቂያ ላይ የጊዮርጊሷ ኢየሩስ ወንድሙ ከቅጣት ምት ያደረገችው እና የግቡን አግዳሚ ተጠግቶ የወጣው ኳስ በአጋማሹ የተሻለው ሙከራ ነበር። ጨዋታውም በድሬዳዋ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ይርጋጨፌ ቡና 4-2 ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ
መጠነኛ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ ንፋስ ስልኮች በ5ኛው ደቂቃ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። መቅደስ ተስፋዬ ያሻገረችላትን ኳስ ያገኘችው ዓለም በየቻ በግሩም አጨራረስ አስቆጥራዋለች። በተደጋጋሚ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ንፋስ ስልኮች 32ኛው ደቂቃ ላይ በሬዱ በቀለ ግብ ጠባቂዋን አልፋ ባስቆጠረችው ግብ መሪነታቸውን ሲያጠናክሩ ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው መመለስ የቻሉት ይርጋጨፌ ቡናዎች 39ኛው ደቂቃ ላይ ዳግማዊት ሰለሞን ከሳጥን አጠገብ ባስቆጠረችው ድንቅ ግብ ወደ ጨዋታው ተመልሰዋል።
ጨዋታው ከዕረፍት ሲመለስ 47ኛው ደቂቃ ላይ ንፋስ ስልኮች ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። መቅደስ ተስፋዬ ከሳጥን አጠገብ ያደረገችውን ሙከራ የግቡ አግዳሚ ገጭቶ መልሶባታል። ከዚህ ሙከራ በኋላ ግን ጨዋታውን ፍጹም በሆነ የበላይነት የተቆጣጠሩት ይርጋጨፌዎች ሦስት ግቦችን አከታትለው አስቆጠረዋል። በቅድሚያም 48ኛው ደቂቃ ላይ መስታዎት አመሎ ባስቆጠረችው የአቻነት ግብ ወደ ጨዋታው የተመለሱት ቡናዎች 62ኛው ደቂቃ ላይ በፍሬሕይወት ተስፋዬ ግብ ጨዋታውን መምራት ጀምረዋል። በአንድ ደቂቃ ልዩነትም መታሰቢያ ክፍሌ ከረጅም ርቀት ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ሸዊት አብርሃ በድንቅ ብቃት ስታስወጣባት 85ኛው ደቂቃ ላይ ግን ፍሬሕይወት ተስፋዬ ለራሷ ሁለተኛውን ለቡድኗ አራተኛውን ግብ አስቆጥራ ጨዋታው በይርጋጨፌ ቡና 4-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
መቻል 3-1 ልደታ ክ/ከተማ
ሴናፍ ዋቁማ ደምቃ በታየችበት የመጀመሪያ አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫውን ለመውሰድ ብርቱ ፉክክር ሲያስመለክተን የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ በኩል ግን መቻሎች የተሻሉ ነበሩ። 16ኛው ደቂቃ ላይ በሴናፍ ዋቁማ ግብ ጨዋታውን መምራት የጀመሩት መቻሎች 27ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ሴናፍ ዋቁማ ሳጥን ውስጥ ዓየር ላይ እንዳለ የሞከረችው ኳስ የግቡን የግራ ቋሚ ገጭቶ ተመልሶባታል።
በራሳቸው የሜዳ ክፍል በጥሩ ቅብብል የታጀበ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመጠጋት የተቸገሩት ልደታዎች የጠራ የግብ ዕድል መፍጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። ይባስ ብሎም 42ኛው ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስተናግደዋል። ሴናፍ ዋቁማ ከሳጥን ውጪ ድንቅ ግብ አስቆጥራ መቻል በሁለት ግቦች እየመራ ወደ ዕረፍት እንዲያመራ አስችላለች።
ከዕረፍት መልስ ልደታዎች እጅግ ተሻሽለው በመቅረብ በኳስ ቁጥጥሩ መጠነኛ ብልጫ ቢወስዱም ነጻነት ፀጋዬ ራሷ ላይ ካስቆጠረችላቸው ግብ ውጪ ንጹህ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ቢወሰድባቸውም አልፎ አልፎ ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴ የሚያደርጉት መቻሎች 78ኛው ደቂቃ ላይ መሠረት ምክሬ ራሷ ላይ ባስቆጠረች ግብ መሪነታቸውን አጠናክረዋል። ለግቧ መገኘትም የመቻሏ ቤተልሔም በቀለ ጥረት የሚደነቅ ነበር። ጨዋታውን በመቻል 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።